ቅድመ ዳሰሳ | ፋሲል ከነማ ከ ባህር ዳር ከተማ

ነገ ከሰዓት በሚደረገውን ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

አዲስ አበባ ስታድየም ላይ የተደረገውን የዚህን መርሐ-ግብር የመጀመሪያ ዙር ፍልሚያ ለተመለከተ የነገውን ጨዋታ በጉጉት መጠበቁ አስገራሚ አይሆንም። ተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ ጥሩ አቋም ላይ የሚገኙት እና በድሬዳዋ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታም በየፊናቸው ድልን ያጣጣሙት ፋሲል እና ባህር ዳር ነገ ሁለተኛውን ለመድገም ይገናኛሉ። በመሪነቱ እየገሰገሰ ለቻምፒዮንነቱ በመቃረብ ላይ የሚገኘው ፋሲል ዘንድሮ ሙሉ ነጥብ ካላሳካባቸው ሦስት ጨዋታዎች ሰባት ነጥብ ሲያጣ ሁለቱን ነጥቦች ለመጣል የተገደደው በባህር ዳር እጅ መሆኑ ከሰበታው ጨዋታ በኋላ አምስተኛ ድሉን ለማስመዝገብ ተጨመሪ ተነሳሽነት ይፈጥርለታል። በፋሲል ላይ የመጀመሪያ የሊግ ድላቸውን ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ የሚጠበቁት የጣና ሞገዶችም በተመሳሳይ አምስተኛ ተከታታይ ድልን በመቀዳጀት የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳታፊነት የማግኘት ሩጫቸውን ለማስቀጠል ይፋለማሉ።

ፋሲል ከነማ ወላይታ ድቻን በረታበት የመጨረሻ ጨዋታው የነበረው የሜዳ ላይ መንፈስ ለነገው ከባድ ግጥሚያ መነሻ ይሆነዋል። ከተጋጣሚ ጫና ቀስ በቀስ በመውጣት ጨዋታውን በራስ መንገድ ለማስኬድ መሞከር እና ግብ እስኪያገኙ ድረስ በእርጋታ ክፍተቶችን የመፈለግ ጥንካሬ በአፄዎቹ ላይ ተስተውሏል። እርግጥ ነው የነገ ተጋጣሚያቸው ከጨዋታው መጀመር አንስቶ አጥቅቶ የመጫወት ዝንባሌ እንደሚኖረው ይገመታል። በዚህም በድቻው ጨዋታ ኳስን ለመጀመር እምብዛም ጫና ያልነበረባቸው የቡድኑ የኋላ መስመር ተሰላፊዎች እና ከጥልቅ የሚነሱ አማካዮች በዚህ ጨዋታ ከኳስ ጋር እምብዛም ጊዜ ሳያገኙ ማጥቃቱን የማስጀመር ኃላፊነት ይጠብቃቸዋል።

ከሁሉም በላይ ግን ቡድኑ በፈለገው ጊዜ ተገቢውን ምላሽ እየሰጠ የሚገኘው ሙጂብ ቃሲምን ያማከሉ ኳሶች ከሁለቱ መስመሮች ወደ ሳጥን ውስጥ ማድረስ የቡድኑ ቅብብሎች የመጨረሻ ግብ የሚሆን ይመስላል። ፋሲል ያለፉትን ዘጠኝ ነጥቦች በሙሉ በግዙፉ አጥቂ ጎሎች ብቻ እንደማሳካቱ የሚኖርበትን ጫና ከሌሎች ተጫዋቾችም ጭምር ግብ በማግኘት ማቃላል የሚኖርበት መሆኑ ግን ዕሙን ነው። ለዚህም የቡድኑ ስብስብ ከጉዳት እና ቅጣት ነፃ ሆኖ ለጨዋታው መድረሱ ለአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ሰፊ አማራጭ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።

ከተጋጣሚያቸው በተለየ ያለፉትን አራት ጨዋታዎች ሙሉ ነጥቦችን እንዲያገኙ የረዷቸውን ስድስት ጎሎች ከአምስት የተለያዩ ተጫዋቾች ያገኙት የጣና ሞገዶቹ ይህ ጠንካራ ጎናቸው ነገም ተጠቃሚ ሊያደርጋቸው ይችላል። በግብ ፊት የተሻለ ዕድል ላለው የቡድን ጓደኛ ኳስን ለማድረስ ከመድፈር እና የመጨረሻ የግብ ውሳኔዎችን ከመወሰን አንፃር መሰል እውነታዎች የቡድንን ማጥቃት ፍፃሜ እንዲያምር ጉልህ ድርሻ ይኖራቸዋል። ከዚህ ባለፈ ባህር ዳር አማካይ ክፍል ላይም የሚና ሽግሽጎች አድርጎ በተለይ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ሲገባ እንደ ሳምሶን ጥላሁን ካሉ ተጫዋቾች በተለየ ሁኔታ የመጨረሻ የግብ ዕድል የሚፈጥሩ ኳሶችን ሲያገኝ መታየቱ ከዚህ ቀድም በዚህ ረገድ ያለበትን ችግር ማሻሻሉን ያሳያል።

ቡድኑ መሀል ሜዳ ላይ ከባድ ፍልሚያ እንደሚደረግ ከሚጠበቅበት ከነገው ጨዋታ አንፃር ተጋጣሚውን የሚመጥን የወገብ በላይ አቋም ላይ እንዳለ መናገር ቢቻልም በመከላከሉ ረገድ ግን እንዳይቸገር ያሰጋል። እርግጥ ነው ላለፉት ሦስት ጨዋታዎች ግብ አለማስተናገዱ ሲታይ ለፋሲል አጥቂዎች በቀላሉ እንደማይከፈት መናገር ቢቻልም ተጋጣሚው በልዩነት ፈጣሪ ተጫዋቾች የተሞላ ከመሆኑ አንፃር አልፎ አልፎ የሚታይበትን የመናበብ ስህተት መቅረፍ ይኖርበታል። ከዚህ አንፃር የመሀል ተከላካዩ መናፍ ዐወል ለጨዋታው መድረስ አጠራጣሪ መሆን አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ለሰለሞን ወዴሳ ሁነኛ አጣማሪ የማግኘት የቤት ሥራ የሚሰጣቸው ይመስላል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊግ ጨዋታዎች ሦስት ጊዜ በተገናኙባቸው አጋጣሚዎች ስምንት ጎሎች ተቆጥረዋል። በጨዋታዎቹ አንድ ጊዜ ድል የቀናው ፋሲል ከነማ ስድስቱን ባህር ዳር ደግሞ ሁለቱን ሲያስቆጥሩ ሁለቱ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ነበሩ።

* ወቅታዊው የኮቪድ ወረርሺኝ በቡድኖቹ የስብስብ ምርጫ ላይ እያሳደረ ካለው ተለዋዋጭነት አንፃር ግምታዊ አሰላለፍ ለማውጣት አዳጋች በመሆኑ የወትሮው የአሰላለፍ ትንበያችን በዳሰሳው ያልተካተተ መሆኑን እንገልፃለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ