ሪፖርት | የጣናው ሞገዶቹ አራተኛ ተከታታይ ድላቸውን አስመዝግበዋል

ወልቂጤ ከተማን ሁለት ለምንም የረቱት ባህር ዳር ከተማዎች ቅዱስ ጊዮርጊስን በመብለጥ ሦስተኛ ደረጃን የያዙበትን ውጤት አስመዝግበዋል።

በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመሩት ባህር ዳር ከተማዎች በ16ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ አዳማ ከተማን ከረቱበት ስብስባቸው ሦስት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም ሀሪሰን ሄሱን በፂዮን መርዕድ፣ ፍፁም ዓለሙን በአፈወርቅ ኃይሉ እንዲሁም ወሰኑ ዓሊን በግርማ ዲሳሳ ተተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በተመሳሳይ አሠልጣኝ ደግአረገ ይግዛውም ከመጨረሻ ጨዋታቸው ሦስት ተጫዋቾች ለውጠው ለጨዋታው ቀርበዋል። በዚህም አዲስ ፈራሚያቸው እስራኤል እሸቱ እንዲሁም ፍሬው ሰለሞን እና ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስን በሄኖክ አየለ፣ ያሬድ ታደሰ እና በኃይሉ ተሻገር ምትክ ጨዋታውን ጀምረዋል።

ጨዋታውን በተሻለ ንቃት የጀመሩት የሚመስሉት ባህር ዳር ከተማዎች ከወልቂጤ በተሻለ ኳስን ተቆጣጥረው ሲጫወቱ ታይቷል። ቡድኑም የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ በ8ኛው ደቂቃ በግርማ ዲሳሳ አማካኝነት ሰንዝሮ ጀማል ጣሰው አምክኖበታል። በአንፃሩ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን ሲጠባበቁ የነበሩት ወልቂጤ ከተማዎች ደግሞ በ10ኛው ደቂቃ አብዱልከሪም ወርቁ እና ረመዳን የሱፍ በፈጠሩት አስገራሚ የኳስ ቅብብል የተገኘውን ኳስ አብዱልከሪም ወደ ጎል ሞክሮት ቀዳሚ ለመሆን ተቃርበው ነበር። ከዚህ ሙከራ በተጨማሪም በ17ኛው ደቂቃ የተገኘውን የመዓዘን ምት በመጠቀም ቶማስ ስምረቱ ሌላ ጥቃት ፈፅሞ ነበር።

የማጥቃት ሀይላቸውን በግራ መስመር በኩል በማድረግ ጨዋታውን የቀጠሉት ባህር ዳሮች በ21ኛው ደቂቃ በድጋሜ ግርማ በሞከረው ጥብቅ ኳስ የተጋጣሚያቸውን የግብ ክልል ፈትሸው ተመልሰዋል። ከደቂቃ ደቂቃ እድገት እያሳዩ የመጡት ሠራተኞቹ በበኩላቸው ፈጣኑ ተጫዋቻቸው አብዱልከሪም ወርቁ በሚፈጥራቸው የግብ ዕድሎች ታግዘው ባህር ዳርን ለማስጨነቅ ሲሞክሩ ተስተውሏል። በተቃራኒው ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው መጫወትን በቀጣዮቹ ደቂቃዎች የመረጡት ባህር ዳሮች በ33ኛው ደቂቃ የወልቂጤ ተጫዋች የተሳሳተውን ኳስ በመጠቀም ያገኙትን ዕድል በሳለአምላክ አማካኝነት ወደ ጎልነት ለመቀየር ታትረዋል። ይሁን እና ሳለአምላክ የሞከረው ኳስ ጀማልን እምብዛም ሳይፈትን መክኗል። አጋማሹ ሊገባደድ አራት ደቂቃዎች ሲቀሩት ግን ቡድኑ እጅግ መሪ ለመሆን ተቃርቦ ነበር። በዚህ ደቂቃም ባዬ ገዛኸኝ ወደ ግራ ባዘነበለ ቦታ ላይ ያገኘውን ኳስ ወደ ጎል ሲመታው የግቡ አግዳሚ መልሶበታል። የተመለሰውን ኳስ በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ሳለአምላክ ቢያገኘውን ዕድሉም ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በአጋማሹ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የነበራቸው ወልቂጤዎች የተቆጣጠሩትን ኳስ ወደ ጎልነት መቀየር ሳይችሉ ያለምንም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ እጅግ ተነቃቅተው ወደ ሜደ የገቡት ባህር ዳር ከተማዎች በአንድ ደቂቃ ልዩነት ባስቆጠሯቸው ሁለት ጎሎች መሪ ሆነዋል። በቅድሚያም የቡድኑ የመሐል አጥቂ ባዬ ገዛኸኝ ከሳምሶን ጥላሁን የተቀበለውን ኳስ መረብ ላይ አሳርፏል። ይህ ጎል ይበልጥ ያነቃቃው ቡድኑ ድጋሜ በ55ኛው ደቂቃ ግርማ የግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰውን መውጣት ተከትሎ ወደ ጎል በመታው ውብ ኳስ መሪነታቸውን ወደ ሁለት አስፍተዋል።


ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ማድረጋቸውን የቀጠሉት ወልቂጤዎች በ66ኛው ደቂቃ ረመዳን ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመታው ኳስ ጥቃት ሰንዝረዋል። ከደቂቃ በኋላም ቡድኑ ተቀይሮ ወደ ሜዳ በገባው አቡበከር ሳኒ እና አብዱልከሪም እጅግ ጥሩ ሙከራዎች ታግዞ የባህር ዳርን የግብ ክልል ጎብኝቷል። የቡድኑ አሠልጣኝ ደግአረገም የማጥቃት ሀይላቸውን በይበልጥ ለማጠናከር የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ለውጠው በማስገባት ከጨዋታው ነጥብ ለማግኘት ታትረዋል። በ81ኛው ደቂቃም አህመድ ሁሴን ድንቅ ሙከራ ተገልብጦ በመምታት አድርጎ ነበር። አህመድ ይህንን ሙከራ ካደረገ ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም ረመዳን ከመስመር ባሻገረለት ኳስ ተጠቅሞ ሌላ ጥቃት በግንባሩ ፈፅሟል።

መሪነታቸው ተረጋግተው እንዲጫወቱ ዕድል የሰጣቸው ባህር ዳሮች ቀሪዎቹን ደቂቃዎች ተከላክለው በመጫወት ነገር ግን የወልቂጤ ተጫዋቾች ለማጥቃት ትተውት የሄዱትን ሰፊ ቦታ በፍጥነት በማጥቃት ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ሞክረዋል። ግብ ካስተናገዱ በኋላ በተሻለ ተጭነው ለመጫወት የሞከረት ወልቂጤዎች ግን ውጥናቸው ሳይሰምር ተሸንፈው ከሜዳ ወጥተዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ነጥባቸውን 29 ያደረሱት ባህር ዳር ከተማዎች ደረጃቸውን ከአራተኛ ወደ ሦስተኛ አሳድገዋል። በተቃራኒው ሦስት ነጥብ ያስረከቡት ወልቂጤዎች በሰበሰቧቸው 20 ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ ፀንተው ተቀምጠዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ