ከምሽቱ ጨዋታ በኋላ ተጋጣሚ አሰልጣኞች ለሱፐር ስፖርት የሰጡት አስተያየት ይህን መሳይ ነበር።
አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ – ሲዳማ ቡና
ውጤቱ ከነበሩበት ስሜት ያወጣቸው ስለመሆኑ
ከነበርንበት ስሜት ብቻ ሳይሆን ከአደጋውም የሚያወጣን ስለሆነ ለእኛ በጣም ትልቅ ትርጉም አለው። የነበርንበት ደረጃ ይታወቃል። አሁን ከወራጅ ቀጠናው ቢያንስ በአንድ ደረጃ ወጥተናል ማለት ነው። የመጀመሪያ የአሸናፊነት ስሜት ይዘን እሱን ማስቀጠል ራሱ በቀጣይ በተሻለ ሁኔታ እንድንቀርብ ይረዳናል። በራስ መተማመንም ይፈጥርልናል።
ቡድኑ ካሰቡት በፈጠነ ጊዜ ወደ ውህደት ስለመምጣቱ
አይባልም ፤ አዳዲስ ተጫዋቾችም አሉ ፤ ወደምንፈልገው ደረጃ ገብተናል ማለት አይቻልም። ማለት የሚቻለው ከተወሰኑ ጨዋታዎች በኋላ አይተህ ነው። በሁለት ጨዋታ የምንኮፈስበት ወይም ደግሞ ተስፋ የምንቆርጥበት አይደለም። ከዚህ በኋላ ገና ስምንት ጨዋታ ይቀረናል። በእነዚህ ጨዋታዎች ደረጃችንን እያሻሻልን መሄድ ይጠበቅብናል። ነገር ግን ይሄ የአሸናፊነት ስሜት እንዲቀጥል እና በራስ መተማመን ስሜታችን እንዲጨምር ያደርጋል። ስለዚህ ጥሩ ነው። ከዛ መንፈስ ወጥቶ ወደ ተሻለ ደረጃ እየተሸጋገርን ነው ማለት ይቻላል።
ስለመረጡት አጨዋወት
4-3-3 ነው የተጠቀምነው። ግን ሲስተም እንደእንቅስቃሴው ነው። መግቢያችን ላይም እንዳልኩትም በጥንቃቄ እንጫወታለን ነው። ምክንያቱም ባለፉት ጨዋታዎች ያጣናቸው ነጥቦች ነበሩ። ገና ባልተደራጀንበት ጊዜ ስለነበር። እነሱ ስህተቶች እንዳያጋጥሙን በጣም በጥንቃቄ ነበር ስንጫወት የነበረው። እና የመስመር ተጫዋቾቻችን ተመልሰው የሚከላከሉበት ዘዴ በጣም ጥሩ ነው። የሜዳው ሁኔታ እንደምታየው በምንፈልገው መልኩ ሊያስኬደን አልቻለም ፤ ዝናቡ የፈጠረው። ግን በዛም አለ በዚህ እኛ የምንፈልገውን ነገር አግኝተናል ማለት ይቻላል።
አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው – ወልቂጤ ከተማ
ስለቶማስ ስምረቱ ቀይ ካርድ ውሳኔ
የዳኝነት በደል በተከታታይ ነው እኛ ጋር የሚደርሰው ፤ የዛሬው ደግሞ ጭራሽ ዓይን ያወጣ ዳኝነት ነው የነበረው። አንደኛ ለእነሱ አላስፈላጊ የሆኑ የኃይል አጨዋወት ይፈቅዳል። ቶማስ ጭራሽ ቢጫ ካርድ ሊያይም አይገባውም ነበር። ግን ቢጫ ካርድ ሰጥቶ ቀይ አሳየ። ትንሽ ያማል ፤ እንደቡድንም ደግሞ ትልቅ ጉዳት አለው።
ስለውሳኔው ተፅዕኖ
ከፍተኛ ተፅዕኖ ነበረው። ጨዋታውን ተቆጣጥረን ለመጫወት ነበር የሞከርነው። ተጫዋቾቻችን ከዚህ ጨዋታ ሦስት ነጥብ ይዞ ለመውጣት በቁርጠኝነት ነበር የገቡት። ሜዳ ላይ የሚተገብሩበትም መንገድ በጣም ደስ የሚል ነበር። ሆኖም ግን ከኋላ መስመር የምንጠቀምበትን ተጫዋች ያለአግባብ ፍትህ በጎደለው ሁኔታ ነው ዳኛው ከሜዳ ያስወጣው። ይህ ደግሞ በተጨዋቾች ሥነልቦና ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ነው ያሳደረው። ሜዳው ጭቃ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ትልቅ ጉልበት ይጠይቃል። በጎዶሎ ስንጫወት ደግሞ በጣም ፈታኝ ነው የነበረው።
ስለአብዱልከሪም ቀዳሚ ተሰላፊ አለመሆን
ባለፈው ጨዋታ ላይ የቁርጭምጭሚት ጉዳት አስተናግዶ ነበር። ለዛሬው ጨዋታ ሰፊ ጊዜ ስላላገኘ ተገቢውን ዕረፍት አድርጎ ለቀጣይ ጨዋታዎች እንዲደርስ በማሰብ ነው።
በአማካይ እና በማጥቃት መስመሩ መሀል ክፍተት ስለመኖሩ
ክፍተት አለው ብዬ አላምንም። ሆኖም ግን በማጥቃት እንቅስቃሴው ላይ እየተወረወሩ እንዲገቡ ነበር ጥረት እያረግን የነበረው። ምን አልባት ትልቁ ጎዶሎ የነበረው የተጫዋቹ በቀይ ካርድ መውጣት አጠቃላይ የጨዋታውን ቅርፅ ቀይሮታል።
© ሶከር ኢትዮጵያ