ቅድመ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ ሀዲያ ሆሳዕና

የ18ኛው ሳምንት ማሳረጊያ የሆነውን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ከፊቱ የሁለት ቀናት ዕረፍት የሚጠብቁት የቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ ምሽት አዳማን ከሆሳዕና ያገናኛል። ሰባት ነጥቦች ላይ የቆመው አዳማ ከተማ የድሬዳዋ ቆይታውንም በሽንፈት መጀመሩ የሊጉ ቆይታው ላይ ትልቅ ጥያቄ ምልክት አስቀምጦበታል። ተስፋው ጨርሶ እንዳይጨልም እያንዳንዱ ጨዋታ ወሳኝ ከመሆኑ አንፃርም ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር በብርቱው እንደሚፋለም ይጠበቃል። የድሬው ውድድር ሲጀምር አራፊ የነበሩት ነብሮቹ ከተጋጣሚያቸው በደረጃ እጅግ ርቀው ይገኛሉ። ነብሮቹ ከመሪው ጋር ያላቸው ልዩነት ቢሰፋም ይኬንፌዴሬሽን ዋንጫ ፉክክሩ አሁንም እጃቸው ላይ ነው ፤ ነገ ድል ከቀናቸውም የቅዱስ ጊዮርጊስን የአራተኝነት ቦታ የሚይዙ ይሆናል።

በ17ኛው ሳምንት በሲዳማ ሽንፈት የገጠመው አዳማ በጨዋታው አዳዲስ ፈራሚ የውጪ ዜጋ ተጫዋቾቹንም ተጠቅሟል። ምንም እንኳን አሁንም ገና ወደ ሜዳ ያላስገባቸው ተጫዋቾች ቢኖሩም የቡድኑ ድክመት በግለሰባዊ ለውጦች ብቻ የሚስተካከል አይመስልም። በቀላሉ ግቦችን ከማስተናገዱ ባለፈ በራሱ የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን መፍጠር እጅግ ከብዶት ታይቷል። ከነገ ተጋጣሚው የመከላከል ብርታት አንፃርም ፈተናው ይበልጥ እንዳይብስ ያሰጋል። በቡድኑ ውጥ በግሉ ጥሩ እየተንቀሳቀሰ ያለው አብዲሳ ጀማል በግሉ የሚያደርጋቸው ጥረቶች እንዳሉ ሆነው አዳማ አሁንም ፊት ላይ አስፈሪነትን የሚያላብሰው ጥምረት ያስፈልገዋል።

አነጋጋሪነቱ የቀጠለው የሀዲያ ሆሳዕና የሜዳ ውጪ ጉዳይ ማምሻውን ጊዜያዊ መፍትሄ እንዳገኘ ተነግሯል። ስብስቡም ነገ ረፋድ ላይ ወደ ድሬዳዋ እንደሚደርስ ይጠበቃል። የከተማዋን ሞቃታማ አየር ከመላመድ አንፃር የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ስስብስብ ከሌሎች አንፃር መዘግየቱ ሊጎዳው ቢችልም የመጀመሪያ ጨዋታው ምሽት ላይ የሚደረግ መሆኑ መልካም ዜና ይሆንለታል። ሙሉ ስብስባቸው መልካም ጤንነት ላይ የሚገኙት ነብሮቹ በሦስቱ ከተማዎች ያሳዩትን የኋላ መስመራቸው ጥንካሬ በድሬዳዋም ይዘው ለመቀጠል እንደሚሞክሩ ሲጠበቅ የማጥቃት ሂደታቸው ላይ ተሻሽለው ለመቅረብ ሲሰሩ እንደሰነበቱም ይገመታል። ከነገ ተጋጣሚያቸው ወቅታዊ አቋም አንፃርም በአዳዳስ ተጫዋች የተጠናከረው የቡድኑ የወገብ በላይ ክፍል የተሻለ ብቃት ሊያሳይ እንደሚችል ይጠበቃል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– 2008 ላይ በተደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታዎች አዳማ ከተማ አራት ግቦችን አስቆጥሮ ሁለቴም ባለድል መሆን ሲችል ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ የዘንድሮውን ሦስተኛ ግንኙነታቸውን በ3-1 ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

* ወቅታዊው የኮቪድ ወረርሺኝ በቡድኖቹ የስብስብ ምርጫ ላይ እያሳደረ ካለው ተለዋዋጭነት አንፃር ግምታዊ አሰላለፍ ለማውጣት አዳጋች በመሆኑ የወትሮው የአሰላለፍ ትንበያችን በዳሰሳው ያልተካተተ መሆኑን እንገልፃለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ