ሪፖርት | ሁለት ግቦች የተቆጠሩበት ጨዋታ በአቻ ውጤት ተገባዷል

በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጅማ አባጅፋር መካከል የተደረገው ጨዋታ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

በሸገር ደርቢ ኢትዮጵያ ቡናን ረተው ለዚህኛው ጨዋታ የቀረቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሦስት ነጥብ ባገኙበት ጨዋታ የተጠቀሙትን ቋሚ አሰላለፍ በድጋሜ በመጠቀም ወደ ሜዳ ገብተዋል። ጅማ አባ ጅፋሮች ደግሞ በሰበታ ከተማ ከተረቱበት ጨዋታ አራት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም ከድር ኸይረዲን፣ አማኑኤል ተሾመ፣ ሱራፌል ዐወል እና ሳዲቅ ሴቾን ከጉዳት በተመለሰው መላኩ ወልዴ፣ ዋለልኝ ገብሬ፣ ሀብታሙ ንጉሴ እና ለመጀመሪያ ጊዜ በቀዳሚው አሰላለፍ ውስጥ በተካተተው ዋንጎ ፕሪንስ ተክተዋል።

በቶሎ ግብ አስቆጥረው የተጋጣሚያቸውን ጊዜ ፈተና ላይ መጣል የፈለጉት ፈረሰኞቹ ገና በጊዜ ጅማ የግብ ክልል ደርሰው ነበር። በዘጠነኛው ደቂቃም ውጥናቸው በቶሎ ሰምሮ የመጀመሪያ ጎል አስቆጥረዋል። በዚህ ደቂቃም የተገኘውን የመዓዘን ምት ጋዲስ መብራቴ አሻምቶት የቡድኑ አምበል ጌታነህ ከበደ በግንባሩ ወደ ግብነት ቀይሮታል። ለተቆጠረባቸው ጎል ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ያሰቡ የሚመስሉት ጅማዎች ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ በራሂም ኦስማኖ አማካኝነት አቻ ለመሆን ቢጥሩም የጊዮርጊስ ተከላካዮች ውጥናቸውን አክሽፈውባቸዋል። በ13ኛው ደቂቃም በቀኝ መስመር ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል ደርሰው ባሻገሩት እና ግዙፉ አጥቂ ኦስማኖ በግንባሩ ሞክሮት ለጥቂት ዒላማውን በሳተበት ኳስ ሌላ ጥቃት ፈፅመዋል።

ግብ ካስተናገዱ በኋላ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቁጥጥር ስር የነበረውን ብልጫ ወደ ራሳቸው በማድረግ መንቀሳቀስ የቀጠሉት ጅማዎች በ20ኛው ደቂቃም ወደ ግብ ቀርበው ነበር። በዚህም ኤልያስ አታሮ ከቅጣት ምት የተሻገረን ኳስ በመቆጣጠር ወደ ሳጥን ቢልከውም በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረ ተጫዋች ባለመኖሩ ወርቃማው ዕድል መክኗል። የጊዮርጊስ ተከላካዮች የራስ ምታት ሆኖ ያመሸው ኦስማኖ በ32ኛው ደቂቃ እጅግ ጥብቅ ኳስ ወደ ግብ መትቶ ነበር። ነገርግን ኦስማኖ ከተመስገን ደረሰ የተቀበለውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ቢመታውም የግብ ዘቡ ባህሩ ነጋሽ በጥሩ ቅልጥፍና ኳሱን አውጥቶበታል። በተቃራኒው እንደ አጀማመራቸው መዝለቅ ያልቻሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች መሪነታቸውን ለማስጠበቅ በሚመስል መልኩ ለመከላከል ቅድሚያ በመስጠት ሲጫወቱ ታይቷል። አልፎ አልፎም በፈጣን እንቅስቃሴዎች ጅማ የግብ ክልል ቢደርሱም ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር የሚያስችል ምንም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ አጋማሹን አገባደዋል። ጅማዎችም ግብ ካስተናገዱ በኋላ ሻል ብለው ቢታዩም ወደ ጨዋታው ሊመልሳቸው የሚችለውን ኳስ ከመረብ ማገናኘት ተስኗቸው ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋም።

አንድ አንድ ብቻ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ በመጀመሪያው አጋማሽ ያደረጉት ሁለቱ ቡድኖች በዚህኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በርከት ያሉ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ታይቷል። ገና አጋማሹ በተጀመረ በ15ኛው ሰከንድ ደግሞ ጥሩ መነቃቃት ላይ የነበሩት ጅማዎች እጅግ ፈጣን ኳስ መረብ ላይ አሳርፈው አቻ ሆነዋል። በዚህም አጋማሹን በኦስማኖ አማካኝነት የጀመረው ቡድኑ ዋውንጎ ፕሪንስ ከኦስማኖ ተቀብሎ ወደ ሳጥን ባሻገረው እና ተመስገን ደረሰ የግብ ዘቡ ባህሩ ጀርባ በሚገኘው መረብ ላይ በቀላቀለው ኳስ ወደ ጨዋታው ተመልሷል። ሳያስቡት ግብ የተቆጠረባቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ49ኛው ደቂቃ ዳግም መሪ ሊሆኑበት የሚችለውን አጋጣሚ ፈጥረው ነበር። በዚህም ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ አቡበከር በአግባቡ መቆጣጠር ሳይችል ጌታነህ አግኝቶት ወደ ግብ ቢመታውም ስዩም ተስፋዬ ኳሱን ከግብነት አግዶታል።

ጥሩ ፉክክር ማስመልከት የቀጠለው ጨዋታው በ54ኛው ደቂቃ ሌላ ሙከራ አስተናግዷል። በዚህ ደቂቃም ተመስገን ወደ ግራ ባዘነበለ ቦታ የተገኘውን የቅጣት ምት በመጠቀም ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል ለማስቆጠር ሞክሮ ነበር። ከዚህ ሙከራ ከስምንት ደቂቃዎች በኋላም ከጨዋታ ጨዋታ ጥሩ መግባባት እያሳዩ የሚገኙት ኦስማኖ እና ተመስገን ፍጥነት የታከለበት ቅብብል አድርገው ኦስማኖ በሞከረው ኳስ ቡድናቸውን ለመጥቀም ጥረዋል። የማጥቃት ሀይላቸውን ለማሻሻል ለውጦችን ያደረጉት አሠልጣኝ ፍራንክ ናታል በ66ኛው ደቂቃ ተጫዋቾቻቸው መሪ ሊያደርጓቸው ነበር። በዚህም በፍጥነት በእንቅስቃሴዎች የተደራጀበትን መንገድ ያጣው የጅማ የተከላካይ ክፍል ጀርባ የተገኘው አማኑኤል ጥሩ ኳስ ተቀይሮ ወደ ሜዳ ለገባው ሳልዓዲን ቢያመቻችለትም ከድር ኸይረዲን ደርሶ አጋጣሚውን ከአቡበከር ጋር በመተባበር አክሽፎታል። በተጨማሪም በ71ኛው ደቂቃ ያገኙትን የቅጣት ምት ለትችት በሚጋብዝ ሁኔታ የተጠቀሙት ጅማዎች ራሳቸው ላይ አደጋን ፈጥረው ነበር። በዚህም በመዘናጋት ለጊዮርጊስ ተጫዋቾች ያቀበሉትን ኳስ በመጨረሻም ያገኘው ጌታነህ ጅማን ለመቅጣት ቢጠቀምበትም ውጥኑ ሳይሰምር ቀርቷል።

በአቻ ውጤት 86ኛው ደቂቃ የደረሰው ጨዋታው በስተመጨረሻ መሪ ሊያገኝ ነበር። በተጠቀሰው ደቂቃም የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾችን የኳስ ቅብብል ስህተት ተጠቅሞ እግሩ ስር ኳስ የደረሰው ዋውንጎ ፕሪንስ ለተመስገን ጥሩ ኳስ ቢያመቻችም የአንዱ ግብ ባለቤት ዕድሉን በአስቆጪ ሁኔታ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ቅዱስ ጊዮርጊሶችም የመጨረሻ ሀይላቸውን በመጠቀም ግብ ለማስቆጠር ቢጥሩም የጅማን የተከላካይ መስመር ማለፍ ተስኗቸው ጨዋታውን ለመጨረስ ተገደዋል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት 1-1 በሆነ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።

ውጤቱን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ባህር ዳርን በግብ ልዩነት በልጦ በ31 ነጥቦች ወደ ሦስተኛ ደረጃ ከፍ ሲል ጅማ አባጅፋሮች ደግሞ ከሰሰቧቸው ነጥቦች እኩል አስራ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ፀንተው ተቀምጠዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ