በ17ኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የታዘብናቸው ዓበይት ተጫዋች ነክ ጉዳዮችን በተከታዩ መልኩ ለመዳሰስ ሞክረናል።
👉የውጭ ተጫዋቾች ቁጥር መጨመር
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ተፅዕኗቸው እየቀነሱ የሚገኙት የውጭ ሀገራት ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾች ቁጥር በሁለተኛው ዙር የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ግን በቁጥር ጨምረው ታይተዋል።
በተለይም የመውረድ ሥጋት የተደቀነባቸው ቡድኖች በተለይም አዳማ ከተማ በመጀመሪያ ዙር የተስተዋሉባቸው ክፍተቶችን ለመድፈን የቡርኪናፋሶ፣ ጋና፣ ማሊ፣ ቤኒን እና ጊኒ ዜግነት ያላቸውን ተጫዋቾች ማስፈረም ችለዋል። በእርግጥ የተቀላቀሏቸው ቡድኖች ላይ የሚፈጥሯቸው ተፅዕኖዎች በሒደት የሚታይ ቢሆንም ላለመውረድ እየተጫወቱ የሚገኙ ቡድኖች በሁለተኛው ዙር ከፍተኛ በጀት በመመደብ በርከት ያሉ የውጭ ሀገራት ተጫዋቾችን በውድድር ዘመኑ አጋማሽ የዝውውር መስኮት የመሰብስብ ዝንባሌ በሊጋችን ቀስ በቀስ እየተለመደ መጥቷል።
በመጀመሪያው ዙር ደካማ የነበሩት ቡድኖች በሁለተኛው ዙር ተሻሽለው ለመቅረብ የአዳዲስ ተጫዋቾችን ማስፈማቸው የተለመደ ቢሆንም በዚህ ሒደት ውስጥ ግን ለሀገሪቱም ሆነ ለእግርኳሱ ሩቅ የሆነ የውጭ ሀገራት ተጫዋቾች በዚህ ውጤት ሆነ አዎንታዊ ተፅዕኖ ከተጫዋቾች በሚጠበቅበት ፈታኝ ሰአት ላይ በብዛት ወደ ስብስብ የመቀላቀሉ አካሄድ ግን ለቡድኖቹ ነገሮችን ፈታኝ እንዳያረግባቸው ያሰጋል።
👉ፓትሪክ ማታሲ በጨዋታ ዕለት ስብስብ
በ6ኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሃግብር በሸገር ደርቢ በ10ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከሜዳ ከተወገደ ወዲህ ከክለቡ አመራሮች ጋር በፈጠረው አለመግባባት ለወራት ከቡድኑ ስብስብ ውጭ የነበረው ኬኒያዊው ግብ ጠባቂ ፖትሪክ ማታሲ ዳግም በጨዋታ ዕለት ስብስብ ውስጥ ተመልከተነዋል።
በተፈጠረው አለመግባባት ክለቡን በስምምነት ለመልቀቅ ደብዳቤ አስገብቶ የነበረው ማታሲ በአሰልጣኝ ፍራንክ ናታል የመጀመሪያ ይፋዊ የጨዋታ ዕለት ስብስብ ውስጥ አካል በመሆን በሰበታ ከተማው ጨዋታ በተጠባባቂነት ጨዋታው መጀመሩን መመልከት ችለናል። ታድያ የአዲሱ አሰልጣኝ መምጣት ለተጫዋቹ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ህልውናውን ለማስቀጠል ተጨማሪ እድል ያስገኝለት ይሆን የሚለው በቀጣይ የሚታይ ይሆናል።
👉ቤኒናዊው “አዱኛ ፀጋዬ”
በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የድሬዳዋ ከተማ የመጀመሪያ የጨዋታ ሳምንት የማሳረጊያ መርሐግብር ሲዳማ ቡና አዳማ ከተማን መርታት ችሏል።
በጨዋታው በሲዳማ ቡና በኩል ክለቡን በውድድር አጋማሹ የዝውውር መስኮት የተቀላቀለው ቤኒናዊው ግብ ጠባቂ ፋቢያን ፋርኖሌ ለክለቡ የመጀመሪያውን ጨዋታ ማድረግ ችሏል። በጨዋታው ግብጠባቂው ጥሩ ጥሩ ኳሶችንም እንዲሁ ማዳን ችሏል።
በጨዋታውም አዲሱ የሲዳማ ቡና ግብጠባቂ በመጀመሪያው ዙር ከፍቅሩ ወዲሳ እና መሳይ አያኖ ቀጥሎ የሲዳማ ቡናው ሦስተኛ ግብጠባቂ ይለብሰው የነበረውን “23” ቁጥር መለያ ላይ “Adunga T.” እስከሚለው ፅሁፍ በጨዋታው ላይ ለብሶ ሲጠቀም አስተውለናል።
በሁለተኛው አጋማሽ ሲዳማዎች የአዱኛን ፀጋዬን ስም በሌላ ቀለም በመጠቀም ለማደብዘዝ ጥረት አድርገው ብንመለከትም ከጨዋታው አስቀድሞው በፋርኖሌ ስም የታተመ መለያ ማዘጋጀት ባይቻል እንኳን መሰል ቸልተኝነት የተሞላበት ድርጊቶች ከክለቡን ገፅታ አንፃር በቀጣይ ሊታረሙ ይገባል።
👉”አነሳሹ” ሪችሞንድ አዶንጎ
ድሬዳዋ ከተማ ጅማ አባ ጅፋርን በረታበት ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ጉዳት ባስተናገደው አስቻለው ግርማ ምትክ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ጋናዊው አጥቂ ሪችሞንድ አዶንጎ በሜዳ ላይ በነበረው ቆይታ የተለየ ተግባርን ሲፈፅም ተስተውሏል።
ተጫዋቹ ድል እጅግ ያስፈልገው ለነበሩ ቡድን ተጫዋቾች በሜዳ ላይ በነበረባቸው ደቂቃዎች ያበረታታበት እንዲሁም ተጫዋቾች ያነሳሳበት የነበረው መንገድ እጅግ አስደናቂ ነበር። በጨዋታው ተጫዋቹ ግብ ማስቆጠር ባይችልም የቡድኑን መንፈስ በመገንባት ረገድ ለተወጣው ሚና ግን አድናቆት ሊቸረው ይገባል።
👉ለሰበታ መፍትሔ ይዞ የመጣው ኦሲ ማውሊ
በመጀመሪያው ዙር የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሰበታ ከተማ እንደ ቡድን ኳስን ለመቆጣጠር ከመሻት በዘለለ በማጥቃቱ ረገድ የጠሩ መንገዶችን ሲከተሉ አይስተዋልም። በተለይም ቡድኑ በመስመሮች በኩል ያለው የማጥቃት እንቅስቃሴ እጅግ የተዳከመ መሆኑ ተስተውሏል።
በውድድር ዘመኑ አጋማሽ በተለይ ይህን ችግር ለመቅረፍ በማሰብ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የቀድሞውን የመቐለ 70 እንደርታ እና ፋሲል ከነማ የመስመር አጥቂ ኦሲ ማውሊን ወደ ስብስባቸው መቀላቀላቸው ይታወሳል።
ኦሲ ማውሊም ለክለቡ ባደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ምንም እንኳን ግብ ማስቆጠር ባይችልም በሜዳ ላይ የነበረው እንቅስቃሴ ግን የተሟላ ነበር። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በነበረው ጨዋታ ማውሊ በመስመሮች በኩል የሚሰነዙር ጥቃቶችን ለማሻሻል ሰበታዎች እርግጥም እሱን በማዘዋወራቸው መልስ ያገኙ ይመስላል።
ታታሪው አጥቂ በመስመር አጥቂነት እንዲሁም በሁለተኛው አጋማሽ በፊት አጥቂነት በተሰለፈበት የቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ላይ ተጫዋቹ ከመስመር እየተነሳ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን በመሰንዘር ለአዲሱ ቡድኑ ሰበታ ከተማ ተስፋ ሰጪን እንቅስቃሴ በመጀመሪያው ጨዋታ ማሳየት ችሏል።
👉ዳንኤል ኃይሉ ተፅዕኖውን ማሳረፍ ጀምሯል
በውድድር ዘመኑ አጋማሽ የዝውውር መስኮት የቀድሞው የባህር ዳር ከተማ አማካይ ዳንኤል ሀይሉ ሰበታ ከተማን ለቆ ድሬዳዋ ከተማን መቀላቀሉ ይታወሳል። ተጫዋቹ ለአዲሱ ቡድኑ ባደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ቡድኑ ከስድስት ጨዋታዎች በኃላ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያሳካባትን ብቸኛ ግብ በፍፁም ቅጣት ምት ማስቆጠር ችሏል።
በድሬዳዋ ከተማ የመሐል አማካይ ስፍራ ከዳንኤል ደምሴ ጋር በመጣመር ጥሩ እንቅስቃሴን ባደረገበት የጅማ አባጅፋሩ ጨዋታ አዲሱ የድሬዳዋ ከተማ ፈራሚ በመጀመሪያ አጋማሽ ኳስን ለመቆጣጠር ባሰበው የዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ ቡድን ውስጥ ይህን እንቅስቃሴ ከተከላካዮች ፊት ሆኖ በመምራት እና ኳሶችን በማደራጀት አይነተኛ ሚናን ሲወጣ በሁለተኛው አጋማሽ ደግም ፈጣን አጥቂዎቻቸውን ወደ እንቅስቃሴ ሊያስገቡ የሚችሉ የተመጠኑ ኳሶችን በማድረስ ጥሩ የጨዋታ ቀን አሳልፏል።
በቀጣይ ጨዋታዎችም ቡድኑ የተጫዋቹን ልምድ በመጠቀም ከወራጅ ቀጠና ስጋት ለመላቀቅ በሚያደርጉት ጥረት ከዳንኤል ኃይሉ ብዙ የሚጠብቅ ይሆናል።
👉”ጎል የተራበው” ሙጂብ ቃሲም
በፋሲል ከነማ አስደናቂ የ2013 ግስጋሴ ውስጥ በግንባር ቀደምነት ከሚጠቀሱ ስሞች ሁሉ ቀድሞ የሚነሳው ሙጂብ ቃሲም በሊጉ አስራ ስድስተኛ እና አስራ ሰባተኛ ግቦቹን ቡድኑ በ17ኛ ሳምንት ወላይታ ድቻን ሲረቱ በማስቆጠር ከአቡበከር ናስር ጋር የነበረውን ልዮነት ወደ ሦስት ማጥበብ ችሏል።
በአማካይ በጨዋታ አንድ ግብን እያስቆጠረ የሚገኘው ሙጂብ ቃሲም በወላይታ ድቻው ጨዋታ ይታይበት የነበረው የጎል ርሀብ አስገራሚ ነበር። ተጫዋቹ በጨዋታው እያንዳንዱን እድሎች ወደ ግብነት ለመቀየር ከነበረው ከፍተኛ ፍላጎት ባነሰ የቡድን አጋሮቹ ለሚያመክናቸው ኳሶች ያሳየው የነበረው አካላዊ ቋንቋ ተጫዋቾች ያለበትን እጅግ ከፍተኛ መነሳሳት የሚያሳይ ነበር።
የፋሲል ከነማን ግብ የማምረት ኃላፊነት ለብቻው እየተወጣ የሚገኘው ሙጂብ አስራ ሁለት ግቦች ላይ ለጥቂት ሳምንታት ከቆመ ወዲህ አሁን ላይ በተከታታይ ዳግም ግቦችን ማምረት ጀምሯል። በዚህ አካሄዱ የሚቀጥል ከሆነም ለከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት የሚደረገው ፉክክር ይበልጡኑ እየጦዘ መምጣቱ አይቀርም።
👉 አሕመድ ረሺድ በመሐል ተከላካይነት
ባህር ዳር ከተማ ወልቂጤን 2-0 ባሸነፈበት ጨዋታ አሕመድ ረሺድ ጨዋታውን በግራ መስመር ተከላካይነት ቢጀምርም መናፍ ዐወል ጉዳት ማስተናገዱን ተከትሎ አሰልጣኝ ፋሲል በሌላ የመሐል ተከላካይ ከመተካት ይልቅ አሕመድን ወደ መሐል በማሸጋሸግ በግራ ተከላካይ ቦታ ላይ ሳሙኤል ተስፋዬን ቀይረው አስገብተዋል። በቀሪው ሰፊ የጨዋታ ክፍለ ጊዜም አሕመድ ከሰለሞን ወዴሳ ጋር ጥሩ ጥምረት በመፍጠር ቡድኑ ጎል እንዳያስተናግድ አድርጓል።
በሁለቱም እግሮቹ በእኩል ደረጃ የሚጫወተው አሕመድ በእግርኳስ ዘመኑ በቀኝ እና ግራ መስመር ተከላካይነት ተመጣጣኝ የጨዋታ ቁጥርን ማድረግ የቻለ ሲሆን በመሐል ተከላካይነትም አልፎ አልፎ ሲጫወት ይስተዋላል። የተለይ በበቡና ቆይታው አሰልጣኝ አንዋር ያሲን በቦታው ሲጠቀሙበት የነበረው አሕመድ ጠባብ የተከላካይ አማራጭ ላለው ባህር ዳር ወደፊት ጥሩ መፍትሄ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።
👉ስህተት ያበዛው የወልቂጤ ከተማ የኋላ ክፍል
በሊጉ ጅማሮ የመጀመርያ ጨዋታዎች በጥንካሬያቸው ከሚጠቀሱ የተከላካይ መስመሮች አንዱ የነበረው የወልቂጤ የኋላ መስመር አሁን ላይ በነበረው ጥንካሬ ላይ አይገኝም። ቡድኑ በተለይ በቅዱስ ጊዮርጊስ 4-3 ከተረታበት ጨዋታ ወዲህ በተጫዋቾች ላይ የተናጠል ስህተት በተደጋጋሚ እየተስተዋለ ይገኛል።
በዚህ የጨዋታ ሳምንትም ቡድኑ የተቆጠሩበት ሁለት ጎሎች ለዚህ ማሳያ ነበሩ። የመጀመርያው ጎል ላይ በግራ የመከላከል ክፍል ላይ በነበሩ ተጫዋቾች ላይ ከፍተኛ የትኩረት ችግር ሲስተዋል በሁለተኛው ጎል ላይ ደግሞ ከቀኝ መስመር ተከላካዩ ይበልጣል ሽባባው የኳስ የመመስረት ስህተት እስከ መሐል ተከላካዮቹ ትኩረት ማጣት እንዲሁም ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው ጊዜውን ያልጠበቀ ውሳኔ ድረስ አስተዋፅኦ ነበረው።
ከቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ዳግም ንጉሤ ከጉዳት መልስ በነበረበት አቋም ላይ አለመገኘት ለቡድኑ የኋላ ክፍል መሳሳት ዋነኛው መንስኤ ይመስላል። ተጫዋቹ በተደጋጋሚ በቀጥታ ጎል ለሆኑ ስህተቶች ተጋላጭ ከመሆኑ በተጨማሪ በቀድሞው የአካል ብቃት ደረጃው ላይ ስለመገኘቱም አጠራጣሪ ነው።
አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ለረመዳን የሱፍ የሰጡት ሰፊ ማጥቃት ተሳትፎ ነፃነት በቡድን ሚዛን አለማመጣጠናቸውም ሌላው የኋላ ክፍሉ ተጫዋቾች ለስህተት እንዲጋለጡ በር የከፈተ ጉዳይ ነው። አማካይ ክፍሉ የመከላከል ተሳትፎ እንዲሁም የመስመር አጥቂዎቹ ተመላልሶ ክፍተቶችን የመዝጋት ብቃትም ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው።
© ሶከር ኢትዮጵያ