ከቡድኖቹ የጨዋታ አቀራረብ አንፃር ተጠባቂ የነበረው የሰበታ እና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና 2-1 አሸናፊነት ተገባዷል።
በ17ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አቻ የተለያዩት ሰበታዎች በዛሬው ጨዋታ ፉዓድ ፈረጃ እና ያሬድ ሀሰንን ቋሚ በማድረግ መስዑድ መሀመድ እና ኃይለሚካኤል አደፍርስን አሳርፈዋል። በሀዋሳ ከተማ ከደረሰባቸው ሽንፈት ለማገገም ወደ ሜዳ የገቡት ኢትዮጵያ ቡናዎ በበኩላቸው ወንድሜነህ ደረጄ፣ እያሱ ታምሩ፣ ሬድዋን ናስር እና አቤል ከበደን በማሳረፍ ሀብታሙ ታደሰ፣ የአብቃል ፈረጃ፣ አማኑኤል ዩሃንስ እና ምንተስኖት ከበደን ወደ አሰላለፍ በማምጣት ጨዋታውን ጀምረዋል።
ቀዝቀዝ ባለ እንቅስቃሴ ታጅቦ የጀመረው ይህ ጨዋታ ቀስ በቀስ ጥሩ ጥሩ ሙከራዎችን ማስተናደግ ይዟል። በተለይም ኢትዮጵያ ቡናዎች በተሻለ ኳስን ተቆጣጥረው በመጫወት ተጋጣሚያቸው ላይ ጥቃት መሰንዘር ጀምረዋል። በዚህም በ7ኛው ደቂቃ አስራት ቱንጆ ከግራ መስመር ወደ ሳጥን የላከውን ኳስ አቡበከር ከተከላካዮች ጋር ታግሎ በማግኘት ከጠበበ አንግል ወደ ግብነት ቀይሮታል። የቡድኑ አምበል 21ኛ የሊግ ግቡን ካስቆጠረ ከስድስት ደቂቃዎች በኋላም ሌላ ምርጥ አጋጣሚ ፈጥሮ ነበር። በዚህም ተጫዋቹ ከመሐል የተሰነጠቀለትን ኳስ የግብ ክልሉን ለቆ የወጣውን ምንተስኖት ካታለለ በኋላ ወደ ግብ ቢመታውም የግቡን ቋሚ ገጭቶ ወደ ውጪ ወጥቶበታል። ገና ከጅምሩ ጫናዎች የበረታባቸው ሰበታዎ በድፍረት የግብ ክልላቸውን ለቀው ለማጥቃት ቢሹም ውጥናቸው እምብዛም ሳይሰምር ቀርቷል። ይልቁንም በዚህ አጨዋወት በጎ ነገሮችን ለራሳቸው ሲያመጡ የታዩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ናቸው። በተለይም ቡድኑ ከተከላካይ ጀርባ የሚገኙ ቦታዎችች በፍጥነት ለማጥቃት ሲታትር ተስተውሏል።
ከ20ኛው ደቂቃ በኋላ በጣለው ዝናብ ታጅቦ የቀጠለው ጨዋታው ኢትዮጵያ ቡናን የእንቅስቃሴ የበላይ አድርጓል። ቡድኑም ዊልያም እና ሚኪያስ ባገኟቸው ተከታታይ የሳጥን ውስጥ ኳሶች ተጠቅሞ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ቢጥርም አንተነህ እና ምንተስኖት የተጫዋቾቹን ሙከራ አምክነዋል። ገና በጊዜ መመራት የጀመሩት ሰበታዎች ኢትዮጵያ ቡና የግብ ክልል ደርሰው የመጀመሪያውን አስደንጋጭ ሙከራ ያደረጉት በ31ኛው ደቂቃ ነው። በዚህ ደቂቃም ፈጣኑ አጥቂ ኦሴ ማውሊ ከግራ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ግብ ለማስቆጠር ታትሮ ነበር። የነበራቸውን የጨዋታ ብልጫ በሰፊ ጎል ማስቀጠል ያለሙት ቡናዎች በ41ኛው ደቂቃ አስራት የምንተስኖትን በቦታው አለመገኘት ተመልክቶ በመታው ጥብቅ ኳስ ግብ ፍለጋቸውን ቀጥለዋል። ይህ ሙከራ ከተደረገ ከደቂቃ በኋላ በፈጣን እና በረጅሙ በተላከ ኳስ የኢትዮጵያ ቡና የግብ ክልል የደረሱት ሰበታዎች ወደ ጨዋታው የሚመለሱበትን ጎል በፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። በዚህም ተከላካዩ ምንተስኖት ፍፁም ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ፎዓድ ፈረጃ ወደ ግብነት ቀይሮታል። ጎል 45ኛው ደቂቃ ላይ ከተቆጠረ በኋላም የመጀመሪያው አጋማሽ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተገባዷል።
የሁለተኛው አጋማሽ ተጀምሮ ገና አንድ ደቂቃ ሳይሞላው ወደ ሰበታ የግብ ክልል ያመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ታፈሰ ለአቡበከር አቀብሎት አቡበከር መረብ ላይ ባሳረፈው ኳስ ዳግም መሪ ሆነዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው አቻ የሆኑበትን ጎል አስቆጥረው የነበረው ነገርግን ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በአንደኛው ደቂቃ ግብ ያስተናገዱት ሰበታዎች በአጋማሹ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ የእንቅስቃሴ እድገት አሳይተው ነበር። ግብ ካስተናገዱ ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም ኦሴ ማውሊ ከሳጥን ውጪ በመታው ኳስ ዳግም ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረዋል።
ሲያጠቁ አስፈሪ ሆነው እየተጫወቱ የነበሩት ቡናዎች በ58ኛው ደቂቃ ሦስተኛ ጎል የሚያስቆጥሩበትን እጅግ ጥሩ ዕድል አግኝተው ነበር። በዚህ ደቂቃም አስራት በተከላካዮች መሐል ለአቡበከር ጥሩ ኳስ አቀብሎት አቡበከር ወደ ጎል ቢመታውም የግቡ አግዳሚ ለሁለተኛ ጊዜ መልሶበታል። በድጋሜም ተጫዋቹ በ63ኛው ደቂቃ የራሱን እንዲሁም የቡድኑን ሦስተኛ ጎል የሚያስቆጥርበትን ኳስ ከሚኪያስ አግኝቶ የነበረ ቢሆንም የሰበታ ተከላካዮች በቶሎ ተረባርበው አውጥተውበታል። የጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ የመጨረሻ ሀይላቸውን በመጠቀም ከየአቅጣጫው ጥቃት መሰንዘር የያዙት ሰበታዎች በአመዛኙ ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም ግብ ለማስቆጠር ታትረዋል። በተለይም በ82ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ቢያድግልኝ ኤልያስ በግንባሩ የሞከረው ኳስ ለግብ ቀርበዋል። ከዚህ ሙከራ በተጨማሪም በ84ኛው ደቂቃ ማውሊ እንዲሁም በ85ኛው ደቂቃ ዳዊት በሞከሯቸው ኳሶች ቡናን አስደንግጠዋል። ምንም እንኳን ቡድኑ ከጨዋታው አንድ ነጥብ ይዞ ለመውጣት ቢጥርም ሳይሳካለት ጨዋታው ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎም በጨዋታው ሦስት ነጥብ ያስረከቡት ሰበታዎች በሰበሰቧቸው 19 ነጥቦች ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በተቃራኒው በአቡበከር ሁለት ጎሎች ድል ያደረጉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ነጥባቸውን 33 በማድረግ ሁለተኛ ደረጃን አጠናክረው ይዘዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ