ሪፖርት | ሲዳማ ቡና ተከታታይ ድሉን አሳክቷል

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ምሽት ላይ ቀጥሎ ሲዳማ ቡና በዳዊት ተፈራ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል 1-0 አሸንፎ ከወራጅ ቀጠናው ወጥቷል።

ወልቂጤ ከተማ በባህር ዳር ከተሸነፈበት የ17ኛው ሳምንት ጨዋታ አምስት ለውጦችን በማድረግ በዳግም ንጉሤ፣ ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ፣ አብዱልከሪም ወርቁ፣ እስራኤል እሸቱ እና አህመድ ሁሴን ምትክ መሐመድ ሻፊ፣ በኃይሉ ተሻገር፣ ጂብሪል ናስር፣ አቡበከር ሳኒ እና ሄኖክ አየለ ወደሜዳ ሲገቡ ሲዳማዎች ከአዳማው ድል አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ የወጣው ሰንደይ ሙቱኩን በፈቱዲን ጀማል ተክተዋል።

በዝናብ ምክንያት ሜዳው ለመጫወት አስቸጋሪ ሆኖ ባመሸበት ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ ተመጣጣኝ የጨዋታ እንቅስቃሴ የታየበት ቢሆንም ሲዳማ ቡናዎች ወደፊት በሚያመሩበት ወቅት የተሻለ አስፈሪነት ታይቶባቸዋል። በዚህም በጥቂት አጋጣሚዎች ወደ ተጋጣሚ የጎል ክልል አምርተው አደጋ መፍጠር ችለዋል። በተለይ በአስረኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት በረጅሙ የተላከውን ኳስ ፈቱዲን ጀማል ከመሬት ጋር አጋጭቶ ሞክሮ በግቡ አናት የወጣበት አጋጣሚ የሚጠቀስ ነበር።

ሄኖክ አየለ በመጀመርያው ደቂቃ ከሳጥኑ ጠርዝ ያገኘውን ኳስ መትቶ ፋቢየን ፌርኖሌ በቀላሉ በተያዘበት ሙከራ ወደፊት ያመሩት ወልቂጤዎች በዚህ አጋማሽ በተሳካ ሁኔታ ወደፊት ሲጓዙ አልስተዋሉም።

ጨዋታው ቀጥሎ በ35ኛው ደቂቃ ኳስ በሚይዝባቸው አጋጣሚዎች የወልቂጤ ተከላካዮችን ሲፈተን የነበረው ኦኪኪ አፎላቢ ከዳዊት ተፈራ የተቀበለውን ኳስ ተቆጣጥሮ ለማለፍ ሲሞክር በቶማስ ስምረቱ ተጎትቶ በመውደቁ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ዳዊት በቀላሉ አስቆጥሮ ሲዳማን መሪ ማድረግ ችሏል።

ከጎሉ በኋላ ወልቂጤዎች በፍጥነት ምላሽ ለመስጠት ጥሩ ዕድል ማግኘት ቢችሉም ሄኖክ አየለ ከጎሉ አቅራቢያ ያገኘውን ኳስ በአግባቡ ባለመምታቱ የፌርኖሌ ሲሳይ ሆናለች። የመጀመርያው አጋማሽም በሲዳማ መሪነት ተጠናቋል።

ወልቂጤዎች ወደ ግራ ካመዘነ ቦታ ያገኙትን ቅጣት ምት ፍሬው ሰለሞን በቀጥታ መትቶ በተከላካዮች ተጨራርፎ በወጣ ሙከራ የጀመረው ሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታውን መልክ የለወጠ ክስተት አስተናግዷል። በ50ኛው ደቂቃ የመሐል ዳኛው ብርሀኑ መኩርያ ለማዕዘን ምት ሲሻሙ የነበሩት ጊት ጋት እና ቶማስ ስምረቱ የነበረውን ፍትጊያ ተከትሎ ቢጫ ካርድ ያሳዩ ሲሆን ቶማስ በፍፁም ቅጣት ምቱ ውሳኔ ወቅት ቢጫ ካርድ ተመልክቶ የነበረ ቢሆንም ዳኛው ዘንግተውት ጨዋታው በዚሁ ከቀጠለ በኋላ ከአራተኛው ዳኛ አማኑኤል ኃይለሥላሴ በደረሳቸው መረጃ በሁለተኛ ቢጫ ከሜዳ አስወጥተውታል። ከቢጫው መረሳት በተጓዳኝ ቶማስ ቢጫ ካርድ የተመለከተበት ቅፅበት ግልፅ ያልነበረ መሆኑ የጨዋታው አነጋጋሪ ክስተት ነበር።

ከቀይ ካርዱ በኋላ የተከላካይ መስመር ተጫዋች ቀይረው ሳያስገቡ ጨዋታውን የቀጠሉት ወልቂጤዎች በተሻለ ሁኔታ መንቀሳቀስ ቢችሉም በጠሩ የጎል ዕድሎች ማጀብ አልቻሉም። 70ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ከአሜ የተላከውን ኳስ መትቶ ለጥቂት ወደላይ የወጣበት እና ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ በጥሩ ፍሰት ወደፊት የሄደውን ኳስ ከቀኝ የሳጥኑ ክፍል ሄኖክ አግኝቶት ወደ ላይ የሰደደው ኳስ ብቻ ተጠቃሽ የጎል ዕድሎች ነበሩ።

ኦኪኪ በመልሶ ማጥቃት አክርሮ መትቶ ጀማል ከያዘበት ሙከራ ውጪ እምብዛም ወደፊት ያልሄዱትና ሙከራዎች ያላደረጉት ሲዳማ ቡናዎች በጥንቃቄ በመጫወት ራሳቸው ላይ አደጋ ሳይጋብዙ ጨዋታውን አንድ ለምንም ማሸነፍ ችለዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ሲዳማ ቡና ከሁለት ተከታታይ ድል በኋላ ነጥቡን 17 አድርሶ ወደ አስረኛ ደረጃ ከፍ ሲል በወቅታዊ የውጤት ቀውስ ላይ የሚገነው ወልቂጤ ከተማ በዛው ሃያ ነጥብ ላይ ቆሞ ወደ ወራጅ ቀጠናው እየተጠጋ ይገኛል።


© ሶከር ኢትዮጵያ