በድሬዳዋ እየተካሄደ የሚገኘው አራተኛው ዙር የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ የኮቪድ ምርመራ ውጤት አገላለፅ ጥያቄ እየተነሳበት ይገኛል።
መጋቢት ሀያ ዘጠኝ የጀመረው የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የድሬዳዋ ውድድር እስካሁን ባለው ሁኔታ ከሞላ ጎደል በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው ማለት ይቻላል። ሆኖም በድሬዳዋ የሚገኘው የኮቪድ ምርመራ ማዕከል የሚሰጣቸው የተጫዋቾች ውጤቶች የተዛቡ ናቸው በሚል ጥያቄ እየተነሳበት ይገኛል። እንደ ወላይታ ድቻ፣ ሲዳማ ቡና፣ ጅማ አባ ጅፋር እና አዳማ ከተማ ያሉ ክለቦችም ቅሬታቸውን በተለያየ መንገድ ሲገልፁ ታይተዋል።
በዚህ ዙርያ ሶከር ኢትዮጵያ ያነጋገረቻቸው የክለብ አመራሮች አንዱን ክለብ ጠቅሞ ሌላኛውን ለመጉዳት ኮቪድ የሌለባቸውን አለባቸው በማለት ያልተገባ ውጤት ለማግኘት እየተደረገ መሆኑን እና ይህንንም ለሊግ ካምፓኒውና ለእግርኳስ የበላይ አካል ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እንዳሳወቁ ነግረውናል።
ይህ ከላይ የተነሳው ጉዳይ ለእግርኳሱ እጅጉን አደገኛ መሆኑን በመገንዘብ የሊግ ካምፓኒው ሥራ አስኪያጅ ወደ ሆኑት አቶ ክፍሌ ሰይፉ ጋር ደውለን እየተባለ ስላለው ጉዳይ ምን ያል መረጃ አላችሁ? ችግሩንስ ለመቅረፍ ምን እየተሰራ ነው? ብለን ጠይቀናቸው ተከታዩን ምላሽ ሰጥተውናል።
” የኮቪድ ምርመራው ከሁለት ተቋም ነው እየመጣ የሚገኘው። አንደኛው ከድሬዳዋ ሌላኛው ከሀረር አለማያ ዩኒቨርስቲ ነው። በዚህም የተለያዩ ውጤቶች መጥተዋል። ስለዚህ እነዚህ ሁለት የተለያዩ ውጤቶችን የሚከታተል ከሀገር አቀፍ ከኢትዮጵያ ጤና ኢኒስቲትዩት ልዑክ ቡድን ነገ ድሬዳዋ ይገባል። በዚህም መሠረት ሁለት የተለያዩ ውጤቶች የሆኑበትን ምክንያት ቁጥጥር የሚያደርግ እና ትክክለኛው የቱ እንደሆነ የሚያሳውቅ ይሆናል።
” በውድድራችን ደንብ መሠረት ማንኛውም ክለብ የኮቪድ ምርመራ ለማድረግ ህጋዊ ፍቃድ ካገኙ ተቋማት ውጤት ይዞ እንዲመጣ መወዳደርም እንደሚችል ይገልፃል። ይህ በተለይ በአዲስ አበባ ክለቦች ከተለያዩ ተቋማት ህጋዊ የሆነ ውጤት ይዘው በመምጣት ሲወዳደሩ ቆይተዋል። ስለዚህ የሚባሉትን ነገሮች ለመመርመር እኛ ሙያውም ሆነ ስልጣን የለንም። የሚመለከተው አካል ነገ ይመጣል። ትክክለኛው ሥራ ምን እንደሆነ የሚያጣራው ይሆናል።”
© ሶከር ኢትዮጵያ