ከኮሮና ጋር በተያያዘ መነጋገሪያ ነገሮች የነበሩበት የወላይታ ድቻ እና ሀዋሳ ከተማ ጨዋታ አምስት ግቦች ተስተናግደውበት ሀዋሳን ባለ ድል አድርጓል።
ኮቪድ-19 ያጠላበት የዛሬ ምሽቱ ጨዋታ ለሁለቱ ቡድን አሠልጣኞች ከባድ ፈተናን ይዞ የመጣ ነበር። ተጫዋቾች በኮቪድ መጠቃታቸውን ተከትሎም ወላይታ ድቻ 11 ሀዋሳ ከተማ ደግሞ 13 ተጫዋቾችን ብቻ ይዘው ወደ ሜዳ የመግባት ግዴታ ተጥሎባቸዋል ። በዚህም የወላይታ ድቻው አሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ግብ ጠባቂዎቻቸውን የፊት አጥቂ በማድረግ እንዲሁም ያለ ምንም ተቀያሪ ተጫዋች ጨዋታውን ጀምረዋል። የሀዋሳ ከተማው አሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረትም ከተጋጣሚያቸው በተሻለ ሁለት ተጫዋቾችን በተጠባባቂነት በመያዝ ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ቀዝቀዝ ባሉ እንቅስቃሴዎች የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያ ደቂቃዎቹ ላይ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማስተናገድ ተስኖት ነበር። በአንፃሩ ግን ሀዋሳ ከተማ በተሻለ ኳስን በመቆጣጠር ሲጫወት ነበር። በተቃራኒው ወላይታ ድቻ ደግሞ አብዛኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በራሱ የግብ ክልል በማድረግ ሲጫወት ተስተውሏል። ይህ ቢሆንም ግን ጨዋታው ገና አምስት ደቂቃዎች ሳያሳልፍ ቡድኑ ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ ነበር። በዚህም አብነት ይስሀቅ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ ያገኘውን ኳስ ለቸርነት በግንባሩ አመቻችቶለት ቸርነት ወደ ግብ ቢመታውም ሜንሳህ ሶሆሆ አውጥቶበራል። የነበራቸውን የጨዋታ የበላይነት በጎል ለማጀብ የፈለጉት ሀዋሳዎች በ17ኛው ደቂቃ መሪ የሆኑበትን ጎል አግኝተዋል። በዚህ ደቂቃም ቸርነት አውሽ ወደ ቀኝ ባዘነበለ በኩል ያገኘውን ኳስ የግል ጥረቱን አክሎበት ከሳጥኑ ጫፍ ሆኖ ወደ ግብ በመምታት ግብ አስቆጥሯል።
ግቡን ካስተናገዱ በኋላ ጥሩ ደቂቃዎችን እንደ ቡድን ያሳለፉት የአሠልጣኝ ዘላለም ተጫዋቾች በሦስት ደቂቃ ውስጥ ሁለት ጎሎችን አከታትለው በማስቆጠር ከመመራት ወደ መምራት ተሸጋግረዋል። በቅድሚያም በ21ኛው ደቂቃ እድሪስ ሰዒድ ከቀኝ መስመር መሬት ለመሬት የተመቻቸለትን ኳስ በመጠቀም የአቻነት ጎል አስቆጥሯል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ቡድኑ ከፈጣኑ ቸርነት የተነሳ እና ተከላካዩ ላውረንስ ራሱ ላይ ሊያስቆጥረው በተቃረበ ኳስ ግብ ሊያገኝ ነበር። ይህ ሙከራ ከተደረገ ከጥቂት ሰከንዶች በኋላ ዳግም በቀኝ መስመር ሀዋሳ የግብ ክልል የደረሰው ቸርነት ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ ላውረንስ በግንባሩ ሲገጨው በነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ደጉ አግኝቶት ቡድኑን መሪ ያደረገ ጎል አስቆጥሯል።
በሦስት ደቂቃ በተቆጠረባቸው ጎል መመራት የጀመሩት ሀዋሳዎች ዳግም ወደ ጨዋታው የሚመለሱበትን ግብ ፍለጋ መታተር ይዘዋል። በዚህም ግቡ ከተቆጠረ ከደቂቃ በኋላ ሄኖክ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ብሩክ በግንባሩ ወደ ግብ ሞክሮ ነበር። በ36ኛው ደቂቃ ግን ቡድኑ አቻ የሆነበትን ኳስ ከመረብ አገናኝቷል። በዚህም አለልኝ ለደስታ የሰጠውን ኳስ ደስታ ሲያሻማው የድቻ ተከላካዮችን ጨርፈውት ዳንኤል አጄይ መረብ ላይ አርፏል። የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃዎችም ፍጥነቱን ተጠቅሞ ወደ ድቻ የግብ ክልል የደረሰው ብሩክ ተጨማሪ ጎል ለማከል ቢጥርም የግቡ ቋሚ ውጥኑን ሳያሰምርለት ቀርቷል። አጋማሹም 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተገባዷል።
መመጣጠን የታየበት የሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች እስከ 54ኛው ደቂቃ ድረስ ሙከራ ሳይኖረው ቀጥሏል። በ54ኛው ደቂቃ ግን ሀዋሳዎች ዳግም መሪ የሚሆኑበትን ጎል ለማግኘት ጥረዋል። በዚህም ወደ ግብ የተመታ ኳስ ተከላካዮች ሲያጨናግፉት እግሩ ላይ ያገኘው አለልኝ ጥሩ ኳስ መረብ ላይ ለማሳረፍ ጥሮ አጄይ አድኖበታል። ይህንን ሙከራ ያደረጉት ሀዋሳዎች በድጋሜም ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ግብ ፍለጋቸውን ቀጥለዋል። በ59ኛው ደቂቃም የድቻን ተጫዋቾች ተጭነው ያገኙትን ኳስ ከርቀት በዘላለም አማካኝነት ወደ ግብ መትተውት ነበር። በተቃራኒው የሀዋሳን ጥቃት መመከት ላይ ተጠምደው መጫወት የቀጠሉት ድቻዎች በ61ኛው ደቂቃ በሚገርም የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ ሀዋሳን አስደንግጠዋል። በዚህም ፍጥነቱን ተጠቅሞ ተጋጣሚ ሳጥን የደረሰው ቸርነት ጥሩ ኳስ ወደ ግብ ልኮ ለጥቂት ወጥቶበታል።
ቀጣዮቹ የጨዋታው ደቂቃዎች እጅግ በተቀዛቀዘ ሁነት ውስጥ በመደረግ ሙከራዎችን ሳያስመለክቱም አልፈዋል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት ግን ቡድኖቹ ግብ ለማስቆጠር ሲፍጨረጨሩ ተስተውሏል። በተለይም ሀዋሳ ከተማዎች ከጨዋታው ሦስት ነጥብ ይዘው ለመውጣት ሲታትሩ ታይቷል። በዚህም በ85ኛው ደቂቃ ዳንኤል ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ በመጠቀም ብሩክ ግብ ለማስቆጠር ጥሮ ነበር። ጨዋታው ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ግን የዘላለም ኢሳያስ ጎል ሀዋሳን አሸናፊ አድርጓል። በዚህ ደቂቃም ያገኙትን መዓዘን በቶሎ የጀመሩት ሀዋሳዎች ተቀባብለው ወደ ሳጥን ያሻገሩት ኳስ ተከላካዮች ሲመልሱት ያገኘው ዘላለም ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። መሪነታቸውን በመጨረሻው ደቂቃ ያገኙት ሀዋሳዎች ጨዋታው ተጠናቆ በተጨመረው ሦስት ደቂቃ አራተኛ ጎል ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት የግቡ ቋሚ መልሶባቸዋል። ጨዋታውም በሀዋሳ ከተማ ሦስት ለሁለት አሸናፊነት ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎ በጨዋታው የተረቱት ወላይታ ድቻዎች በ24 ነጥቦች ስድስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ በጨዋታው ሦስት ነጥብ ያገኙት ሀዋሳዎች ደግሞ ነጥባቸውን ከድቻ ጋር በማስተካከል ነገር ግን ተጋጣሚ ላይ ባስቆጠሩት ግብ ተበልጠው ባሉበት ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ