“ድሬዳዋ አሁን ያለበት ውጤት ቡድኑን የሚገልፅ አይደለም” – ዳንኤል ኃይሉ

በድሬዳዋ የመጀመርያ ጨዋታው ጥሩ ከመንቀሳቀሱ ባሻገር ጎል ማስቆጠር የቻለው ዳንኤል ኃይሉ የሚናገረው አለው።

ባህር ዳር ተወልዶ ያደገው ዳንኤል ለባህር ዳር ከተማ ጥሩ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቶ በዘንድሮ የውድድር ዓመት ሰበታን በመቀላቀል የመጀመርያውን ዙር በክለቡ ማሳለፉ ይታወሳል። አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ አማካዩን ወደ ቡድናቸው ለመቀላቀል በነበራቸው ፍላጎት መነሻነት ከሰበታ ጋር በስምምነት በመለያየት ወደ ምሥራቁ ክለብ ድሬዳዋ ማረፊያውን በማድረግ ዛሴ የመጀመርያ ጨዋታውን አድርጓል። ተጫዋቹ ቡድኑን ከስድስት ሳምንት ድል መራቅ በኃላ ያሸነፈበትን ብቸኛ ጎል በፍፁም ቅጣት ምት ሲያስቆጥር ከስመ ሞክሼው ዳንኤል ደምሴ ጋር ጥሩ ጥምረት ፈጥሮ ውሏል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም ሶከር ኢትዮጵያ ተከታዩን ሀሳብ አጋርቷል።

“ሰበታ በነበረኝ ቆይታ በጣም ደስተኛ ነበርኩ። አሰልጣኝ ዘማርያም በቡድን ውስጥ ያለበትን ክፍተት እንድሸፍን ከእርሱ በመጣ ግፊት ከአሰልጣኝ አብርሀም ጋር በመነጋገር ወደ ድሬዳዋ ልመጣ ችያለሁ።

“በመጀመርያ ድሬዳዋ አሁን ያለበት ውጤት ቡድኑን የሚገልፅ አይደለም። እዚህ ከመጣው በኋላ ያስተዋልኩት የተጫዋቾቹ የመጫወት ፍላጎታቸው የአሰልጣኞቹ የአመራሮቹ ተነሳሽነት ከፍተኛ መሆኑ ይህ ውጤት አይገባቸውም ብዬ አስብ ነበር። ፈጣሪ ይነስገን በመጀመርያ ጨዋታዬ በኔ ጎል በማሸነፋችን በጣም ደስ ብሎኛል። ፈጣሪም የተመሰገነ ይሁን። ውጤቱም ለተጫዋቾቹ ለአሰልጣኞቹ አጠቃላይ ለቡድኑ አባላት የተሻለ ነገር እንድንሰራ ትልቅ መነሳሳት ይፈጥራል።

“ከጨዋታው በፊት አሰልጣኝ ዘማርያም ሦስት ነጥብ እንደሚፈልግ እና እንደናፈቀው ነግሮን ነበር። እኛም እንደ ቡድን ዛሬ እናደርግልሀለን ብለን ቃል ገብተን ስለነበር ጎሉን አግብቼ ከጓደኛዬ ጋር በመሆን ሦስቱን ነጥብ ወደ ኪስህ አስገብተንልሀል ቃላችንን ጠብቀናል ለማለት ነው ጎሉን አግብተን ደስታችንን የገለፅንበት መንገድ በዚህ መልኩ ለመሆን የቻለው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ