ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

ሊጉ በ17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዕረፍት ተመልሷል። በዚህ ሳምንት የተመለከትናቸው ክለብ ተኮር ጉዳዮችንም እንደሚከተለው ተመልክተናል።

👉የአሸናፊነት ሥነ-ልቦናን የተላበሰው ፋሲል ከነማ

ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሊጉን ክብር ለማንሳት ተቃርበው የነበሩት ፋሲል ከነማዎች በዘንድሮው የውድድር ዘመን ሊጉ ሊጠናቀቅ ስምንት ጨዋታዎች እየቀሩት ከተከታዮቻቸው በሁለት አሀዝ ነጥብ ርቀው ሊጉን እየመሩ ይገኛሉ። ቀሪ ጨዋታዎች ቢቀሩም በቡድኑ ተጫዋቾች እና የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ውስጥ ግን ያለው የማሸነፍ ሥነ-ልቦና ግን በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

በእርግጥ በዚህ የጨዋታ ሳምንት በርካታ የመጀመሪያ ተሰላፊ ተጫዋቾቹን ባጣው ወላይታ ድቻ ከፍ ያለ ፈተና ቢገጥመውም በሙጂብ ቃሲም ሁለት ግቦች ጨዋታቸውን አሸንፈው በመውጣት የተከታዮቻቸው ነጥብ መጣልን ተከትሎ ከተከታያቸው ኢትዮጵያ ቡና ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዮነት ወደ አስራ አንድ በማሳደግ መሪነታቸውን ይበልጥ እያደላደሉ መጥተዋል።

ፋሲል ከነማ ከጨዋታ ጨዋታ አይነተኛ የአሸናፊ ቡድኖች መገለጫዎችን ይበልጥ እያስመለከተን ይገኛል። በተለይም ቡድኑ በጨዋታዎች በተጋጣሚዎች ብልጫ ቢወሰድበትም ሆነ እድል በተቃራኒያቸው ቆማ የግብ አጋጣሚዎችን ወደ ግብነት ለመቀየር በተቸገሩባቸው የጨዋታ ቀናት ሳይቀር በትዕግሥት እስከመጨረሻው ተፋልመው ከጨዋታዎች ውጤትን ይዘው ሲወጡ አየተስተዋለ ይገኛል። ይህም ቅዱስ ጊዮርጊስን በረቱበት ጨዋታ ይበልጡኑ የተንፀባረቀ ሆኗል።

ቡድኑ በድቻው ጨዋታም እንደተመለከትነው ግቦችን ለማስቆጠር ያለልክ ሳይጣደፍ እጅግ ተረጋግቶ የጨዋታ ውጤቶችን ለመወሰን የሚሄድበት ርቀት በተጫዋቾቹ እና በአሰልጣኝ ቡድኑ አባላት ውስጥ ያለውን ከፍ ያለ የአምዕሮ ዝግጁነት እና ውጤቶችን ለመቀየር የሚያስችል አቅም መኖርን መረዳቱን በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በግልፅ የሚስተዋል ሀቅ ነው።

ዘንድሮ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ በራሳቸው ውጤት ላይ ብቻ ተመርኩዘው የዋንጫውን ባለቤትነታቸውን የማረጋገጥ እድል በእጃቸው የሚገኘው ዐፄዎቹ በዚህ የአዕምሮ ዝግጅት ከቀጠሉ የጊዜ ጉዳይ እንጂ የሊጉ ክብር መጨረሻ መዳረሻ መሆናቸው የሚቀር አይመስልም።

👉በፈተናዎች በቀላሉ እጅ ያልሰጠው ወላይታ ድቻ

ባለፉት ጥቂት ወራት ዳግም እያገረሸ የሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እግርኳሱ ላይ ጥላውን እያጠላ ይገኛል። በተለይ የድሬዳዋው ውድድር በዚህ ወረርሺኝ ሳቢያ ከወዲሁ ስጋቶች ተጋርጠውበታል።

ክለቦች ከጨዋታ ቀን 72 ሰዓታት አስቀድመው በሚያደርጉት የኮቪድ ምርመራ በዚህ የጨዋታ ሳምንት አብዛኞቹ ቡድኖች በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው የቡድን አባላቶቻቸው በቫይረሱ የመያዛቸው ዜና መነጋገርያ እየሆነ ይገኛል። በዚህ እውነታ ክፉኛ ከተጎዱ ክለቦች መካከልም ወላይታ ድቻ አንዱ ነው።

አስራ ሁለት ያክል ተጫዋቹ በቫይረሱ እንደተያዙበት የተነገረው ወላይታ ድቻ ከእነዚሁ ውስጥ በርከት ያሉት የቡድኑ ቋሚ ተሰላፊ ተጫዋቾች በመሆናቸው መነሻነት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ለወትሮው ከሚጠቀሙበት የመጀመሪያ ተመራጭ ስብስብ ላይ በርከት ያሉ ለውጦችን ለማድረግ ቢገደዱም ሜዳ ላይ በተመለከትነው እንቅስቃሴ ግን ግምቶችን አፋልሰው ጠንካራውን ፋሲል ከነማን መፈተን ችለዋል።

በዚሁ ጨዋታ ሜዳ ላይ የተመለከትነው ወላይታ ድቻ በተደራጀ መልኩ ሲከላከል እና በፈጣን ሽግግሮች እድሎችን ለመፍጠር ሲሞክር ተስተውሏል። በዚህም የፈጠራቸውን እድሎች መጠቀም ሳይችል ቀረ እንጂ የጨዋታው ውጤት መልኩን በቀየረ ነበር። ከዚህ በፈተና ውስጥ ሆኖ አስገራሚው የሜዳ እንቅስቃሴ ካሳየን ብርቱው የድቻ ስብስብ ጀርባ ያለው ቁልፍ ሚስጥር ግን ከዚህ ቀደም አሰልጣኙ የሠሯቸው ስራዎች ነፀብራቅ ነው።

ከአጋማሹ የዝውውር መስኮት በፊት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራውን ወደ መንበረ ስልጣኑ ከመጡ ወዲህ ቡድኑ ከነበረበት የስብስብ ጥልቀት ችግር መነሻነት በፋሲሉ ጨዋታ የተሰለፉት “አዳዲስ” ተጫዋቾች በተለያዩ አጋጣሚዎች በሊጉ በቀደሙት ጨዋታዎች በቋሚነት ጨዋታዎችን በመጀመር ሆነ ተቀይረው በመግባት በሊጉ መጠኑ ይለያይ እንጂ ለሊጉ አዲስ አለመሆናቸው እና የጨዋታ ልምድ ማዳበራቸው ለቡድኑ በዚህ የጭንቅ ወቅት አንዳች ተስፋን የፈነጠቀ እንቅስቃሴ አስመልከተውናል።

ወላይታ ድቻዎች ጥሩ ፉክክር ባደረጉበት በዚህ ጨዋታ አዲስ ፈራሚው የዮናስ ግርማይ እና ወጣቱ መልካሙ ቦጋለ የመሀል ተከላካይ ጥምረት በተወሰነ መልኩ ይጠበቅ በነበረው የተግባቦት ችግር መነሻነት ሁለት ግቦችን አስተናገዱ እንጂ የሜዳ ላይ ልፋታቸው ዋጋ ሊሰጠው የሚገባ ነው።

👉ሲዳማ ቡና ከድል ጋር ታርቋል

በ2002 የውድድር ዘመን አንስቶ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን የሚታወቁት ሲዳማ ቡናዎች በዘንድሮው የውድድር ዘመን ነገሮችን በሚፈልጉት መንገድ ለማስጓዝ በጣሙን ተቸግረው በአሁኑ ወቅት ቡድኑ በወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።

በሊጉ ባደረጋቸው የመጨረሻ አምስት ጨዋታዎች በሁሉም ሽኝፈትን ቀምሶ የነበረው ቡድን ድሬዳዋ ስታዲየም ላይ ውድድሩ ሲጀመር ግን የተሻሻለ ቡድን ስለመሆኑ አዳማ ከተማን የረታበት ውጤት ማሳያ ነው። ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች በውድድር አጋማሹ የዝውውር መስኮት ወደ ስብስባቸው የቀላቀሉት ሲዳማ ቡናዎች አስናቂ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ እንቅስቃሴያቸው ሦስት ግቦችን በኦኪኪ አፎላቢ ፣ ሀብታሙ ገዛኸኝ እና ማማዱ ሲዲቤ በማስቆጠር ከአምስት ጨዋታ በኋላ ወደ አሸናፊነት ተመልሰዋል።

በጨዋታው በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች ያሳዩት የነበረው እንቅስቃሴ በሰንጠረዡ ግርጌ የሚገኝ ሳይሆን በሰንጠረዡ አናት የሚገኝ ቡድን ይመስሉ ነበር። አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ቡድናቸው ውጤቱን ከመፈለጉ የተነሳ ከወትሮው በተለየ አምስት የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች በጨዋታው የመጀመሪያ አሰላለፍ ባካተቱበት ጨዋታ ከጫና ነፃ ሆነው ኳሶችን የሚቀባበሉት ሲዳማ ቡናዎች ከሶስቱ ጎሎች ሁለቱ የተገኙት በፈጣን ሽግግሮች መሆናቸው ቡድኑ ከዚህ ቀደም በዚህ አጨዋወት የነበረውን የስኬታማነት ጊዜያት ያስታወሰ ነበር።

በመጀመሪያዎች አጋማሽ የቤት ሥራቸውን በሚገባ የተወጡት ሲዳማ ቡናዎች በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታውን ፍጥነት ዝግ በማድረግ በእጃቸው ገብቶ የነበረውን ሦስት ነጥብ አስጠብቀው መውጣት ችለዋል። በዚህም ነጥባቸውን ወደ አስራ አራት አሳድገው እዛው በነበሩበት አስራ አንደኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ቢገደዱም ከቀጠናው ለመውጣት ወሳኝ ነጥቦች አሳክተዋል።

👉 በመሻሻሉ የቀጠለው ባህር ዳር ከተማ

የአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ቡድን ከባህር ዳሩ ውድድር ወዲህ በግሩም አቋም ላይ ይገኛል። ሽንፈት ካስመዘገበ ሰባት ጨዋታዎች ያስቆጠረው ቡድኑ በዚህ ሳምንት ከወልቂጤ ጋር ያደረገውን ጨዋታ 2-0 በመርታት ወደ ሁለተኛ ደረጃ ይበልጥ መጠጋት ችሏል።

በዚህ የጨዋታ ሳምንት ያለ ወሳኝ ተጫዋቹ ፍፁም ዓለሙ ወደ ሜዳ የገቡት የጣና ሞገዶቹ የአጥቂ አማካዩ አለመኖር ሳያግዳቸው ከተጋጣሚያቸው ወልቂጤ የተሻሉ የጎል ዕድሎችን መፍጠር ችለዋል። በዚህም በሁለተኛው ከአጋማሽ በአንድ ደቂቃ ልዩነት ባዬ ገዛኸኝ እና ግርማ ዲሳሳ ባስቆጠሯቸው ጎሎች አሸንፈው መውጣት ችለዋል። በጨዋታው የመሐል ተከላካያቸው መናፍ ዐወል በጉዳት ከሜዳ ሲወጣ አሰልጣኙ አህመድ ረሺድን ወደ መሐል ተከላካይነት በማሸጋሸግ ጎል ሳይቆጠርባቸው መውጣትም ችለዋል።

በዚህ ውጤት መነሻነት ነጥባቸውን 29 በማድረስ ወደ ሦስተኛ ደረጃ ከፍ ማለት የቻሉት ባህር ዳሮች ሁለተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና በአንድ ነጥብ ብቻ በማነስ በቀጣዩ የውድድር ዓመት የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳታፊነትን ለማግኘት ከሌሎች ተፎካካሪዎች በተሻለ ወቅታዊ አቋም ላይ መገኘት ችለዋል። ባህር ዳር ባለፉት ጨዋታዎች ላሳየው አስደናቂ መሻሻል እና የአሸናፊነት ጉዞ እንዲሁም የተናጠል የተጫዋቾች ብቃት መሻሻል ቡድኑ ጥሩ ባልሆነበት ወቅት በተጫዋቾቻቸው ላይ እምነት እንዳላቸው ሲያሳዩ የነበሩት አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ሚና ከፍተኛ እንደሆነ መናገር ይቻላል።

በቀጣይ የጨዋታ ሳምንት ከመሪው ፋሲል ከነማ ጋር የሚጫወቱት የጣና ሞገዶቹ በዚህ ጨዋታ የሚያስመዘግቡት ውጤት በቀጣይ ጉዟቸው ላይ የሚኖረው ድርሻ ከፍተኛ ነው።

👉ሀዋሳ ከተማ ለኢትዮጵያ ቡና የሚቀመስ አልሆነም

በአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት የሚመሩት ሀዋሳ ከተማዎች የካሳዬ አራጌውን ኢትዮጵያ ቡና በመጀመሪያው ዙር አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ በረቱበት መንገድ ድሬዳዋ ላይ በተመሳሳይ በማሸነፍ ለኢትዮጵያ ቡና የሚቀመሱ አለመሆናቸውን አስመስክረዋል።

በመጀመሪያው ዙር አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ከተከታታይ አስደንጋጭ የመክፈቻ የጨዋታ ሳምንታት ሽንፈቶች በኃላ ኢትዮጵያ ቡናን የገጠሙት ሀዋሳ ከተማዎች ፍፁም በተቀናጀ መከላከል ለ90 ደቂቃዎች ከፍ ባለ ትኩረት እና ታታሪነት በተሞላበት እንቅስቃሴ በሁለተኛው አጋማሽ ብሩክ በየነ ባስቆጠራት የመልሶ ማጥቃት ኳስ ኢትዮጵያ ቡናን መርታታቸውን ይታወሳል። በ17ኛ የጨዋታ ሳምንት ድሬዳዋ ስታዲየም ላይ ዳግም ሁለቱን ቡድኖችን ባገናኘው ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ በመጀመሪያው ዙር ቡናን ሲረቱ ውጤታማ ያደረጋቸውን አቀራረብ ዳግም ሜዳ ላይ በማሳየት አሁንም በተመሳሳይ የአንድ ለባዶ ውጤት ባለድል መሆን ችለዋል።

ከመጀመሪያው ዙር የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በተወሰነ መልኩ የተለየው ነገር ሀዋሳ ከተማዎች ከአዲስ አበባ ጨዋታ በተለየ በጨዋታው የመጀመሪያ እና ሁለተኛ አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች የተወሰነ የማጥቃት ፍላጎትን በማሳየት ወደ ኢትዮጵያ ቡና የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶችን ማድረጋቸው ነበር። እጅ ከፍ ያለ ትኩረት እና ትጋትን በሚጠይቀው የሀዋሳ ከተማ የጥንቃቄ አጨዋወት ኳስን በትዕግሥት በመቆጣጠር እድሎችን ለመፍጠር የሚተጋው ኢትዮጵያ ቡና ላይ ወሳኙን ሦስት ነጥብ ይዞ በመውጣቱ ነጥቡን ወደ ሃያ በማሳደግ ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ ተጠግቷል።

👉የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን በውጤት ማጀብ የጀመረው ድሬዳዋ ከተማ

ባለፉት ጥቂት የጨዋታ ሳምንታት ሜዳ ላይ የሚያሳየውን እንቅስቃሴ በውጤት ለማጀብ ተቸግሮ የቆየው ድሬዳዋ ከተማ ከስድስት ጨዋታዎች በኃላ የመጀመሪያውን ሶስት ነጥብ ጅማ አባጅፋር ላይ ማስመዝገብ ችሏል። ግቧን ከጥቂት ቀናት በፊት ድሬዳዋ ከተማን ከሰበታ የተቀላቀለው አማካዩ ዳንኤል ኃይሉ ከፍፁም ቅጣት ምት ማስቆጠር ችሏል።

በከፍተኛ ደረጃ የሚፈጠሩ የግብ እድሎችን ወደ ግብ የመቀየር ከፍተኛ ችግር ያለበት ቡድኑ በዘንድሮው የውድድር ዘመን የፈጠራቸው እድሎች ወደ ጎልነት መቀየር ቢችሉ አሁን ላይ ቡድኑ በሰንጠረዡ አናት ካሉት ቡድኖች ተርታ የመመደቡ ጉዳይ የሚቀር አይመስልም ነበር። ጅማን በረታበት ጨዋታ በተመሳሳይ በሁለተኛው አጋማሽ በርካታ እድሎችን የፈጠረው ቡድኑ ሁለት ኳሶች በግቡ ቋሚ ሲመለስ የተቀሩት እንደወትሮው ሁሉ በደካማ ውሳኔ አሰጣጥ መና ቀርተዋል።

ከወትሮው በተለየ በመጀመሪያው አጋማሽ ኳስን ለመቆጣጠር ፍላጎት የነበራቸው ድሬዳዋ ከተማዎች በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ቀደመው መንገዳቸው ማለትም እጅግ ፈጣን የሆኑትን የቡድኑን የአጥቂ መስመር ተሰላፊዎችን ከተጋጣሚ ተከላካይ ጀርባ እንዲሮጡ በማድረግ ተደጋጋሚ እድሎችን ለመፍጠር የሄዱት መንገድ በሁለተኛው አጋማሽ ስኬታማ አድርጓቸዋል።

አሁን የፊት መስመር ተሰላፊዎቻቸው ጉዳይ እልባት ባያገኝም በጅማ አባ ጅፋሩ ጨዋታ ተስፋ ሰጪ የሆነ የሚዋልል እንቅስቃሴን በተወሰኑ የጨዋታ ቅፅበቶች መመልከት ችለናል። ይህም አጥቂዎቻቸው ያላቸውን ተቀራራቢ ባህሪ ይበልጥ ተገማች ባልሆነ መንገድ ለመጠቀም የሚያስችል ከመሆኑ አንፃር በቀጣይ ጨዋታዎች ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። በተመሳሳይ በዘንድሮው የሊግ ቅርፅ የሜዳ ተጠቃሚነት የሚለው ጉዳይ ብዙም የሚስተዋል ባይሆን የአዘጋጅ ከተማ ክለቦች ከሌሎች በተሻለ የመጫወቻ ሜዳውን ሆነ የአየር ንብረቱን ከመልመዳቸው መነሻነት በተወሰኑ መልኩ ያላቸውን የተሻለ ተጠቃሚነት በቀደሙት አስተናጋጅ ከተማዎች የነበሩ ክለቦች በደንብ መጠቀም አለመቻላቸውን ተከትሎ ድሬዳዋ በዚህ ረገድ የመጀመሪያ ጨዋታውን ማሸነፉ የሚኖረው ጥቅም ከፍ ያለ ነው።

👉በጫና ውስጥ የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች

ለሦስተኛ ተከታታይ የውድድር ዘመን የሊጉን ክብር የማሳካት ህልማቸው እየተሟጠጠ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊሶች የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያቸው ከፍ ባለ የስነልቦና ጫና ውስጥ መገኘታቸው ተጫዋቾቹ ማድረግ የሚችሉትን ነገር ከማድረግ የገደባቸው ይመስላል። በድሬዳዋ የመክፈቻ የሊጉ መርሐ ግብር ሰበታ ከተማን የገጠሙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ያለግብ ጨዋታቸውን 0-0 በሆነ ውጤት ፈፅመዋል።

በአዲሱ እንግሊዛዊ አሰልጣኝ ፍራንክ ናታል እየተመሩ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ያደረጉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሰበታው ጨዋታ በተለየ ደቂቃዎች እየገፉ በሄዱ ቁጥር ይስተዋልባቸው የነበረው ከፍተኛ ጥድፊያ እና ይህን ተከትሎ ይፈፅሟቸው የነበሩ የውሳኔ ስህተቶች ቡድኑ ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።

በስብስብ ደረጃ ይህ ቀረው የማይባለው ቡድኑ ቀስ በቀስ የቀድሞው የሜዳ ላይ አስፈሪነቱ እየቀነሰ በመሄዱ አሁን ላይ ቡድኖች ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲገጥሙ ማሸነፍ እንደሚችሉ ማመን እየጀመሩ መምጣታቸው እና በቡድኑ ውስጥ ከሚስተዋለው ከፍ ያለ ጫና ጋር ተዳምሮ ቡድኑ እየተቸገረ ይገኛል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሊጉ ለዋንጫ ይፎካከር የነበረው ቡድኑ አሁን ላይ ቀስ በቀስ ወደ አራተኛ ደረጃ ሲንሸራተት ከመሪው ፋሲል ከነማ ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ወደ አስራ አራት ከፍ ብሏል። አሁን ላይ የቡድኑ ተቀዳሚ አላማ መሆን የሚገባው ከዋንጫው ፉክክር መራቃቸውን ተከትሎ ሌላኛው የአፍሪካ ውድድር ተሳትፎ የሚገኝበት ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ለመጨረስ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ነው።

👉የአዳማ ከተማ ደካማ መከላከል

በሊጉ ግርጌ በሰባት ነጥብ የሚገኙት አዳማ ከተማዎች በዚህ ሳምንት ከሲዳማ ቡና ባደረጉት ጨዋታ ከግማሽ በላይ ስብስባቸውን በአዲስ ተጫዋቾች ተክተው ቢቀርቡም አሁንም ውጤታቸውን ማሻሻል አልቻሉም። ይልንም በቀላሉ ግብ የሚቆጠርባቸው መሆኑን ይህ ጨዋታ አይነተኛ ማሳያ ሆኖ አልፏል።

ሦስቱን ግቦች ያስተናገዱበት መንገድ በአጠቃላይ የቡድኑ የመከላከል መንገድ ላይ ጥያቄ እንዲነሳ የሚያስገድዱ ነበሩ። የመጀመሪያው ግብ ሲቆጠር ሁለቱ የአዳማ ከተማ የመሀል ተከላካዮች ከቦታቸው ለቀው ተመሳሳይ ኳስን ለመሻማት ከአንድ የሲዳማ ቡና ተጫዋች ጋር በተሻሙበት ሒደት በተሸነፉት ሁለተኛ ኳስ የመጀመሪያውን ግብ ሲያስተናግዱ ሁለተኛ ጎል እንዲሁ የሲዳማ ቡናው የመሀል ተከላካይ ሰንደይ ሙቱኩ ከመሀል ሜዳው አጋማሽ በረጅሙ ከተከላካይ ጀርባ የጣለውን ኳስ የግራ መስመር ተከላካዮ ሚሊዮን ሰለሞን እና የመሀል ተከላካዮቹ አስቀድመው ተገንዘበው ሀብታሙ ገዛኸኝን የመሮጫ ቦታ መንፈግ ሲገባቸው በቀላሉ አምልጦ ያስቆጠረው ነው። በተመሳሳይ ሁለተኛው እና ሦስተኛ ግቦች ሲቆጠሩ የግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነት ድርሻ እንዲሁ በቀላሉ የሚታይ አልነበረም።

እግርኳስ የስህተቶች ስፖርት መሆኑ ቢታመንም እንደ አጠቃላይ የቡድኑ ተጫዋቾች በመከላከል አደረጃጀት ወቅት መወጣት የሚገባቸውን ድርሻ መወጣት አለመቻላቸው በስተመጨረሻ ስህተት ጥቂት ተጫዋቾች ላይ እንዲወድቅ ምክንያት መሆኑ ቢታመንም ቡድኑ የሚከላከልበት መንገድ ግን እጅጉን ትኩረት የሚሻ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ