ሪፖርት | ሲዳማ ቡና ከተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ወደ ድል ተመልሷል

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 17ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐ ግብር አዳማ ከተማን የገጠመው ሲዳማ ቡና 3-0 በማሸነፍ ከአምስት ተከታታየሰ ሽንፈት በኋላ አገግሟል።

ሲዳማ ቡናዎች ሊጉ ከእረፍት ከመቋረጡ በፊት ከነበረው ስብስብ ፍቅሩ ወዴሳ፣ አበባየሁ ዮሐንስ፣ ፈቱዲን ጀማል፣ ሽመልስ ተገኝ፣ ግርማ በቀለ እና ዮናስ ገረመውን በአዲስ ፈራሚው ፋቢያን ፋርኖሌ እንዲሁም አማኑኤል እንዳለ፣ ሰንደይ ሙቱኩ፣ ጊት ጋትኮች፣ ሀብታሙ ገዛኸኝ እና ማማዱ ሲዲቤ ለውጠዋል። በአዳማ በኩል ደግሞ ዳንኤል ተሾመ ፣ ደሳለኝ ደባሽ ፣ ጀሚል ያዕቅብ ፣ እዮብ ማቲያስ ፣ ኤልያስ አህመድ እና በላይ አባይነህ በአዲስ ፈራሚዎቹ ላሚን ኩማር ፣ ሚሊዮን ሰለሞን ፣ አሊሴ ኦቢሳ ጆናታን፣ ሀብታሙ ወልዴ እንዲሁም ታሪክ ጌትነት እና ደስታ ጊቻሞ ምትክ ተሰልፈዋል።

ከፍ ባለ ተነሳሽነት ጨዋታውን የጀመሩት ሲዳማ ቡናዎች በመጀመርያው አጋማሽ ለተጋጣሚያቸው አስፈሪ ሆነው ታይተዋል። ኦኪኪ አፎላቢ ከቅጣት ምት ሞክሮ ታሪክ ጌትነት በመለሰበት ጥሩ ሙከራ ጥቃት የጀመሩት ሲዳማዎች በዘጠነኛው ደቂቃ መሪ መሆን የቻሉበትን ጎል አስቆጥረዋል። ከመሐል ሜዳ የተላከውን ኳስ ማማዱ ሲዲቤ ተቆጣጥሮ ለመምታት ሲሞክር ሚሊዮን ቢያስጥለውም ከግራ አቅጣጫ በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ኦኪኪ አግኝቶት ወደ ግብነት ቀይሮታል።

ወደ ማጥቃት ወረዳው በተበታተነ መልኩ ሲደርሱ የነበሩት አዳማዎች የሚጠቀስ ጥቃት ለመፍጠር ሃያ ሦስት ደቂቃ ጠብቀዋል። በዚህ ደቂቃ ከታፈሰ ሰርካ የተሻገረውን ኳስ ያሬድ በመቀስ ምት ለመምታት ሞክሮ ቢያመልጠውም አብዲሳ አግኝቶት ሲመታው በተየላካዮች ተጨርፎ ለጥቂት ወደ ውጪ ውጥቷል። በሠላሳኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ አብዲሳ ከኤልያስ የተቀበለውን ኳስ በደረቱ አመቻችቶ ከሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ ቢመታም ፌርኖሌ በግሩም ሁኔታ አውጥቶበታል።

ከሌሎች ጊዜያት በተሻለ በፊት መስመሩ ንቃት የታየባቸው ሲሳዳዎች በ33ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ጎላቸውን አግኝተዋል። ሰንዴይ ሙቱኩ ከአዳማ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያቋረጠውን ኳስ ወደፊት አሻግሮለት ሀብታሙ ገዛኸኝ አምልጦ ወደፊት በመግፋት በታሪክ ጌትነት መረብ ላይ አሳርፎታል።

አዳማ ከተማ በኤልያስ ማሞ የርቀት ሙከራ አድርጎ ፌርኖሌ ካወጣበት እድል ውጪ ለጎል ያቃረበው ተጨማኢ እድል መፍጠር ያልቻለ ሲሆን በተቃራኒው ሲዳማ መሪነቱን ያደላደለበትን ጎል በመጀመርያው አጋማሽ የጭማሪ ደቂቃ አግኝቷል። ወደ ግራ ካመዘነ ቦታ የተገኘውን የቅጣት ምት ማሊያዊው ማማዱ ሲዲቤ ነበር በግሩም ሁኔታ ያስቆጠረው።

ከዕረፍት በኋላ የሚፈልጉትን ያገኙ የሚመስሉት ሲዳማዎች በእርጋታ ውጤቱን አስጠብቀው ለውጣት ሲንቀሳቀሱ አዳማዎች አንፃሩ በአማካይ ክፍሉ የተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ የእንቅስቃሴ ብልጫ ወስደዋል። በተለይም በ66ኛው ደቂቃ የሲዳማው ተከላካይ ሰንዴይ ሙቱኩ በሀብታሙ ወልዴ ላይ በሰራው ጥፋት በሁለተኛ ቢጫ ከሜዳ ከወጣ በኋላ ጫና ፈጥረው ለመጫወት ጥረዋል። በቀይ ካርዱ ውሳኔ ወቅት የተሰጠውን የቅጣት ምት ኤልያስ ማሞ መትቶ የጎሉ ብረት የመለሰበትም አዳማን ወደ ጨዋታው ልትመልስ የምትችል አጋጣሚ ነበረች።

አዳማዎች ምንም እንኳ ብልጫ ቢወስዱም ከክፍት የጨዋታ እንቅስቃሴ የግብ ዕድል ለመፍጠር የተቸገሩ ሲሆን በ76ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ደሳለኝ ደባሽ በግንባሩ ገጭቶ አግዳሚውን ጨርፎ የወጣበት ሌላው የሚጠቀስ ሙከራ ነበር። ሆኖም ጨዋታው በመጀመርያ አጋማሽ ከተቆጠሩት ጎሎች ተጨማሪ ሳይታይ በሲዳማ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ