የአሠልጣኞች አስተያየት | ሰበታ ከተማ 1-2 ኢትዮጵያ ቡና

ከሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ሱፐር ስፖርት ከአሠልጣኞች የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ተቀብሏል።

ካሣዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

ቡድኑ የመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ ግብ አስተናግዶ ከወጣ በኋላ መልበሻ ክፍል ስለነበረው ምክክር?

በዋናነት ሰበታዎች እየመጡበት ያለውን መንገድ እንዴት መቋቋም አለብን በሚለው ላይ ነው ስንነጋገር የነበረው። በተለይም እኛ የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ ይመጡ ነበር። ከዚህም መነሻነት እኛ የግብ ክልል ሲመጡ የሚተውልን ቦታ ነበር። ስለዚህም ይህንን ቦታ እናግኘው ነበር ስንባባል የነበረው።

የዛሬው ድል ለሀዋሳ ከተማው ሽንፈት ምላሽ ነው?

ማሸነፋችን ጥሩ ነው። ግን ጨዋታውን የተቆጣጠርንበት ሁኔታ ጥሩ አልነበረም። እኔ ጥሩ ነው የምለው እና ለቡድኑም ቀጣይነት መልካም የሚሆነው ጨዋታውን ተቆጣጥረን ብናሸንፍ ነው። ከዕረፍት መልስ መምራት ከጀመርን በኋላ ሰበታዎች በጥሩሁኔታ ጨዋታውን ተቆጣጥረውት ነበር። ግን ጎል ማግባት ስለፈለጉ ቸኩለው ነበር። ከውጤት አንፃር ጥሩ ነው ግን ከእንቅስቃሴው አንፃር መስተካከል ያለበት ነገር አለ።

አብርሃም መብራቱ – ሰበታ ከተማ

ሁለተኛው ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ ሜዳ ላይ ስለነበረው እንቅስቃሴ?

ከዕረፍት ስንመለስ በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ላይ ጥንቃቄ እንድናደርግ ለተጫዋቾቹ ነግሬያቸው ነበር። ግን እንደተመለከታችሁት ሁለቱም ጎሎች ሲቆጠሩብን በተከላካዮቻችን የትኩረት ማነስ ነው። ከዚህ ውጪ በሁለተኛው አጋማሽ ተጭነን ለመጫወት ሞክረናል። በእነሱ ሜዳም ውለናል። ነገር ግን አሁንም እንደ በፊቱ የአጨራረስ ችግራችን ሳይቀረፍ ቀርቶ 2-1 ተሸንፈን ወጥተናል። አንዳንዴ ጥሩ ተጫውተህም ተሸንፈህ ልትወጣ ትችላለህ። ያለው አማራጭ በፀጋ መቀበል እና ለቀጣዩ መዘጋጀት ነው።

ቡድኑ ከኋላ ሲተወው ስለነበረው ሰፊ ቦታ?

እኛ ሙሉ ለሙሉ ተጭነን ለመጫወት ነበር አስበን የነበረው። ሁለታችንም ኳስ ተቆጣጥረን ነበር የምንጫወተው። አልፎ አልፎ ግን ግራ እና ቀኝ የነበረውን ቦታ ሲጠቀሙ ነበር። ይህም ቢሆን ግን ያን ያህል ውጤታማ አልነበሩም። ውጤታማ የነበሩት በመጀመሪያው አጋማሽ እና በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ነው። ግን ኋላ ላይ የምንተወውን ቦታ አልተጠቀሙባቸውም። አለመጠቀማቸው ደግሞ እኛ ተጭነን እንድንጫወት ጠቅሞናል። ግን እንዳልኩት ሁለተኛው አጋማሽ እንደነበረን ብልጫ ውጤታማ አልሆንም። ይህንን እናስተካክላለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ