ሪፖርት | ሀዋሳ እና ጅማ ነጥብ ተጋርተዋል

በሀዋሳ ከተማ እና ጅማ አባጅፋር መካከል የተደረገው የምሽቱ ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ በተቆጠሩ ሁለት ጎሎች አንድ አቻ ተጠናቋል።

በ17ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ ቡናን የረቱት ሀዋሳ ከተማዎች ድል ካደረጉበት ጨዋታ ሁለት የተጫዋች ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ላውረንስ ላርቴ እና ኤፍሬም ዘካሪያስን በፀጋአብ ዮሃንስ እና አለልኝ አዘነ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በተቃራኒው በአሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም የሚመራው እና ድል የናፈቀው ጅማ አባጅፋር በድሬዳዋ ከተረታበት ቋሚ አሰላለፍ አንድ ተጫዋች ብቻ ለውጦ ጨዋታውን ጀምሯል። በዚህም ዋለልኝ ገብሬ አርፎ ሳዲቅ ሴቾ ተተክቷል።

ቀዝቀዝ ባለ እንቅስቃሴ የጀመረው ጨዋታው የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ያስተናገደው በ7ኛው ደቂቃ ነው። በዚህ ደቂቃም ሀዋሳ ከተማዎች ወንድማገኝ ኃይሉ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት አለልኝ አዘነ ወደ ጎል ቢመታውም ኳስ እና መረብ ሳይገናኝ ቀርቷል። በጀብደኝነት የጨዋታውን የመጀመሪያ ደቂቃዎች እየተጫወቱ የነበሩት ሀዋሳዎች ከደቂቃ በኋላም ሌላ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሰንዝረዋል። ለቅጣት ምቱ መገኘት ቀጥተኛ ምክንያት የሆነው ወንድማገኝም ከዳንኤል ደርቤ የተሻገረለት ኳስ ወደ ግብ ለመቀየር ቢጥርም የግብ ዘቡ አቡበከር ኑሩ በጥሩ ቅልጥፍና አምክኖበታል።

ሙሉ ለሙሉ በመከላከሉ ላይ ተጠምደው ያመሹት ጅማዎች ብቸኛውን አጥቂያቸው ራሂም ኦስማኖን ዒላማ ያደረጉ ረጃጅም ኳሶች እና ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች ላይ ብቻ በመንተራስ ግብ ለማስቆጠር ሲዳዱ ተስተውሏል። ቡድኑ ይህንን የጨዋታ መንገድ ቢከተልም በተለይ በማጥቃቱ ረገድ ውጤታማ መሆን ሳይችል ጨዋታው ቀጥሏል።

በጨዋታው ከፍተኛ የበላይነት የነበራቸው ሀዋሳዎች ብልጫቸውን በጎል ለማጀብ ቢፈልጉም የጅማው ግብ ጠባቂ አቡበከር ሊቀመስላቸው አልቻለም። በተለይም በ30ኛው ደቂቃ የአሌክስ አሙዙን ስህተት ተጠቅመው በብሩክ እንዲሁም በ32ኛው ደቂቃ አለልኝ ከርቀት በሞከረው ኳስ ጥቃት ቢፈፅሙም አቡበከር ኳሶቹን አምክኗቸዋል። ከእነዚህ ሙከራዎች በተጨማሪም አለልኝ በ39ኛው ደቂቃ ሌላ የቅጣት ምት ኳስ ወደ ግብ ቢመታም ጥሩ ጊዜን እያሳለፈ የነበረው አቡበከር ዕድሉን አክሽፎታል። እንደ ተመራ ቡድን በከፍተኛ ፍላጎት ከየአቅጣጫው ጥቃት መሰንዘሩን አጠናክሮ የቀጠለው ሀዋሳ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በተጨመረው ደቂቃ መሪ ሆኖ ወደ መልበሻ ክፍል የሚያመራበትን ዕድል በብርሃኑ በቀለ አማካኝነት አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። የመጀመሪያው አጋማሽም ፍፁም የሀዋሳ ከተማ ብልጫ ታይቶበት ነገርግን ግብ ሳይስተናገድበት ተገባዷል።

የሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በ20ኛው ሰከንድ በመጀመሪያው አጋማሽ ምንም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ያላደረጉት ጅማ አባጅፋሮች ሳይጠበቅ መሪ የሆኑበትን ጎል አስቆጥረዋል። በዚህም ሳዲቅ ሴቾ ከኦስማኖ የደረሰውን ኳስ ለተመስገን ደረሰ አመቻችቶለት ተመስገን ጎል አስቆጥሯል። ግቡ ከተቆጠረ ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም ግዙፉ አጥቂ ኦስማኖ ከሳጥን ውጪ ሌላ ጥቃት ፈፅሞ ሁለተኛ ጎል ለማከል ጥሮ ነበር። እጅግ ድንቅ አጀማመር በዚህኛው አጋማሽ ያደረጉት ጅማዎች ከደቂቃ በኋላም መሪነታቸውን ወደ ሁለት የሚያሳድጉበትን ሌላ ድንቅ ዕድል በተመስገን አማካኝነት ፈጥረው ነበር።

በመጀመሪያው አጋማሽ የነበራቸውን የጨዋታ የበላይነት በዚህኛው ግማሽ ያጡት ሀዋሳዎች ጅማዎች ለሚፈፅሙባቸው ጥቃቶች ምላሽ ለመስጠት ተስኗቸው ጨዋታው ቀጥሏል። በአጋማሹም የመጀመሪያ ወደ ግብ የቀረቡበትን ዕድል በ75ኛው ደቂቃ አግኝተዋል። በዚህም ውብሸት ጥፋት ሰርቶ የተገኘው የቅጣት ምት ሲሻማ ቁመተ መለሎው አለልኝ ወደ ግብ ቢሞክረውም ኳስ ዒላማዋን ስታ ወጥታለች። በተጨማሪም በ87ኛው ደቂቃ በተገኘ የመዓዘን ምት ቡድኑ ግብ ለማስቆጠር ሞክሮ ነበር። ተስፋ ሳይቆርጥ እስከ መጨረሻው መታተሩን የቀጠለው ቡድኑ በ90ኛው ደቂቃ የልፋቱን ውጤት አግኝቷል። በዚህ ደቂቃም ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ዓባይነህ ፌኖ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። ጨዋታውም አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

በመጨረሻ ደቂቃ የአቻነት ጎል ያገኙት ሀዋሳዎች ነጥባቸውን 21 በማድረስ ደረጃቸውን ወደ 6 አሳድገዋል። በተቃራኒው የዓመቱ ሦስተኛ ድላቸውን ለማግኘት ተቃርበው የነበሩት ጅማዎች ነጥባቸው 11 ደርሶ እዛው ባሉበት 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ