“በሠራሁት ነገር ተፀፅቼ ንሰሀ ገብቻለሁ…” – ብርሃኑ ግዛው

ሉሲዎቹ ነገ እና ማክሰኞ የሚያደርጉትን የአቋም መፈተሻ ጨዋታን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

ከስምንት ሰዓት ጀምሮ በተከናወነው በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው እና አምበሏ ሎዛ አበራ ተገኝተው ሀሳባቸውን ተናግረዋል። ለሀምሳ ደቂቃዎች በቆየው መግለጫ ላይም ስለ ተጫዋቾች ምርጫ፣ ስለ ዝግጅት እና ስለደቡብ ሱዳኑ የአቋም መለኪያ ጨዋታ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። በቅድሚያም የቡድኑ አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው አጠር ያለ ማብራሪያቸውን በስፍራው ለተገኙ ጥቂት የብዙሃን መገናኛ አባላት ሰጥተዋል።

“ዘንድሮ የተደረጉት የሊግ ውድድሮች በአንድ ቦታ ላይ ስለነበሩ ትልቅ ጥቅም ሰጥቶናል። በተለይም የየክለቦቹ አሠልጣኞች እና በስፖርቱ አካባቢ ያሉ ሰዎች አንድ ላይ ስለነበርን እየተነጋገርን በጎ ነገሮችን ለማምጣት ሞክረናል። እኔም ሁሉንም የፕሪምየር ሊግ ውድድር ስመለከት ነበር። ይህ ደግሞ የተጫዋች ምርጫችን ከሌላ ጊዜው የተሻለ እንዲሆን አድርጎታል። ከጠራኋቸው 26 ተጫዋቾች ውስጥ አስራ አንዱ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የመጡ ናቸው። አራቱ ብቻ ደግሞ ልምምድ ያላቸው ናቸው። ስብስቡ ውስጥም ምንም ልምድ የሌላቸው ተጫዋቾችን አካተናል።

“ይህ የተጫዋቾች ምርጫ ከበፊቱ በጣም ተለውጧል። ጥሩ ጥሩ ወጣት ተጫዋቾች እየመጡ እንደሆነ ይታወቃል። ጥሩዎች ሲመጡ ደግሞ ወደ እነርሱ መዞር ያስፈልጋል። በፊት በፊት እኔ የምታማው ለወጣቶች ዕድል አይሰጥም በሚል ነው። ይህንን ደግሞ ቆም ብዬ ተመልክቻለሁ። በሰራሁት ነገርም ተፀፅቼ ንሰሀ ገብቻለሁ። ስለዚህ ጊዜው የወጣቶች እና የታዳጊዎች ነው። እነሱ ላይ መስራት አለብን በሚል ወደ ስራ ገብተናል።

“26 ተጫዋቾችን ስመርጥ የአካል ብቃት፣ የቴክኒክ አቅም፣ የታክቲክ አረዳድ እና የስነ-ልቦና ዝግጁነትን በዋናነት ተመልክቻለሁ። ተጫዋቾቹም በካፍ የልህቀት ማዕከል በመቀመጥ ልምምዳቸውን እየሰሩ ይገኛሉ። በአሁኑ ሰዓትም ከመረጥኳቸው 26 ተጫዋቾች አንዷ ብቻ ነች ጉዳት ያስተናገደችው።” የሚል ሀሳባቸውን ያስተላለፉት አሠልጣኙ በመቀጠል በመጀመሪያ ቡድኑን ሲረከቡ ፈፅሜዋለሁ ያሉትን ስህተት መግለፅ ጀምረዋል።

“የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ያለፉትን ዘጠኝ ዓመታት ውጤታማ አልነበረም። ለዚህም ደግሞ አንደኛው ተጠያቂ እኔ ነኝ። ምክንያቱም ቅድም እንዳልኩት ለወጣቶች ቦታ ባለመስጠቴ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ ቡድኑን ከአሠልጣኝ ሰላም ዘርዓይ ተረክቤ ለሴካፋ ሳዘጋጅ ስህተቶችን ፈፅሜያለሁ። እርሱም እርሷ እየገነባች የነበረውን ነገር ብዙ ሳልነካካ ማስቀጠል ነበረብኝ። እንደ አዲስ ቡድን ለመገንባት መጣሬ ግን ስህተት ነበር። ይህ እንግዲህ አልፏል። አሁን ላይ ከስህተታችን ተምረናል።” አሠልጣኙ ስለ ደቡብ ሱዳኑ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ሲናገሩም ቡድኑን አድንቀው ጨዋታዎቹን 90% ወጣቶቸን ለመፈተሽ እንደሚጠቀሙበት አስረድተዋል።

አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ዘለግ ላለ ደቂቃ ገለፃቸውን ካደረጉ በኋላ የቡድኑ አምበል ሎዛ አበራ ተከታዩን ንግግር አስከትላለች።

“በቅድሚያ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ማመስገን እፈልጋለሁ። ምክንያቱም ከዚህ ቀደም የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን አናገኝም ነበር። አሁን ግን ይህ ተቀርፎ ጨዋታ ልናደርግ ነው። ይህ ደግሞ ቡድኑ ምን ላይ እንዳለ እንዲያይ ይረዳል። ከዚህ በተጨማሪም እንድናርፍበት የሆነው ቦታም ጥሩ ነው።

“በካፍ የልዕቀት ማዕከል ከተሰባሰብንበት ጊዜ ጀምሮ ጥሩ ቆይታ እያደረግን ነው። ልምምዶቻችንም ጥሩዎች ናቸው። ሁሉም ተጫዋቾች ደግሞ ከውድድር ስለመጡ ብዙም አልተቸገሩም። የነገ እና የማክሰኞውም የአቋም መፈተሻ ጨዋታ እጅግ ይጠቅመናል። ከፊታችን ለሚጠብቁን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ እና የሴካፋ ውድድር ላይ ትልቅ ስንቅ ይሆነናል። ጨዋታውን የአቋም መፈተሻ ጨዋታም ነው ብለን ደግሞ አልናቅነውም። በአጠቃላይ እንደ ግልም ሆነ እንደ ቡድን ጥሩ ስሜት ላይ እንገኛለን። እኔም ጎሎችን አስቆጥሬ ሀገሬን ለመጥቀም እጥራለሁ። የሀገራችንን መለያም ስለምንለብስ ሁላችንም በትልቅ ተነሳሽነት እየሰራን ነው። ሀገርን መወከል ትልቅ ነገር እንደሆነም ሁሉም ተጫዋች ያውቃል።”

አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው እና አምበሏ ሎዛ አበራ ሀሳባቸውን ካሰሙ በኋላ ሰሞነኛውን የረሂማ ዘርጋውን አለመመረጥ ተከትሎ ከጋዜጠኞች ለተነሳው ጥያቄ የተሰጠውን ዝርዝር ምላሽ ከቆይታ በኋላ ይዘን የምንመለስ ይሆናል።

*የኢትዮጵያ እና የደቡብ ሱዳን የመጀመሪያ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ነገ ምሽት 12:30 በአዲስ አበባ ስታዲየም ይደረጋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ