የከሰዓቱ ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ የቡድኖቹ አሰልጣኞች ከሱፐር ስፖርት ጋር ቆይታ አድርገዋል።
አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው – ወላይታ ድቻ
ለጋቶች ፓኖም ስለሰጡት ከአጥቂ ጀርባ የመጫወት ሚና
አንደኛው ተጫዋቹ ካለው ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶችን የመስጠት አቅም አንፃር ነው። ዋናው ነጥባችን የነበረው ግን ሥንታየሁ ከፊት አለ እሱ ከኋላ አለ። ሁለት ጥሩ ተክለሰውነት ያላቸውን ተጫዋቾች እዛ ጋር ማቆም ማለት በተቃራኒው ከፍተኛ መከላከል ነው። በዚህም አራት የተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾች እዛው እንዲቀሩ አድርገናል። ስናጠቃ እየተከላከልንም ነው የሚል ሀሳብ ስለያዝን ነው።
ከተጋጣሚ ተጫዋቾች ስህተት ስለመጠበቃቸው
አዎ የሆነው ያ ናው ማለት ይቻላል። በዕረፍት ሰዓት የተነጋገርነውም ያንን ነው። አንደኛ ጎሉን ካገባን በኋላ እንዳገባ ቡድን አልነበርንም። ጨዋታውን መቼ ማፍጠን እና መቼ ማቀዝቅዝ እንዳለብን ትንሽ አልተረዳነውም። ከውሀ ዕረፍቱ በፊት እነሱ ተጭነው እያጠቁ ነበር። እኛ አፈግፍገን ስለነበር ኳስ ቶሎ እየነጠቁ ያጠቁ ነበር። ስለዚህ ወደ ፊት ተጭነን ለመጫወት ተነጋገርን እና ያ ነገር ነው የጠቀመን። በመልሶ ማጥቃት የመሄድ ፍላጎት ስለነበራቸው ክፍተቱ ነበር። በረከት ሲያስቆጥር ግን ክፍት ነበር።
አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ – ድሬዳዋ ከተማ
የትኛው ጎል ይበልጥ እንዳቀዘቀዛቸው
ሁለተኛው ኳስ ተንሸራተን በራሳችን ስህተት ነው ፍፁም ቅጣት ምት የሆነው። እንዳጠቃላይ ግን ኳስ ተቆጣጥረን ለመጫወት ሞክረናል ፤ ተጭነን ለመጫወት ሞክረናል አንዳንድ ጊዜ እግርካስ እንዲህ ዓይነት ባህሪ አለው። ስለዚህ መቀበል ነው። ቡድኑ ላይ ከፍተኛ መሻሻል ይታየኛል ፤ ይሄ ጥሩ ነው። በዚህ ሁኔታ ከቀጠልን በቀጣይ ጨዋታዎች አሸንፈን የምንፈልገውን ደረጃ ላይ መድረስ እንችላለን ብዬ አምናለሁ።
የማጥቃት ሂደተታቸው ስለመቆራረጡ
ተቃራኒ ቡድን ኳስ ይዞ አይጫወትም ፤ ረጃጅም ኳስ ስለሚጫወት እኛ ደግሞ ደግሞ ኳሱን ይዘን ቶሎ ቶሎ እየቆረጥን ለመውጣት እንሞክር ነበር። ጨዋታውን ሙሉ ለሙሉ የቀየረችው ሁለተኛዋ በእጅ የተነካችው ኳስ ናት። በአጠቃላይ ግን ቡድኑ ባደረገው እንቅስቃሴ ደስተኛ ነኝ። መሻሻሎች ስላሉ በቀጣይ ጨዋታዎች ቶሎ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ እንጥራለን።
ስለጁኒያስ ናንጄቦ በተከታታይ ጨዋታዎች በግብ ብረት የተመለሱ ኳሶች
ዝቅ አድርጎ መምታት ነው ያለበት እንግዲህ ምንም ማድረግ አይቻልም። የሊጉ ምርጥ አጥቂዎች መካከል አንዱ ነው ጁኒያስ ናንጄቦ ተደጋጋሚ እንዲህ አይነት ነገሮች ገጥመውታል። አጨራረስ ላይ መስራት ይጠበቅብናል።
© ሶከር ኢትዮጵያ