ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

በ17ኛ ሳምንት የድሬዳዋ ከተማ የመጀመሪያ የጨዋታ ሳምንት የተመለከትናቸው ሌሎች የትኩረት ነጥቦች በዚህ ፅሁፍ ተካተዋል።

👉 አሳሳቢው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እና እግርኳሳችን

የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መልኩን እየቀያየረ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሀገራትን ክፉኛ መምታቱን ቀጥሏል። በሀገራችን የኮቪድ-19 በጥቅሉ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከማሻቀቡ ጋር በተያያዘ የፅኑ ታማሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ የሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያዎች እጥረት መነሻነት የሟቾች ቁጥር ከቀን ወደቀን እየጨመረ የመገኘቱ ጉዳይ የአደባባይ ሚስጥር ከሆኑ ቀናት ተቆጥረዋል።

ታድያ በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንኳን የእግርኳስ ውድድሮች በከፍተኛ ጥንቃቄ በተቀመጠላቸው የኮቪድ ፕሮቶኮል መሰረት ለማካሄድ ጥረቶች እየተደረጉ ቢገኝም እግርኳሱም እንደ ማህበረሰብ የሚስተዋልብን ቸልተኝነት በየውድድር ሜዳዎች ሆነ በተጫዋቾች የማደርያ ስፍራ መንፀባረቃቸውን መመልከት ከጀመርን ሰንበተናል። በተደጋጋሚም መሰል ድርጊቶች ላይ የውድድሩ አስተዳዳሪ አካላት የእርምት እርምጃ እንዲወስዱ ቢጠየቅም ሰሚ በመጥፋቱ አሁን የደረስንበት አደገኛ ሁኔታ ላይ እንገኛለን።

በዚህም መነሻነት አስተዳዳሪው ከዚህ ቀደም በክለቦች በኩል ወደ ሜዳ እንዲገቡ ከሚደረጉ ደጋፊዎች ጋር በተያያዘ ጥያቄዎች ይነሳበት በነበረው ጉዳይ ዙርያ ከድሬዳዋው ውድድር የመጀመሪያ ጨዋታ ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ቀን አንስቶ ወደ ሜዳ እንዳይገቡ ክልከላዎችን የጣለ ሲሆን ይህም ቫይረሱ በድሬዳዋ ከተማ ካለው ከፍተኛ ስርጭት አንፃር በበጎው የሚወሰድ መልካም ውሳኔ ነው።

ሌላው አሳሳቢው ጉዳይ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተጫዋቾች ቫይረሱ እየተገኘባቸው የመምጣቱ ጉዳይ ነው። ይህ ከምንም በላይ ልብ ሊባል የሚገባ እና ትኩረትን የሚሻ ጉዳይ ነው። ተጫዋቾች ሆነ የቡድን አባላት በዚህ አስከፊ ወቅት ይበልጥ ትኩረት ሰጥተው በቅድሚያ ራሳቸውን በማስተከተል ደግሞ በዙሪያቸው ያሉትን ሰዎች ከቫይረሱ የመጠበቀ ረገድ የተጣለባቸውን ከፍተኛ ኃላፊነት መወጣት ይጠበቅባቸዋል።

ሌላኛው አነጋጋሪ የነበረው ጉዳይ የኮቪድ ምርመራ ውጤት ትክክለኝነት ጉዳይ ነው። ክለቦች በመጀመሪያ ባደረጓቸው ምርመራዎች በርካታ ቁጥር ያላቸው የቡድን አባላት ቫይረሱ እንደተገኘባቸው የሚገልፁ ውጤቶች መውጣታቸውን ተከትሎ የአንዳንድ ጨዋታዎች የመካሄዳቸው ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ የገቡበት አጋጣሚ መኖሩን አስተውለናል። ሆኖም ለሁለተኛ ጊዜ ክለቦች ናሙናቸውን ሀረር ወደ ሚገኘው የሀሮማያ ዩኒቨርስቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተልኮ ሲመረመሩ ደግሞ በርካቶቹ በመጀመርያ ምርመራ ቫይረሱ እንዳለባቸው ተገልፀው የነበሩ ተጫዋቾች ነፃ ሲሆኑም የተመለከትንበት ጉዳይ የላብራቶሪዎቹን የምርመራ ውጤት ትክክለኝነት ዙርያ ጥያቄ እንድናነሳ የሚያደርጉ ናቸው።

👉 የምሽት ጨዋታዎች ዳግም መመለስ

በኢትዮጵያ የክለቦች የእግርኳስ ውድድር በተለይም በ1990 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እንደ አዲስ ከተደራጀ ወዲህ ለዓመታት በብቸኝነት በምሽት ጨዋታዎች ለማድረግ የሚረዱ መብራቶች የተገጠሙለት አንጋፋው የአዲስ አበባ ስታድየም በርከት ያሉ ጨዋታዎችን አመሻሽ ላይ ያካሄድ እንደነበር ይታወሳል።

ከአዲስ አበባ ስታድየም በተጨማሪም የወልዲያው ሼህ መሀመድ ዓሊ አልአመዲን ስታድየም እንዲሁ በ2008 የስታድየሙን ምርቃት አስመልክቶ ወልዲያ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ያደረገው ጨዋታ እንዲሁ በብቸኝነት የሚጠቀስ ከአዲስአበባ ስታድየም ውጪ የተደረገ ብቸኛው የሊግ ጨዋታ መሆኑ ይታወሳል።

ታድያ በርከት ያሉ ለየት ያሉ ሁነቶችን እያስመለከተን የሚገኘው የዘንድሮው የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ አራተኛዋ አስተናጋጅ ከተማ የሆነችው ድሬዳዋ ከተማ በአካባቢው ከሚስተዋለው ከፍ ያለ ሙቀት ጋር በተያያዘ ጨዋታዎችን አመሻሹን እንዲካሄዱ በተወሰነው መሠረት በሀገራችን ባልተለመዱ መልኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በምሽት አንድ ሰዓት ጨዋታዎችን እያካሄደች ትገኛለች።

በተሰረዘው የውድድር ዘመን የአዲስአበባ ከተማ ክለቦች በፕሪምየር ሊጉ ቁጥራቸው መመናመኑን ተከትሎ በአዲስ አበባ የሚደረጉ ጨዋታዎች በአመዛኙ ወደ 9 ሰዓት በመገፋታቸው በተወሰነ መልኩ አመሻሹን የሚደረጉ ጨዋታዎችን የመመልከት ዕድላችን እጅጉን የጠበበ የነበረ ቢሆንም ዘንድሮ ከአዲስአበባ እና ወልዲያ ቀጥሎ ድሬዳዋ ሦስተኛዋ የምሽት ጨዋታን ማስተናገድ የቻለች ከተማ መሆን ችላለች።

👉 ብዙ ያልተነገረለት አስደናቂ ርብርብ

የድሬዳዋ ስታዲየም የምሽት ጨዋታዎች ለማስተናገድ ይረዳው ዘንድ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የመብራት ገጠማ እንደተደረገለት ይታወሳል። ምንም እንኳን ዘግይቶ ቢሆንም የተገጠሙትን መብራቶች በማሻሻል የLED መብራቶችን ለመግጠም ሥራዎች የተጀመሩት ባሳለፍነው ረቡዕ ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት የLED መብራቶች ገጠማ ስራው ሰኞ ዕለት አንስቶ መከናወን ቢጀምርም ከነበረው የጊዜ መጣበብ አንፃር መብራቶቹን ለጨዋታዎች በታቀደው ጊዜ ለማድረስ ግን በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል።

ረቡዕ ምሽት የነበረው የኢትዮጵያ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ ጨዋታ የሚቀሩ ሥራዎች በወቅቱ መጠናቀቅ ባለመቻላቸው የቀጥታ ሽፋን ማግኘት ባይችልም ቀሪ ሥራዎቹ ተጠናቀው የቀጣዩ የጨዋታ ዕለት የምሽት ጨዋታ የቀጥታ ሽፋን እንዲያገኝ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በኩል ቀን ከሌሊት የተደረገው ርብርብ ከፍተኛ አድናቆት የሚቸረው ነው።

በተለይም ከዚህ የስታድየም መብራት ጀርባ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱት የናሽናል ሲሚንቶ አክሲዮን ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት ብዙአየሁ ታደለ (ዶ/ር) እንዲሁም በዚህ ስራ ላይ ለተሳተፉ አካላት ሁሉ ላቅ ያለ ምስጋና ይገባቸዋል።

👉የቡድኖች የጊዜ አጠቃቀም

የዘንድሮው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር የቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን ማግኘቱ ጋር በተያያዘ በቅድመ ጨዋታ ወቅት ሆነ በጨዋታዎች አጋማሽ ላይ በቡድኖች ሆነ በሌሎች አካላት የሚባክኑ ሽርፍራፊ ሰከንዶችም ቢሆኑ የሚያደርሱት ኪሳራ በቀላል የሚታይ አይደለም።

እንደሚታወቀው በሀገራችን እግርኳስ ውስጥ ደግሞ እጅግ ደካማ የሆነ የጊዜ አረዳድ እና አጠቃቀም መኖሩ አይዘነጋም። ይህ አስተሳሰብ ከዚህ ቀደም የባህርዳሩ ውድድር በመክፈቻ ዕለቱ እንዳስተናገደው በድሬዳዋው ውድድር የመክፈቻ ዕለትም የተወሰኑ መጠዳደፎች መኖራቸውን ታዝበናል።

ጅማ አባጅፋር ከድሬዳዋ ከተማ ባደረጉት ጨዋታ የቡድኖች ተሰላፊዎች ዝርዝር ለመገናኛ ብዙሃን አባላት የደረሰው እጅጉን ዘግይቶ ነበር። በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ቡና እና ሀዋሳ ጨዋታ ላይ ይህን ሂደት የተመለከትን ሲሆን በትላንቱ የማሳረጊያ መርሃግብር ሲዳማ ቡና ከአዳማ ከተማ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ጭምር የቡድኖቹ የሁለተኛ አጋማሽ ጨዋታ ከተያዘለት ሰዓት ለአራት ያክል ደቂቃዎች ዘግይቶ ለመጀመር በቅቷል።

በተለይ የድሬዳዋ ከተማው ውድድር በሁለቱ የጨዋታ መርሐግብሮች መካከል ያለው የሰዓት ልዩነት እጅግ ጠባብ ከመሆኑ አንፃር ክለቦች ይህን በመረዳት ዝግጅታቸውን ከዚህ ሂደት አንፃር መቃኘት ይጠበቅባቸዋል።

👉በከተማ አውቶቢስ ሜዳ የደረሱት ጅማዎች

ጅማ አባ ጅፋር እንደ ክለብ ሜዳ ላይ ከሚያስመዘግበው ውጤት በበለጠ ከሜዳ ውጪ ባሉ ሁነቶች አሁንም ርዕሰ ዜና መፍጠሩን ቀጥሏል።

ከዚህ ቀደም ሊግ በጅማ ከተማ በነበረው ቆይታ የቡድኑ ተጫዋቾች ወደ ጨዋታው ሜዳ በኪራይ በቀረበ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ አውቶብስ ወደ ሜዳ የመጣው ቡድኑ አሁን ደግም ድሬዳዋ ላይ በድሬዳዋ ከተማ የህዝብ ትራንስፖርት በሚሰጥ የከተማ አውቶብስ ወደ ስታድየም የመጡበት ሂደት በሳምንቱ ትኩረትን የሳበ ጉዳይ ነበር።

የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊዎቹ ጅማ አባጅፋሮች ለተጫዋቾች እና የቡድን አባላት ደመወዝ ለመክፈል መቸገር ፣ የተጫዋቾች ልምምድ ማቆም አሁን ደግሞ የትራንስፖርት አቅርቦት ችግር መገለጫቸው እየሆነ መጥቷል።

👉”እኔ የሰላም አምባሳደር ነኝ”

ድሬዳዋ ከተማ ከጅማ አባጅፋር ጋር ካደረጉት ጨዋታ መጀመር በፊት ኢንተርናሽናል አልቢትር ሊዲያ ታፈሰ ከተጋጣሚ ተጫዋቾች ጋር በመሆን “እኔ የሰላም አምባሳደር ነኝ” የሚል መልዕክትን ስትስተላልፍ ተደምጣለች። ይሂ ሁነት በወላይታ ድቻ እና ፋሲል ከነማ ጨዋታ ላይም ሲተገበር ተመልክተናል።

አሁን ላይ እግርኳሱ ካለው ተደራሽነት አንፃር መሰል ማህበራዊ ሀሳቦች አሰልቺ ባልሆነ መልኩ መነሳታቸው ከሚኖረው የጎላ ፋይዳ አንፃር ይህ ተግባት ሊለመድ የሚገባው ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ