በሀድያ ሆሳዕና አመራሮች እና ተጫዋቾች መካከል በደሞዝ አከፋፋል ዙርያ የተካሄደው ውይይት ያለ ስምምነት ተጠናቋል።
ሀድያ ሆሳዕና በታሪኩ በሊጉ ከተሳተፈባቸው ጊዜያት አስመዝግቦ የማያቀውን ውጤት ዘንድሮ በተሻለ ሁኔታ እያሳካ ቢሆንም ከቡድኑ በስተጀርባ ያለው የአስተዳደር ችግር በጥንካሬ እንዳይዘልቅ እየተፈታተነው ይገኛል። እስካሁን ባለው የቤትኪንግ ፕሪምየርሊግ የሦስት ምዕራፍ ጉዞ በአዲስ አበባ፣ ጅማ እንዲሁም ባህር ዳር ውድድሮች ተጫዋቾች ደሞዝ አልተከፈለንም በሚል ልምምድ እያቋረጡ ዳግም እየተመለሱ ሁኔታው ለተጫዋቾችም ለሰሚውም አሰልቺ ሆኖ ቆይቷል። ዛሬም እንደወትሮ ወደ ድሬዳዋ ከማቅናታቸው አስቀድሞ በባቱ ከተማ ለቀናት ሲዘጋጁ የቆዩት ተጫዋቾቹ “ተደጋጋሚ የደሞዝ ጥያቄያችን አልተፈታም” በሚል ከክለቡ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ባረፉበት ሆቴል ሰፊ ውይይት ቢያደርጉም ሳይስማሙ መለያየታቸው ታውቋል።
ይህ አለመስማማት መጨረሻው ወዴት ያመራል የሚለውን መገመት ባይቻልም የክለቡ አመራሮች ነገ በድጋሚ ችግሩን ለመቅረፍ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ተጫዋቾቹን አሳምነው የፊታችን ማክሰኞ ምሽት ላይ ከአዳማ ከተማ ጋር ላለው ጨዋታ እንዲጓዙ ለማድረግ እንደታሰበ የሰማን ሲሆን በተጫዋቾቹ በኩል ደግሞ “የጠየቅነው ጥያቄ እስካልተመለሰ ድረስ ምንም አይነት የአቋም ለውጥ አናደርግም” በማለት እየገለፁ ይገኛል።
በአሰልቺነቱ የዘለቀው የሀድያ ሆሳዕና አመራር እና የተጫዋቾች ጉዳይ መቼ መቋጫ እንደሚያገኝ እንዲሁም በቀጣይ ከአዳማ ከተማ ጋር የሚያርገው ጨዋታን በምን መልኩ ያስኬደዋል የሚለው ተጠባቂ ጉዳይ ይሆናል።
© ሶከር ኢትዮጵያ