በሉሲዎቹ ፍፁም የበላይነት እየተከናወነ የነበረው ጨዋታ በመብራት ችግር ምክንያት ተቋርጧል

በአሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በአቋም መፈተሻ ጨዋታ የደቡብ ሱዳን አቻውን ገጥሞ እስከ 81ኛው ደቂቃ ድረስ ዘጠኝ ግቦችን አስቆጥሯል።

ይጀመራል ተብሎ ከተነገረበት ሰዓት ሠላሳ ደቂቃዎችን ዘግይቶ የተጀመረው ይህ ጨዋታ በቀዝቃዛማው የአዲስ አበባ ስታዲየም አየር ታጅቦ መደረግ ቀጥሏል። የሉሲዎቹ ዋና አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛውም ታሪኳ በርገዳ፣ ሀሳቤ ሙሳ፣ ትዝታ ኃይለሚካኤል፣ ብዙአየሁ ታደሰ፣ እፀገነት ብዙነህ፣ መሳይ ተመስገን፣ ሰናይት ቦጋለ፣ አረጋሽ ካልሳ፣ ሴናፍ ዋቁማ እና ዮርዳኖስ ሙዕዝን በ4-3-3 የተጫዋች አደራደር ቅርፅ በማሰለፍ ለጨዋታው ቀርበዋል።

የጨዋታውን የሃይል ሚዛን ወደ ራሳቸው በማድረግ ጨዋታውን የጀመሩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ገና በጅምሩ ባስቆጠሯቸው ሁለት ጎሎች መምራት ጀምረዋል። በዚህም በ7ኛው ደቂቃ ሎዛ አበራ ወደ ግብ የመታችውን ኳስ ካላድ ሀሰን ስትመልሰው በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረችው ሴናፍ ዋቁማ ኳሱን ወደ ግብነት ቀይራዋለች። ይህ ፈጣን ጎል ያላረካቸው የሉሲዎቹ ተጫዋቾች ከደቂቃ በኋላም ተጨማሪ ጎል አስቆጥረዋል። በዚህ ደቂቃም የግራ መስመር ተከላካዩዋ ብዙአየሁ ታደሰ ከመስመር ያሻገረችውን ኳስ የቡድኑ አምበል ሎዛ አበራ ከመረብ ጋር አዋህዳዋለች።

ገና በጊዜ ፈተናዎች የበዛባቸው ደቡብ ሱዳኖች በራሳቸው የግብ ክልል ተወስነው ለመከላከል ቢፈልጉም ፈጣኖቹን የሉሲዎቹ ተጫዋቾች መቆጣጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በ18ኛው ደቂቃም ሎዛ አበራ ከአረጋሽ ካልሳ የተቀበለችውን ኳስ ወደ ግብነት በመቀየሯ ሦስተኛ ጎል አስተናግደዋል። በተቃራኒው ጨዋታው እጅግ ቀሏቸው ሲጫወቱ የታዩት የአሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ተጫዋቾች በ20ኛው ደቂቃ መሪነታቸውን ወደ አራት ከፍ የሚያደርጉበትን ዕድል አገኝተዋል። በዚህም ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ ለማውጣት ስትጥር የነበረችው የደቡብ ሱዳኗ የመሐል ተከላካይ ሞዴስቶ አሲንዞ እራሷ ላይ ግብ አስቆጥራለች። ሙሉ ለሙሉ ማጥቃቱ ላይ ትኩረታቸውን አድርገው ጨዋታውን የቀጠሉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች በ28ኛው ደቂቃ አረጋሽ እና ሴናፍ በሞከሯቸው ተከታታይ ኳሶች በድጋሜ ወደ ግብ ቀርበው ነበር።

ጥቃቶችን በመመከት ተጠምደው ያመሹት ደቡብ ሱዳኖች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የግብ ክልል የደረሱት በ33ኛው ደቂቃ ነው። በዚህ ደቂቃም ቡድን የቅጣት ምት አግኝቶ በኢስተር ሉዊስ አማካኝነት ወደ ግብነት ለመቀየር ታትሯል። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም በድጋሜ በፈጣን ሽግግሮች ተጋጣሚ የግብ ክልል ደርሰው በግሎሪያ ፍራንሲስ አማካኝነት ጥቃት ፈፅመው ነበር። ያስቆጠሯቸው አራት ጎሎች ያልበቃቸው ሉሲዎች የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አምስስ ደቂቃዎች ሲቀሩት አረጋሽ ካልሳ ከሳጥን ውጪ በመምታት ባስቆጠረችው ድንቅ ጎል አምስት ለምንም መምራት ችለዋል። አጋማሹም ተጨማሪ የግብ ሙከራዎች ሳይስተናገዱበት በሉሲዎቹ መሪነት ተጠናቋል።

የመጀመሪያውን አጋማሽን አጠናቀው ወደ መልበሻ ክፍል ያመሩት የሁለቱ ቡድን ተጫዋቾች የሁለተኛውን አጋማሽ ለመጀመር ወደ ሜዳ ሲገቡ የስታዲየሙ ፓውዛ ጠፍቶ ነበር። ፓውዛውም እስኪበራ ድረስ ለአምስት ደቂቃዎች ያክል ሜዳ ላይ ለመቆየት ተገደው ነበር። መብራቱ መጥቶ አጋማሹ በተጀመረ በስድስተኛው ደቂቃም ጎል ማምረታቸውን የቀጠሉት ሉሲዎቹ ስድስተኛ ጎል አስቆጥረዋል። በዚህም የቡድኑን አምስተኛ ጎል በሚገር ሁኔታ ያስቆጠረችው አረጋሽ ከዮርዳኖስ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብላ ያገኘችውን የመጨረሻ ኳስ መረብ ላይ አኑራለች። አረጋሽ ስድስተኛውን ጎል ካስቆጠረች በኋላ ግን የስታዲየሙ ፓውዛ በድጋሜ ጠፍቷል። ከዚህም መነሻነት የጠፉት መብራቶች እስኪበሩ አስራ ስድስት ደቂቃዎች ፈጅተዋል።

የስታዲየሙ መብራቶች ከበሩ በኋላ የቀጠለው ጨዋታው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የጨዋታ የበላይ አድርጎ ነበር። በዚህም ቡድኑ በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ሁለት ጎሎችን አስቆጥሯል። በቅድሚያም በ67ኛው ደቂቃ ሎዛ ከሰናይት የተቀለችውን ኳስ ወደ ግብነት ቀይራለች። ይህንን ጎል ያስቆጠረችው ሎዛ በድጋሜ በ69ኛው ደቂቃ ዮርዳኖስ ያመቻችላትን ኳስ ተጠቅማ የቡድኑን ስምንተኛ ጎል አስቆጥራለች። ጨዋታው ሊጠናቀቅ አስር ደቂቃዎች ሲቀሩትም ሎዛ አበራ የቡድኗን ዘጠነኛ የራሷን ደግሞ አምስተኛ ጎል አስቆጥራለች። ጨዋታው 81ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግን የስታዲየሙ ፓውዛ ለሦስተኛ ጊዜ ጠፍቷል። በዚህም ጨዋታው እስከ 81ኛው ደቂቃ ድረስ በተመዘገበው ውጤት እንዲገባደድ እና ቀሪዎቹ ዘጠኝ ደቂቃዎች ወደ ነገ እንዲዘዋወሩ ሆኗል። ቀሪዎቹ ዘጠኝ ደቂቃዎችም ነገ አራት ሰዓት እንደሚከናወኑ ታውቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ