ሪፖርት | የጦና ንቦቹ ዳግም ወደ አሸናፊነት ተመልሰዋል

በድሬዳዋ እና ወላይታ ድቻ መካከል የተደረገው የ10 ሰዓቱ ጨዋታ በድቻ አሸናፊነት ተቋጭቷል።

ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር የተታረቁት ድሬዳዋዎች ሦስት ነጥብ ካገኙበት የጅማው ጨዋታ ሁለት ተጫዋቾችን በጉዳት እና ቅጣት ምክንያት ለውጠው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዚህም አስቻለው ግርማ እና ፍሬዘር ካሳን በዘነበ ከበደ እና ሱራፌል ጌታቸው ተክተዋል። በፋሲል ከነማ ተረተው ለዚህኛው ጨዋታ የቀረቡት ድቻዎች ደግሞ አንተነህ ጉግሳ፣ በረከት ወልዴ፣ ነፃነት ገብረመድህን እና ጋቶች ፓኖምን በመልካሙ ቦጋለ፣ አበባየሁ አጪሶ፣ መሳይ አገኘው እና ዲዲዬ ለብሪ በመተካት ወደ ሜዳ ገብተዋል።

መመጣጠን የነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ ደቂቃዎች ፍልሚያ እስከ 18 ድረስ ምንም ሙከራ አላስተናገደም ነበር። ቡድኖቹ ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም ቀዳሚ ለመሆን ቢጥሩም ውጥናቸው እምብዛም ሳይሰምር ጨዋታው ቀጥሏል። በ18ኛው ደቂቃ ላይ የተፈጠረው የጨዋታው የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ግን መረብ ላይ አርፎ ቀዝቀዝ ያለውን ጨዋታ አነቃቅቷል። በዚህ ደቂቃም ቸርነት ጉግሳ ከመልስ ውርወራ የተቀበለውን ኳስ በግል ብቃቱ የድሬዳዋን ተከላካዮችን አልፎ ለስንታየሁ መንግስቱ አቀብሎት ቁመታሙ አጥቂ ጎል አስቆጥሯል። መሪ የሆነው ቡድኑም ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ሌላ የግብ ማግባት ሙከራ በቢንያም ፍቅሬ አማካኝነት አድርጎ የነበረ ቢሆንም ፍሬው ጌታሁም ኳሱን አምክኖታል።

ወደ ጨዋታው ቶሎ ለመመለስ ጥረት ማድረግ የጀመሩት ድሬዳዋዎች በ23ኛው ደቂቃ ጥሩ ጥቃት ፈፅመው ተመልሰዋል። በዚህ ደቂቃም ሄኖክ ኢሳይያስ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት ዳንኤል ኃይሉ አሻምቶት የቡድኑ አምበል በረከት ሳሙኤል በግንባሩ የዳንኤል አጄን መረብ ለማግኘት ጥሯል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ግን ቡድኑ ለልፋቱን ፈጣን ምላሽ አግኝቷል። በዚህም ሙኅዲን ሙሳ ከዳንኤል የተቀበለውን የመጨረሻ ኳስ በጥሩ እርጋታ መረብ ላይ አሳርፎ ድሬዳዋ አቻ ሆኗል።

ከሰባት ደቂቃዎች በላይ የጨዋታው መሪ መሆን ያልቻሉት የአሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ተጫዋቾች ዳግም መሪ ለመሆን በ31ኛው ደቂቃ ሙከራ አድርገዋል። ስንታየሁ ግብ ሲያስቆጥር የመጨረሻ ኳስ አመቻችቶ የነበረው ቸርነትም በዚህ ደቂቃ ከሳጥን ውጪ ጥብቅ ኳስ ቢመታም ፍሬው ዕድሉን ተቆጣጥሮበታል። ድሬዳዋዎች ደግሞ በ39ኛው ደቂቃ ሄኖክ ከግራ መስመር ወደ ግብ በመታው ኳስ መሪ ለመሆን ያላቸውን ፍላጎት ለመተግበር ጥረዋል። አጋማሹ ሊገባደድ አንድ ደቂቃ ሲቀርም ስንታየሁ መንግስቱ ለድቻ ጥሩ ጥቃት ቢሰነዝርም የግቡ ቋሚ ኳሱን መልሶበታል። እንደ አጀማመሩ ያልዘለቀው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመሪያውን ግብ ካስመለከተ በኋላ ተነቃቅቶ ቢታይም ከሁለት በላይ ግቦችን ሳያስተናግድ አጋማሹን ቋጭቷል።

ድሬዳዋን የኳስ ቁጥጥር የበላይ አድርጎ የተጀመረው የሁለተኛው አጋማሽም እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሙከራ ለማስተናገድ ደቂቃዎች ወስደውበታል። 59ኛው ደቂቃ ላይ ግን የድቻን ግብ ተቀባብለው ያውቆጠሩት ቸርነት እና ስንታየሁ በድጋሜ የተጣመሩበትን ትዕይንት ተመልክተናል። በዚህም ቸርነት ከመስመር ጥሩ ኳስ አሻግሮ የነበረ ቢሆንም ስንታየሁ ዕድሉን አምክኖታል። ጨዋታው ቀጥሎም ድሬዳዋዎች ኳስን ተቆጣትረው መጫወታቸውን ቢገፉበትም በ76ኛው ደቂቃ በሰሩት ጥፋት ተቀጥተዋል። በዚህ ደቂቃም ያሬድ ዳዊት ከቀኝ መስመር ኳስ ወደ ሳጥን እየገፋ ሲሄድ ኳሱን ለማውጣት ሲጥር የነበረው ዘነበ ከበደ ኳስ በእጅ በመንካቱ የዕለቱ ዳኛ የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተዋል። የፍፁም ቅጣት ምቱንም ስንታየሁ መንግስቱ ወደ ግብነት ቀይሮት ድቻዎች መምራት ጀምረዋል።

 
በመጨረሻዎቹ የጨዋታው ደቂቃዎች ያላቸውን ሀይል በመጠቀም ከጨዋታው አንዳች ነገር ይዞ ለመውጣት የጣሩት ድሬዎች ሱራፌል በ81ኛ ደቂቃ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመታው ኳስ የአቻነት ጎል ፈልገው ነበር። ነገር ግን በጭማሪው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ድሬ ግብ ክልል የደረሱት ድቻዎች በረከት ወልዴ ከርቀት በመታው ድንቅ ኳስ መሪነታቸውን ወደ ሦስት አስፍተዋል። ጨዋታውም በወላይታ ድቻ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ በጨዋታው ሦስት ነጥብ ለተጋጣሚ ያስረከቡት ድሬዳዋዎች እስካሁን በሰበሰቧቸው 16 ነጥቦች ያሉበት 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በተቃራኒው ከፋሲል ከነማው ሽንፈት ያገገሙበትን ውጤት ያስመዘገቡት ወላይታ ድቻዎች ነጥባቸውን 24 በማድረስ ትናንት አተውት የነበረውን ስድስተኛ ደረጃ ዳግም ተረክበዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ