ቅድመ ዳሰሳ | ድሬዳዋ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

ነገ 10 ሰዓት የሚደረገውን የድሬዳዋ እና ድቻን ጨዋታ እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።

ማሸነፍ የሌለባቸው ስድስት የጨዋታ ሳምንታትን አሳልፈው የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በከተማቸው ያደረጉትን የመጀመሪያ ጨዋታ በመርታት ከድል ጋር ታርቀዋል። ይህንን የአሸናፊነት መንፈስም ከአንድ ጨዋታ ለማዘለል እና ከወራጅ ቀጠናው በአስተማማኝ ሁኔታ ለመራቅ የነገውን ጨዋታ ይጠባበቃሉ። ከሰባት ተከታታይ ያለመሸነፍ ግስጋሴ በኋላ በ17ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር በፋሲል ከነማ የተረቱት ወላይታ ድቻዎች ደግሞ የነበሩበትን የአሸናፊነት መንገድ ዳግም ለማግኘት እና ከበላያቸው ያሉትን ክለቦች በነጥብ ለመቅረብ ድልን እያለሙ ለጨዋታው ይቀርባሉ።

በአሠልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ እየተመሩ በጥሩ የእንቅስቃሴ መሻሻል ላይ ያሉ የሚመስሉት ድሬዳዋዎች መሻሻላቸውን በውጤት ማሳጀም ጀምረዋል። በተለይም ቀስ በቀስ እየተዋሀደ የመጣው ቡድኑ ግቦችን የማስተናገድ ችግሩን እየቀረፈ ይመስላል። ከምንም በላይ ደግሞ ጅማን ሲረታ የታየው የቡድኑ የአማካይ ክፍል ጥምረት በጎ ነገሮችን ሲያስመለክት ነበር። ከዚህም መነሻነት ሞክሼዎቹ ዳንኤሎች (ዳንኤል ደምሴ እና ዳንኤል ኃይሉ) ቡድኑ ሲከላከልም ሆነ ሲያጠቃ ያላቸው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ስለሆነ በነገውም ጨዋታ የሁለቱ ብቃት ልዩነት እንደሚፈጥር ይጠበቃል። በተጨማሪም የጁንያስ ናንጄቦ ከተከላካይ ጀርባ ሩጫዎች ለምስራቁ ክለብ አዎንታዊ ነገሮችን ሊያስገኙ ይችላል።

በመቀመጫ ከተማቸው ሁለተኛ ጨዋታቸውን የሚያደርጉት ድሬዳዋዎች በስብስባቸው ውስጥ መጥፎ የጉዳት እና የቅጣት ዜና አለ። እርሱም ፍጥነቱን ተጠቅሞ ተጋጣሚን የሚያስጨንቀው አስቻለው ግርማ በጉዳት እንዲሁም ያለፉትን ጨዋታዎች እጅግ የተሻሻለው ፍሬዘር ካሳን በአምስት ቢጫ ካርድ ምክንያት የሚያጣ ይሆናል። ከዚህም መነሻነት ስብስቡ ፊት እና ኋላ ላይ መሳሳት እንዳያስመለክት ያሰጋል።

አሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራው የአሠልጣኝነት መንበሩን ከተረከቡ በኋላ እጅግ የተሻሻለው ወላይታ ድቻ ምንም እንኳን በመጨረሻው ጨዋታ በፋሲል ከነማ ቢረታም በሜዳ ላይ ያሳየው ብቃት አድናቆት የሚያስችረው ነበር። ከምንም በላይ 7 ቋሚ ተሰላፉ ተጫዋቾችን በህመም ምክንያት አቶ የነበረው ቡድኑ ሳይጠበቅ የሊጉን መሪ ሲፈትን ተስተውሏል። ከዚህም መነሻነት በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ረገድ ስል የሆነው ድቻ ነገም በሚታወቅበት ጥንቃቄ የታከለበት አጨዋወት ለተጋጣሚው ቡድን (ድሬዳዋ) ፈተናን ሊሰጥ እንደሚችል ይታሰባል።

በቡድኑ ውስጥ የተሰማው መልካም ዜና በፋሲሉ ጨዋታ ያልተሰለፉት ነፃነት ገብረመድህን፣ ጋቶች ፓኖም፣ በረከት ወልዴ እና አንተነህ ጉግሳ ከህመማቸው ማገገማቸው ነው። ይህም ደግሞ ለቡድኑ አንዳች ጥንካሬ እንደሚያላብሰው ያሳብቃል። በአንፃሩ ግን የሳሳ የአጥቂ አማራጭ ያለው ስብስሱ ዲዲዬ ለብሪን በህመም ማጣቱ ፊት ላይ አስፈሪ እንዳይሆን ሊያደርገው ይችላል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– የሁለቱ ቡድኖች የግንኙነት ታሪክ በድሬዳዋ የበላይነት የተያዘበት ነው። እስካሁን በሊጉ ለ9 ጊዜያት ሲገናኙ ብርቱካናማዎቹ አምስት ጊዜ ባለድል መሆን ሲችሉ ቀሪዎቹ አራት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ነበሩ ፤ ወላይታ ድቻ ግን እስካሁን ድል ማስመዝገብ አልቻለም። በጨዋታዎቹ ድሬ 10 ፤ ድቻ 4 ጎሎችንም አስቆጥረዋል። 

* ወቅታዊው የኮቪድ ወረርሺኝ በቡድኖቹ የስብስብ ምርጫ ላይ እያሳደረ ካለው ተለዋዋጭነት አንፃር ግምታዊ አሰላለፍ ለማውጣት አዳጋች በመሆኑ የወትሮው የአሰላለፍ ትንበያችን በዳሰሳው ያልተካተተ መሆኑን እንገልፃለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ