የአሰልጣኞች አስተያየት | ሲዳማ ቡና 3-0 አዳማ ከተማ

ከ17ኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ በኋላ ተጋጣሚ አሰልጣኞች ከሱፐር ስፖርት ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ – ሲዳማ ቡና

ስለጨዋታው ዋጋ

የዚህ ጨዋታ ዋጋው በጣም ብዙ ነው። ከረጅም ጊዜ በኋላ ነው ወደ አሸናፊነት የተመለስነው። ለቡድናችን የስነ ልቦና የበላይነትን የሚጨምር ነው። ወደ አሸናፊነት መመለስ በራሱ አንድ ትልቅ እርምጃ ነው።

ስለቡድኑ የጨዋታ ቁጥጥር እና ስለአጥቂዎቹ

አዎ ፤ እንደቡድን ስንጫወት በምንፈልገው ደረጃ ተቆጣጥረነዋል ማለት አንችልም። ትኩረታችን ከተሸናፊነት ወደ አሸናፊነት መመለስ ላይ ብቻ ስለነበር በቁጥጥር ደረጃ ገና ይቀረናል። ግን የሰራነውን ያህል የምንተገብር ከሆነ ወደ ፊት ጥሩ ይሆናል ብዬ አስባለሁ። ያም ቢሆን አጥቂዎቻችን የማግባት አቅማቸው ምን ድረስ እንደነበር የሚያሳይ ጨዋታ ነበር።

ከጎሎቹ መሀል የእርሳቸው ምርጫ ስለሆነው ጎል

ለእኔ ሁሉም ያው ነው። አንደኛው ስትል ሁለተኛ ለማሸነፍ በምታደርገው ጥረት ዋጋ አለው። ሁለተኛው ስትል ደግሞ ሦስተኛው ሊያረጋጋን የሚችል ስለሆነ ሁሉም ዋጋ አላቸው። እንደ ቡድን ስታየው ግን ከነበርንበት ጫና ለመውጣት የመጀመሪያው ጎል ትልቅ ዋጋ አለው።

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – አዳማ ከተማ

አብዲሳ ጀማል በቂ ኳሶች ስላለማግኘቱ

ወደ ፊት ስንሄድ የተሻልን ብንሄንም ከተጋጣሚ አንፃር በቁጥር እናንስ ነበር። በተለይ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾቻችንን ነኮቪድ ምክንያት መጠቀም አልቻልንም። ዞሮ ዞሮ በራሱ ጥረት ግን ጎል ጋር ይደርስ ነበር። ተደጋጋሚ ኳሶችን ወደ ጎል ሞክሯል። እንደውም ዕድል ከማጣቱ አንፃር በግሉ የተሻለ ነገር በግሉ አድርጓል ማለት እችላለሁ።

ቡድኑን ስላወረደው ጎል እና ስለኮቪድ

ሁለተኛው ኳስ የቡድናችንን እንቅስቃሴ ያወረደ ኳስ ነው። ከጨዋታ ውጪ ይሁን አይሁን አላውቅም። ግን ይመስላል አጠገቤ ሳሰነበር ፤ እሱን ምስሉን ከተመለከትኩ በኋላ የምናገረው ይሆናል። ዞሮ ዞሮ እሱ ኳስ አውርዶናል። እንደዛም ሆኖ ለመነሳሳት ሞክረናል። ባለቀ ሰዓት ላይ ሦስተኛው ጎል መቆጠሩ ትንሽ የዳኝነት ሚዛን ብዙ ጊዜ ወይ ከጨዋታ ውጪ ወይ ፍፁም ቅጣት ምት ነው ዳኛ ላይ የሚባለው እንጂ ቴክኒካሊ መሀል ላይ በዳኝነት የሚደረጉ ፋዎሎች ዋጋ ያስከፍላሉ። ለካርድ የሚያጋልጡ ጥፋቶችን እየሰሩ በተደጋጋሚ እንደውም ወደ ተቃራኒ ቡድን ይሰጥ ነበር። እነዛ እነዛ ነገሮች እኔንም ስሜታዊ አድርገውኝ ነበር ፤ ቡድኔም ስሜታዉ ሆኖ ነበር። ግን ከዕረፍት በኋላ ተረጋግተን ለመጫወት ሞክረናል። ያው ከዕረፍት በፊት ቅድሚያውን ስለወሰዱ ያንን ይዘው ወጥተዋል። ዞሮ ዝሮ ቡድናችን ላይ ጥሩ መሻሻሎች አሉ። አዲስ ቡድን ነው እንዳያችሁት። በተለይ የግብ ጠባቂያችን አለመኖር ትንሽ ዋጋ አስከፍሎናል። ሦስቱንም ማለት ይቻላል ማዳን የሚቻል ስለነበር እዛ ጋር ያለውን ነገር የምናርም ከሆነ እና ዕድል የምናገኝ ከሆነ መጠቀም እንችላለን ብዬ አስባለሁ። ከዚህ ውጪ ለማሳሰብ መናገር የምፈልገው ነገር ግን በኮቪድ ጉዳይ አወዳዳሪው አካል በጣም ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል። ምክንያቱም በአንድ ቀን ሃያ ምናምን ሰው ተይዞ እንደገና በአንድ ቀን ሃያ ምናምን ሰው ነፃ ነው ሲባል ትንሽ ቡድኖች ላይ የሚፈጥረው ጫና ከፍተኛ ነው። ኮቪድ የፈጠረብን ጫና በጣም ትልቅ ነው። ያለመረጋጋት ነው ወደዚህ የመጣነው። ከመጣን በኋላ ይህ ነገር ሊፈጠር ችሏል። እዛ ላይ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ብዬ ነው የማስበው።


© ሶከር ኢትዮጵያ