ሪፖርት | ቡርትካናማዎቹ ከወራጅ ቀጠናው ፈቅ ያሉበትን ውጤት አግኝተዋል

ለወራጅ ቀጠናው ፍልሚያ እጅግ ወሳኝ የሆነው የድሬዳዋ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ በድሬዳዋ አንድ ለምንም አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል።

የድሬዳዋ ከተማው አሠልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ነጥብ ሲጋሩ ከተጠቀመው ቋሚ አሰላለፍ ሦስት ተጫዋቾችን ለውጠዋል። በዚህም ዘነበ ከበደ፣ ያሬድ ዘውድነህ እና ኢታሙና ኬይሙኒን በማሳረፍ ዐወት ገብረሚካኤል፣ በረከት ሳሙኤል እና ጁኒያስ ናንጄቦ ወደ ቋሚነት መልሰው ጨዋታውን ጀምረዋል። በሲዳማ ቡና በኩል ደግሞ አሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በሊጉ መሪ ከተረቱበት ጨዋታ ሁለት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም የአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት ያለበት ብርሀኑ አሻሞን በያሬድ ከበደ እንዲሁም የግብ ዘቡ ፍቅሩ ወዴሳን በፋቢያን ፋርኖሌ በመተካት ለጨዋታው ቀርበዋል።

መመጣጠን የነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ ደቂቃዎች ጨዋታ እስከ 10ኛው ደቂቃ ድረስ ምንም ሙከራ አላስተናገደም ነበር። በ10ኛው ደቂቃም ሱራፌል ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘው የቅጣት ምት ከርቀት ሲሻማ ያገኘው ጁኒያስ ናንጄቦ ጥሩ ጥቃት ፈፅሞ ነበር። በአብዛኛው የሚያገኟቸውም ኳሶች በረጅሙ በቁመት ዘለግ ላሉት አጥቂዎቻቸው መጣልን ያዘወተሩት ሲዳማዎች በራሳቸው በኩል የመጀመሪያ ለግብ የቀረበ ሙከራ ያደረጉት በ14ኛው ደቂቃ ነው። በዚህ ደቂቃም ማማዱ ሲዲቤ ከሳጥን ውጪ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ቢመታውም የግብ ዘቡ ፍሬው ጥቃቱን ተቆጣጥሮታል። ከደቂቃ በኋላ የቅጣት ምት ያገኙት ድሬዎች በበኩላቸው የጨዋታውን ሁለተኛ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ በአምበላቸው በረከት ሳሙኤል አማካኝነት ቢሰነዝሩም ፍቅሩ ወዴሳ ኳሱን መልሶባቸዋል። ይህንን ሙከራ ያደረገው በረከት በ20ኛው ደቂቃም ሲዲቤ በሰራው ጥፋት የተገኘን ሌላ የቅጣት ምት በመጠቀም ቡድኑን መሪ ለማድረግ ጥሮ ነበር።

በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ተሽለው የታዩት ድሬዳዋዎች በፈጣኖቹ አጥቂዎችቸው እንቅስቃሴ ታግዘው የሲዳማን የግብ ክልል መጎብኘት ይዘዋል። በ22ኛው ደቂቃም ሱራፌል ጌታቸው እና ሙኅዲን ሙሳ በፈጠሩት ቅብብል የተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ ተገኝተው ሙኅዲን ሙከራ ቢያደርግም ተጫዋቹ ወደ ጎል የመታው ኳስ ሃይል ባለመኖሩ መረብ ላይ ሳያርፍ ቀርቷል። በ34ኛው ደቂቃ ላይ ግን የቀኝ መስመር ተከላካዩ ዐወት ገብረሚካኤል እጅግ ራቅ ካለ ቦታ ለማሻማት ይሁን በቀጥታ ግብ ለማስቆጠር ባልታወቀ ሁኔታ ወደ ግብ የላከው ኳስ መረብ ላይ ለማረፍ ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም ኳስን የግቡ አግዳሚ መልሶታል።

የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አስራ አምስት ሰከንዶች ሲቀሩት ሲዳማ የግብ ክልል የደረሱት ድሬዳዋዎች ኳስ በእጅ በመነካቱ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። ሱራፌል ኳስ አሳልፋለሁ ሲል ሰንደይ ሙቱኩ በእጅ በመንካቱ ምክንያት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምትም ሙኅዲን ሙሳ ወደ ግብነት ቀይሮታል። አጋማሹም በማብቂያው ላይ በተቆጠረ ብቸኛ ጎል ፍፃሜውን አግኝቶ ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ጨዋታው ግማሽ ሰዓት ካስቆጠረ በኋላ መጠነኛ እድገት እያሳዩ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች ምንም እንኳን በአጋማሹ መገባደጃ ላይ ግብ ቢያስተናግዱም በሁለተኛው አጋማሽም የነበራቸውን ብልጫ በማስቀጠል ወደ ጨዋታው ለመመለስ ሲታትሩ ነበር። ድሬዳዋዎች በበኩላቸው በመጀመሪያው አጋማሽ የነበራቸውን ፍጥነት ትንሽ ገታ አድርገው በእጃቸው የገባውን ሦስት ነጥብ ለማስጠበቅ ሲንቀሳቀሱ ታይቷል። ይህ ቢሆንም ግን ከመልሶ ማጥቃት እና ከቆሙ ኳሶች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ሲሹ ታይቷል። በ48ኛው ደቂቃም ናንጄቦ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን የቅጣት ምት ሱራፌል በመጠቀም የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ለማድረግ ሞክሮ ነበር።

የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ማድረግ የተሳናቸው ሲዳማዎች የማጥቃት ሀይላቸውን ለማጠናከር ለውጦችን ቢያደርጉም እስከ 80ኛው ደቂቃ ድረስ ፍሬውን የሚፈትን ኳስ ወደ ግብ አላኩም። ከዚህ ደቂቃ በኋላ ግን ጥሩ ጥሩ ኳሶችን ወደ ግብነት ለመቀየር ሞክረዋል። በመጀመሪያም በ80ኛው ደቂቃ ግዙፉ የመሐል አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢ ከሳጥን ውጪ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ በመምታት ቡድኑን አቻ ለማድረግ ጥሯል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ተመሳሳይ ኳስ በተቃራኒ መስመር ያገኘው ኦኪኪ ያገኘውን ኳስ በጥሩ ሁኔታ ወደ ግብ ቢልከውም አልቀመስ ያለው ፍሬው ኳሱን ወደ ውጪ አውጥቶበታል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩትም ቡድኑ የቅጣት ምት አግኝቶ የነበረ ሲሆን የተሻማውንም ኳስ የቡድኑ አምበል ፈቱዲን ጀማል በግንባሩ ለማስቆጠር ጥሮ መክኖበታል። በቀሪዎቹ ደቂቃዎችም ሲዳማዎች ከጨዋታው አንድ ነጥብ ይዘው የሚወጡበትን አጋጣሚ ለመፍጠር ሲፍጨረጨሩ ቢታይም የድሬዳዋን መረብ ማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በድሬዳዋ አንድ ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ሙሉ ሦስት ነጥብ ያገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች አጠቃላይ ነጥባቸውን 20 በማድረስ ከአስጊው ቀጠና በመጠኑም ቢሆን ራቅ ብለዋል። በጨዋታው ሦስት ነጥብ ያስረከቡት ሲዳማ ቡናዎች ደግሞ ሁለተኛ ተከታታይ ሽንፈታቸውን በማስተናገዳቸው በ17 ነጥቦች ያሉበት 12ኛ ደረጃ ላይ ፀንተው እንዲቀመጡ ሆኗል።


© ሶከር ኢትዮጵያ