“…በሁለት ነገሮች መነሻነት ረሒማን በስብስቡ ማካተት አልቻልንም” – ብርሃኑ ግዛው

ከሰሞኑን መነጋገሪያ የነበረውን የረሒማ ዘርጋው ለብሔራዊ ቡድን አለመመረጥ ጉዳይ የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ማብራርያ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ነገ እና ማክሰኞ ከደቡብ ሱዳን ጋር ለሚያደርጉት የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ከሳምንት በፊት ለ26 ተጫዋቾች ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል። ከተጫዋቾች ምርጫ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች ተብላ የተመረጠችው ረሂማ ዘርጋው በስብስቡ ውስጥ አለመካተቷ ከሰሞኑን መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል። የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛውም ከፊታቸው ስላለባቸው ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታ መግለጫ በሚሰጡበት ጊዜ ስለ ጉዳዩ ከጋዜጠኞች ጥያቄ ተነስቶላቸው የሰጡትን ምላሽ እንደሚከተለው አስፍረነዋል።

“እስካሁን ምንም አላልኩም ነበር። አሁን ግን ህዝብ ማወቅ አለበት። እኔ እስከማውቀው ድረስ ከረሒማ ጋር ጥሩ ግንኙነት ነው ያለን። ረሒማም ጨዋ እና ጨዋ ያሳደጋት ተጫዋች ናት። እኔ እርሷን የማውቃት ለ18 ዓመታት ነው። ከአስራ ስምንቱ ደግሞ አስራ ሦስቱን አብረን ሰርተናል። በአሠልጣኝነት ህይወቴም ካገኘኋቸው ዋንጫዎች አስራ አራቱ ከእርሷ ጋር በመሆን ያነሳኋቸው ናቸው። እስካሁንም በመከባበር ነው የሰራነው ወደፊትም በመከባበር እንደምንቀጥል አስባለሁ።

“ረሒማ ወንጂ ላይ ልምምድ ስንሰራ መጠነኛ ጉዳት አጋጥሟታል። ከጉዳቱ እንድታገግምም በደንብ ታከሚ ስንላት ነበር። እርሷ ግን አዳማ ጎበዝ ወጌሻ አሉ፤ እዛ ልሂድ አለች። ይህ በእንዲህ እንዳለ ውድድሩ ማብቂያ ላይ ደግሞ ከድካም ጋር የተያያዘ ጫናዎች ነበሩባት። ከእነዚህ ሁለት ነገሮች መነሻነት ተጫዋቿን በስብስቡ ማካተት አልቻልንም።

“በሀገራችን ጥሩ ጥሩ ወጣት ተጫዋቾች እየመጡ እንደሆነ ይታወቃል። ጥሩዎች ሲመጡ ደግሞ ወደ እነርሱ መዞር ያስፈልጋል። በፊት በፊት እኔ የምታማው ለወጣቶች ዕድል አይሰጥም በሚል ነው። አሁን ግን ልምድ ያላቸውን ከብዙ ወጣቶች ጋር እያዋሀድን ቡድን መስራት አለብን። ከዚህም መነሻነት 26 ተጫዋቾችን መርጠናል። ነገ እና ማክሰኞ በምናደርገው የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ወጣቶቹን እናያለን። በቀጣይም ቡድኑን እየገነባን በሚኖሩ ክፍተቶች ላይ ድጋሜ ተጫዋቾችን የምንጠራበት ዕድል ይኖራል።

“አላስፈላጊ ንግግሮች እኔን አያሸማቅቁኝም። ከረሂማ ጋር ምንም ግላዊ ነገር የለንም። ተጫዋቿ እንደውም ሰሞኑን እያደረገች ያለችው ነገር እውነት እሷ ነች? ብዬ እንድጠይቅ አድርጎኛል። ቀድሜ እንዳልኩት ግን ለእርሷ ጥሩ ክብር አለኝ። 18 ዓመታት ለሴቶች እግር ኳስ ስለለፋችም ክብር መስጠቱ ጥሩ ነው። በአጠቃላይ ግን የአሁኑ ስብስብ ከ95% በላይ በሴካፋ እና በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ውድድሮች ይቀጥላል። እንዳልኩት ግን አስፈላጊ በሆኑ ክፍተቶች ላይ ወደፊት ተጫዋቾችም እንጠራለን።”

አሠልጣኙ ከተጫዋቿ አለመመረጥ ጋር ተያይዞ ሲነሳ የነበረውን ነገር ካጠራ በኋላ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ብርትካን ገብረክርስቶስ የሰራችውን አይነት ስራ ቢሰሩ መልካም ነው የሚል መልዕክቱን በተከታይነት አስተላልፏል።

“ሲጀምር ልምድ ካላቸው ተጫዋቾች ረሂማን ብቻ አደለም ያልጠራሁት። ሌሎችም በርከት ያሉ ተጫዋቾችን አልመረጥኩም። ግን የረሂማ ለምን እንደተጋነነ አላቅም። ምንም ይሁን ምንም ግን ያለን ሀገር አንድ ነው። ለሀገራችን ደግሞ በአንድነት መስራት አለብን። በአጠቃላይ ልምምድ ያላቸው ተጫዋቾች የብርቱካንን ተሞክሮ ቢወስዱ መልካም ነው። ብርቱካን በብሔራዊ ቡድንም ሆነ በክለብ ደረጃ ልምድ ያላት ተጫዋች ናት። አሁን ግን አልተጠራችም። ይህ ሳይዛት ግን ወደ እኛ መጥታ አበረታታናለች። ይህ ደግሞ በጣም የሚደነቅ ነው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ