የሀድያ ሆሳዕና እና ተጫዋቾቹ ወቅታዊ መረጃ

ትናንት ከክለቡ አመራር ጋር በደሞዝ ክፍያ ዙርያ ያልተስማሙት የሆሳዕና ተጫዋቾች ጉዳይ ከምን እንደደረሰ ወቅታዊ መረጃ እናድርሳችሁ።

በሀድያ ሆሳዕና ክለብ ዙርያ በትናንትናው ዕለት ዘገባችን “ተደጋጋሚ የደሞዝ ጥያቄያችን አልተፈታም” በሚል ከክለቡ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ባረፉበት ሆቴል ሰፊ ውይይት በማድረግ ውይይታቸው መፍትሄ ሳያስገኝ መለያየታቸውን መዘገባችን ይታወቃል። ሆኖም የክለቡ አመራሮች ችግሩን ለመቅረፍ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ተጫዋቾቹን አሳምነው የፊታችን ማክሰኞ ምሽት ላይ ከአዳማ ከተማ ጋር ላለው ጨዋታ እንዲጓዙ ለማድረግ ማሰባቸውን ገልፀን ነበር።

አሁን በተገኘው መረጃ የከተማው ካቢኔ ለክለቡ የፋይናንስ ክፍል ገንዘብ ገቢ ማድረጉ የታወቀ ሲሆን ይህም ተጫዋቾቹ ያቀረቡትን ጥያቄ ሙሉ ለሙሉ ምላሽ መስጠት ባይቻልም የተወሰነው ጥያቄን የሚመልስ በመሆኑ ነገ ጠዋት አንድ ሰዓት በሚኖረው በረራ ከአዲስ አበባ ወደ ድሬዳዋ እንደሚጓዙ ክለቡ ተስፋ አድርጓል።

ሆኖም ከተጫዋቾቹ ወገን ምንም እንኳን የሁለት ወር ደሞዝ ቢከፈላቸውም “አሁንም መሠረታዊ የሆነው ጥያቄያችን አልተፈታም” በሚል የአቋም ለውጥ እንደማያደርጉ እየገለፁ ይገኛሉ።

በአጠቃላይ የክለቡ ጉዳይ በዚህ ደረጃ የሚገኝ ሲሆን የክለቡ አመራሮች በተለይም ፕሬዝዳንቱ አቶ መላኩ ማደሮ ቡድኑ ለነገው ምሽት ጨዋታ ማለዳ ላይ ወደ ድሬዳዋ እንዲጓዙ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።


© ሶከር ኢትዮጵያ