ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

በድሬዳዋ ከተማ የመጀመሪያ የጨዋታ ሳምንቱን ባጠናቀቀው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የተመለከትናቸውን አሰልጣኝ ነክ ጉዳዮች እና ዓበይት አስተያየቶች በተከታዮ ፅሁፍ ዳሰናቸዋል።


👉እንደ ቡድን የመጫወት ጉዳይ

በዘመናዊዉ እግርኳስ አንዳንድ ቡድኖች ከተጋጣሚዎቻቸው አንፃር ያላቸውን ግልፅ ልዩነት ለማጥበብ ብሎም ከተቻለ የተሻለ ሆነ ለመገኘት ነቢር ነበብ የሆኑ ስልታዊ ቡድኖችን በመገንባት ለመገዳደር ይጥራሉ። በዚህ ሂደት ውስጥ እንደ ቡድን የመጫወት ጉዳይ ትልቅ አፅንኦት የሚሰጠው ነው።

በመሰል ቡድኖች ውስጥ ተጠቃሽ ክዋክብት ባይኖሩም ቡድኑ ክነዚህ ክዋክብቶች የሚፈጥሩትን ተፅዕኖ እንደ ቡድን በመነቀሳቀስ በብዙ አማካይ የብቃት ደረጃ ባላቸው ተጫዋቾች የጋራ ጥረት የእነዚህን ክዋክብት ክፍተት ለመድፈን ይሞክራሉ ፤ ከዚህም በተጨማሪ በተጫዋቾች የብቃት ልዮነት የሚወሰድባቸውን ብልጫ ለማካካስ ደግሞ ከተጋጣሚ ቡድን አንፃራ ውጤታማ ሊያደርጓቸው የሚችሉ ስልቶችን በመከተል ይህን ልዮነት በተመሳሳይ ለማጥበብ ይሞክራሉ።

ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነን ጉዳይ ሀዋሳ ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን የረታበት ጨዋታ ነው። ሀዋሳ ከተማ በሁለቱም ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ቡናን ሲረታ ከቡድኑ ውጤት ጀርባ በልዩነት የሚጠቀስ ተጫዋቾች ባይኖርም እንደ ቡድን የቡድን ተጫዋቾች ባደረጉት ተጋድሎ የተገኘ ውጤት ነው።

በእግርኳስ የማጥቃት አጨዋወቶች ተጫዋቾች በነፃነት የራሳቸው አዕምሮ በፈቀደው መልኩ ደመነፍሳዊ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ለተጫዋቾች ራሳቸውን ለመግለፅ የተመቸ ሲሆን በተቃራኒው የመከላከል አጨዋወቶች ከራስ አቅም ይልቅ የተጋጣሚን እንቅስቃሴ ማቋረጥ ላይ ያተኮረ መሆናቸው ከፍተኛ ታክቲካዊ ዝግጅት ሆነ የትኩረት ደረጃን ከመፈለጋቸው አንፃር በተቀናጀ መልኩ ለ90 ደቂቃዎች መከላከል ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠው ነው።

ሀዋሳ ከተማዎች አሉታዊ በሆነ አቀራረብ በሊጉ የእራሱ የሆነ መለያ ባህሪ ያለውን ቡድን ምንም እንኳን ወደ ጨዋታው ሁለተኛ የማሸነፍ ግምትን ይዘው ቢገቡም በጠንካራ የቡድን ስራ ይህ የጥራት ልዮነት ቀልብሰው ውጤታማ መሆን ችለዋል ፤ ይህ በሊጉ እየተዋዳደሩ ለሚገኙ በርካታ ቡድኖች እንደ ቡድን በአንድ ገዢ የጨዋታ ስልት ውስጥ ሆኖ መጫወት የሚያስገኘውን ጥቅም ለማሳያነት መቅረብ የሚችል ጨዋታ ነበር።

👉የገብረመድህን ኃይሌ የመጀመሪያ ድል በሲዳማ

ላለመውረድ እየታገለ የሚገኘው ሲዳማ ቡናን በውድድር ዘመኑ አጋማሽ የተረከቡት ገብረመድህን ኃይሌ ከጨዋታዎች በኃላ የመጀመሪያ ድሉን በሲዳማ ቡና ቤት ማስመዝገብ ችለዋል።

እንደ ቡድን በመጀመሪያው አጋማሽ ምርጥ ጊዜን ያሳለፉት ሲዳማ ቡናዎች በተለይ አሰልጣኙ ቡድን ከተረከቡ ወዲህ ያስፈረሟቸው ተጫዋቾች የሚጠበቅባቸውን ግልጋሎት መስጠት ስለመጀመራቸው ፍንጮች በታዩበት ጨዋታ ነባሮቹ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች ዳግም በሚታወቁበት አቅም ላይ ባይገኙም ሀብታሙ ገዛኸኝ እና ማማዱ ሲዲቤ ግብ ከማስቆጠር ባለፈ በጨዋታው የተሻለን እንቅስቃሴ ማድረጋቸው በቀጣይ ጨዋታዎች አሰልጣኙ ቡድናቸው ወደተሻለ መንገድ ጉዞ ስለመጀመሩ ፍንጮች ናቸው።

👉የዘማርያም እና የተጫዋቾቹ ደስታ አገላገፅ

በ17ኛ የጨዋታ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ ውድድሩ ወደ መቀመጫ ከተማቸው በመመለሱ የተነቃቁ የሚመስሉት ድሬዳዋ ከተማዎች ጅማ አባጅፋርን በአዲስ ፈራሚያቸው ዳንኤል ኃይሉ ብቸኛ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል በማሸነፍ ከስድስት የጨዋታ ሳምንታት በኃላ ሙሉ ሦስት ነጥብ ማስመዝገብ ችለዋል።

ድሬዎችን አሸናፊ ያደረገችው ግብ ከተቆጠረች በኃላ የድሬዳዋ ከተማ ተጫዋቾች ወደ አሰልጣኛቸው በቀጥታ እየሮጡ በማምራት ወደ አሰልጣኛቸው የሱሪ ኪስ ውስጥ ሙሉ ሦስት ነጥቡ ወደ ካዝናቸው መግባቱን ለመግለፅ በእጅ እንቅስቃሴ ሦስቱን ነጥቦቹን ወደ ኪሶቹ መግባታቸውን ለመግለፅ የሞክሩበት መንገድ ያልተለመደ ትዕይንት ነበር።

👉ቅብጥብጡ ናታል

ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት የአሰልጣኝ ሹም ሽሩ አሁንም እንደቀጠለ ይገኛል። ከቀናት በፊት ፈረሰኞቹ በማሒር ዳቪድስ ምትክ እንግሊዛዊውን አሰልጣኝ ናታልን መሾማቸው ይታወሳል።

እንግሊዛዊው ፍራንክ ናታል የመጀመሪያ የፉክክር ጨዋታቸውን በዚህ የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ሰበታ ከተማን በገጠመበት ጨዋታ ማድረግ ሲችሉ በሜዳው ጠርዝ በነበራቸው የመጀመሪያ የ90 ደቂቃ ቆይታም ተጫዋቾቻቸውን በተደጋጋሚ ለማነሳሳት ብሎም በሜዳ ጠርዝ ሆነው እንቅስቃሴዎችን ከፍ ባለ ስሜት ሲከታተሉ ተስተውለዋል።

በተጨማሪም አሰልጣኙ በድህረ ጨዋታ ቃለ መጠይቃቸው ወቅት በቀጣይ ቡድኑ በእሳቸው የአሰልጣኝነት ዘመን ይበልጥኑ ለኳስ ቁጥጥር ትኩረት ሊሰጥ እንደሚችል ፍንጭ የሰጠ ሀሳብ ሲሰጡ ተደምጠዋል።

ዓበይት አስተያየቶች

👉ሥዩም ከበደ ወላይታ ድቻን ስለረቱበት ጨዋታ….

“የጨዋታው የመጨረሻ ሰዓት ላይ የወላይታ ድቻ የተወሰኑ ተጫዋቾች እንደታመሙ ሰምተን ነበር። ይህ ቢሆንም ግን ሜዳ ላይ የነበረው ነገር ከዚህ የተገላቢጦሽ ነው። ሜዳ ውስጥ የነበሩት የድቻ ተጫዋቾች በጣም ጥሩ ነበሩ። ማድረግ የሚፈልጉትን ነገር ለማድረግ ያላቸው ቁርጠኝነትም ደስ ይላል። እኛ ደግሞ የዛሬውን ጨዋታ እንደ ፍፃሜ ነበር የወሰድነው። ምክንያቱም ከተከታዮቻችን የምንርቅበት ዕድል ያለን ዛሬ ነበር። በዚህም ስሌት በሁለቱም አጋማሽ የነበረን ነገር ጥሩ ነው። በተወሰነ መልኩ የሚቆራረጡ ነገሮች ቢኖሩትም አጠቃላይ የቡድናችን አደረጃጀት ጥሩ ነበር። ያገኘነውም ውጤት እጅግ አስደስቶኛል። ለቀጣይ ጨዋታዎችም የሚያነሳሳን ይሆናል። ከዚህም በኋላ በድሬዳዋ በሚኖሩን ጨዋታዎችም ትልቅ ስንቅ ለሀዋሳው ውድድር ይዘን የምንሄድ ይመስለኛል።”

👉ዘላለም ሽፈራው ቡድኑ ሰባት ወሳኝ ተጫዋቾችን በህመም ምክንያት አጥቶ ስላደረገው ጨዋታ?

“ሰባት ወሳኝ ተጫዋቾችን በአንድ ጊዜ ማጣት ያስደነግጣል። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ እንደዚህ አይነት አጋጣሚዎች ያልታሰበ ነገር ይዘው ይመጣሉ። ካልተጠበቁ ተጫዋቾች የማይጠበቅ ነገር እንደሚመጣም ማሳያ ነው። በእርግጥ ጨዋታውን ተሸንፈናል ግን ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ የግብ ማግባት ዕድሎችን ስንፈጥር ነበር። ግን የመጠቀም ችግር ነበረብን። በአጠቃላይ ግን በዛሬው የተጫዋቾቼ ብቃት ተደስቻለሁ። ረክቻለሁ!”

👉ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ቡድኑ በሁለተኛው አጋማሽ ውጤታማ ስላደረጋቸውው የእንቅስቃሴ ለውጥ…

“ዛሬ ከወትሮ በተለይ ኳስን ይዘን ለመጫወት ሞክረናል። ይህንን ስናደርግ ደግሞ ከጎሉ ራቅን። ከዚህም መነሻነት ቶሎ ቶሎ ወደ ጎል ለመድረስ በሁለተኛው አጋማሽ ተነጋግረን ወደ ሜዳ ገብተናል። በተነጋገርነውም መሠረት ስኬታማ ሆነናል። በዚህም ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን ፈጥረን ጎል አስቆጥረን አሸንፈን ወጥተናል።በአጠቃላይ ጨዋታውን ካየነው ግን የግቦቹ ቋሚ እና አግዳሚዎችም ከእነሱ ጋር ነበሩ። በተደጋጋሚ የግቡ አንግሎች ኳሶቻችንን ይመልሱ ነበር። በአጠቃላይ የተሻለው ቡድን ሦስት ነጥብ ከጨዋታው ይዞ ወጥቷል።”

👉ገብረመድህን ኃይሌ አዳማን የረቱበት ጨዋታ ስለነበረው ዋጋ

“የዚህ ጨዋታ ዋጋው በጣም ብዙ ነው። ከረጅም ጊዜ በኋላ ነው ወደ አሸናፊነት የተመለስነው። ለቡድናችን የስነ ልቦና የበላይነትን የሚጨምር ነው። ወደ አሸናፊነት መመለስ በራሱ አንድ ትልቅ እርምጃ ነው።”

👉ፋሲል ተካልኝ ከሁለቱ ግቦች የሚመርጡት እና ወደ ሰንጠረዡ አናት ስለመጠጋታቸው

“ከሁለት ቆንጆ ሴቶች አንዱን ምረጥ እንደማለት ነው ፤ ሁለቱም ውብ ናቸው።

“ረጅም ነው ጉዞዎ ገና ከፊታችን ስምንት ጨዋታዎች ይቀሩናል። ከፊታችን ፋሲል እያሸነፈ ነው። እኔ የምፈልገው በእያንዳንዱ ጨዋታ በአዕምሮም በአካልም ተዘጋጅተን ጨዋታዎችን ማሸነፍ ነው። ማሸነፍ ካለ መጨረሻ ወደምንፈልገበት ቦታ እንደርሳለን። እስከአሁን የመጣንበትን መንገድ እያስቀጠልን ለመሄድ እንጥራለን።”

👉ዘርዓይ ሙሉ ስለኮቪድ ወቅታዊ ሁኔታ

“ለማሳሰብ የምፈልገው ነገር ግን በኮቪድ ጉዳይ አወዳዳሪው አካል በጣም ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል። ምክንያቱም በአንድ ቀን ሃያ ምናምን ሰው ተይዞ እንደገና በአንድ ቀን ሃያ ምናምን ሰው ነፃ ነው ሲባል ትንሽ ቡድኖች ላይ የሚፈጥረው ጫና ከፍተኛ ነው። ኮቪድ የፈጠረብን ጫና በጣም ትልቅ ነው። ያለመረጋጋት ነው ወደዚህ የመጣነው። ከመጣን በኋላ ይህ ነገር ሊፈጠር ችሏል። እዛ ላይ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ብዬ ነው የማስበው።”

👉ፀጋዬ ኪዳነማርያም ጫና ውስጥ እየገቡ ስለመሆኑ

“ያለንበት ደረጃ አሳሳቢ ነው። ያም ሆነ ይህ ግን እግር ኳስ ተስፋ የምትቆርጥበት አደለም። ስምንት ጨዋታዎች ይቀሩናል። ዛሬ የመጀመሪያ ጨዋታችን ነው። ከዚህ በኋላ ደግሞ ጠንክረን እና ተስተካክለን እንቀርባለን ብዬ እገምታለሁ።”

👉ካሣዬ አራጌ ጉሽሚያዎች መበርከታቸው ስለነበረው ተፅዕኖ

“ዳኞች የእኛን ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ተጫዋቾች መከላከል አለባቸው ፤ ህጉን ተግባራዊ በማድረግ። ካልሆነ ግን ተጫዋቾች በነፃነት መጫወት አይችሉም። በስጋት መጫወታቸው ደግሞ ያላቸውን አቅም እንዳያሳዩ ያደርጋቸዋል። በሙሉ ልባቸውም ኳሱ ላይ መስራት ያለባቸውን እንዳይሰሩ ያደርጋል። ከዚያ ደግሞ ሁኔታው ሲቀጥል ወደ ስሜታዊነት ይወስዳቸዋል። እርግጥ ነው ዳኞች ጋር ስህተት ሲኖር ተጫዋቾች ስሜታዊ መሆን አለባቸው የሚለው ባያስኬድም በተደጋጋሚ ጥፋት ሲሰራባቸው ወደእንደዛ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የመግባት ነገር ነበር።”

👉ሙሉጌታ ምህረት ተጫዋቾቹ ላይ ይታይ ስለነበረው ስሜታዊነት

“ከመጀመሪያም ጀምሮ የመጣ ነው። የተጎዱብን ተጫዋቾች ስለነበሩ ያሉትን ሁሉም ለእኔ እኩል እንደሆኑ እና ማናቸውም መጫወት እንደሚችሉ ኃላፊነቱንም እንደምወስድላቸው ስለነገርኳቸው ጥሩ የቡድን መንፈስ ላይ ነበርን። መነሳሳቱ ከዛ የጀመረ ሲሆን ሜዳ ውስጥም በተግባር የታየው ይሄ ነበር።”


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ