የነገውን ሁለተኛ መርሐ-ግብር የተመለከቱ ነጥቦችን እንዲህ አንስተናል።
በወልቂጤ የበላይነት በመሀከላቸው የስድስት ነጥብ እና የአራት ደረጃዎች ልዩነት ይኑር እንጂ የድሬዳዋ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች ሲደረጉ ሲዳማ በድል ወልቂጤ ደግሞ በሽንፈት ነበር ያሳለፉት። ከሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥብ አሳክተው የነበሩት ወልቂጤዎች በባህር ዳሩ ጨዋታውም መልካም እንቅስቃሴ ማሳየታቸው ባይቀርም በሰሯቸው ስህተቶች የተሸነፉ በመሆኑ በዚህ ጨዋታ በቶሎ ለማገገም ሜዳ ይገባሉ። በተቃራኒው ከአምስት ተከታቶታይ ሽንፈቶች በኋላ ድል የቀናቸው ሲዳማ ቡናዎች ቀድሟቸው የሚጫወተው ድሬዳዋ ከተማን ውጤት አይተው ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት የነገው ፍልሚያ እጅግ አስፈላጊያቸው ይሆናል።
የአሰልጣኝ ደግ አረገ ይግዛው ወልቂጤ ከተማ ኳስን ተቆጣጥሮ ተጋጣሚን ወደ ፊት ገፍቶ የመጫወት ጥንካሬው አሁንም አብሮት እንዳለ ነው። ነገር ግን በሁለቱም ሳጥኖች ውስጥ (በመጨረሻ ማጥቃት እና የግብ ክልሉን በመከላከል) ረገድ ድክመቶቹ ዋጋ እያስከፈሉት ይገኛሉ። በተለይም አሁን አሁን የመጨረሻ ዕድሎችን ከመጨረስ በላይ በኋላ መስመሩ የሚሰራቸው የግለሰብ እና የዲፓርትመንርት ስህተቶች እጅጉን ሲጎዱት ይታያል። በነገውም ጨዋታ አስፈሪ የሦስትዮች የማጥቂት መስመር የፈጠረው ተጋጣሚውን ለመቋቋም ከስህተት ርቆ በተረጋጋ አደረጃጀት ውስጥ መቆየት የግድ ይለዋል። እንደቡድንም የተከላካይ መስመር ድክመቱን ለመሸፈን ታክቲካዊ ሽግሽጎችን ማድረግ በመከላከል ሽግግር ወቅት የአማካይ ክፍል ተሰላፊዎቹን እንዲሁም የማጣቃት ኃላፊነት ያላቸውን ተጫዋቾች ድርሻ ከፍ ማድረግ ከቡድኑ የሚጠበቅ ይሆናል።
ሲዳማ ቡና አዳማን በረታበት ጨዋታ ከድል ባለፈ በሰፊ ግብ የማሸነፍ እና መረቡን ሳያስደፍር የመውጣት ስኬቶችን ከረጅም ሳምንታት በኋላ ማስመዝገብ ችሏል። ይህን ማድረግ ያስቻሉትን ጠንካራ ጎኖች ከአዳማ የተሻለ ብቃት ላይ በሚገኙ ቡድኖች ላይ ማስቀጠልም የአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ቀጣዩ የቤት ሥራ ይመስላል። ቡድኑ የተሻለ መናበብ ያለው የኋላ ክፍል ጥምረት ያገኘ መሆኑ በሰንደይ ሙቱኩ አለመኖር ምክንያት ካልተከፈተ በቀር መልካም የሚባል ሲሆን አማካይ ክፍሉም ከቀጥተኛ ኳሶች በተጨማሪ ፈጠን ባሉ ቅብብሎች ኳስን ወደ ፊት በማድረሱ ረገድ ተስፋ ሰጪ ብቃት አሳይቷል። ከሁሉም በላይ ግን አጠቃላይ የቡድኑን መንፈስ የቀየረው ፊት መስመር ላይ የተፈጠረው ጥምረት አስፈሪነት ነው። የኦኪኪ አፎላቢ ወደ ቡድኑ መምጣት ከተጫዋቹ ከሚገኘው ቀጥተኛ ጥቅም በተጨማሪ ሀብታሙ ገዛኸኝ እና ማማዱ ሲዲቤንም ይበልጥ ያሻሻላቸው ይመስላል። ከነገ ተጋጣሚያቸው የመከላከል ክፍተት አንፃርም የሦስትዮሽ ጥምረቱ ዳግም ያንፀባርቅ እንደሆነ ከጨዋታው ይጠበቃል።
በነገው ጨዋታ የወልቂጤው ወሳኝ ተጫዋች አብዱልከሪም ወርቁ ገጥሞት ከነበረው መጠነኛ ግጭት ያገገመ ሲሆን አሳሪ አልመሀዲ ግን አሁንም ሙሉ ግልጋሎት መስጠት አይችልም። በሲዳማ ቡና በኩል ሰንደይ ሙቱኩ በአዳማ ከተማው ጨዋታ ላይ በተመለከተው የቀይ ካርድ የነገው ጨዋታ የሚያልፈው ሲሆን በቡድኑ ውስጥ ያለውን የጉዳት ዜና ለማጠናቀር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– በሁለቱ ቡድኖች መሀከል የመጀመሪያ የሊግ ግንኙነት ሆኖ በተመዘገበው የመጀመሪያ ጨዋታ ሲዳማ ቡና በዳዊት ተፈራ ብቸኛ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል አሸናፊ መሆን ችሏል።
* ወቅታዊው የኮቪድ ወረርሺኝ በቡድኖቹ የስብስብ ምርጫ ላይ እያሳደረ ካለው ተለዋዋጭነት አንፃር ግምታዊ አሰላለፍ ለማውጣት አዳጋች በመሆኑ የወትሮው የአሰላለፍ ትንበያችን በዳሰሳው ያልተካተተ መሆኑን እንገልፃለን።
© ሶከር ኢትዮጵያ