አሰልቺው የሀዲያ ሆሳዕና እና የተጫዋቾቹ ሁኔታ አነጋጋሪነቱ ቀጥሏል

ያለፉትን ሦስት ቀናት እያነጋገረ የሚገኘው የሀዲያ ሆሳዕና እና የተጫዋቾቹ ውዝግብ ዛሬ ለጨዋታ መዘጋጀት በነበረባቸው ሰዓትም ቀጥሏል።

በክለቦች እና በተጫዋቾች መካከል ግልፅ ሳይደረጉ የሚከናወኑ ስምምነቶች በተደጋጋሚ ጊዜያት ውዝግብ ሲፈጥሩ መስተዋሉ በኢትዮጵያ እግርኳስ አዲስ ነገር አይደለም። ይህ ሁኔታ በእግርኳሱም ሆነ በሀገር ገፅታ ላይ መጥፎ ስም እያተረፈ ያለፉትን ዓመታት ተጉዞ እዚህ ደረጃ ላይ ደርሷል።

ሰሞነኛው የሀዲያ ሆሳዕና እና የተጫዋቾቹ ከደሞዝ ክፍያ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጉዳይ ለመስማት አሰልቺ የሆኑ ውዝግቦችን መፈጠራቸውን በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወቃል። የተጫዋቾቹ የሁለት ወር ደሞዝ በትናንትናው እለት መከፈሉ ቢገልፅም በተጫዋቾቹ ዘንድ “ክለቡን ስንቀላቀል እንዲከፈለን የተስማማነው ገንዘብ ይከፈለን” የሚል ጥያቄ ማቅረባቸው የተሰማ ሲሆን ዛሬ በማለዳ በረራ ወደ ድሬ ያቀናሉ ቢባልም ይህንን ዘገባ በምናጠናክርበት ወቅት በአዲስ አበባ በአንድ ሆቴል ተቀምጠው ተጫዋቾቹ ከክለብ አመራሮች ጋር እንደተወያዩ ለማወቅ ችለናል።

ከውይይቱ መጠናቀቅ በኃላ እንዳገኘነው መረጃ ከሆነ ክለቡ የተለያዩ ማማለያዎችን በማቅረብ እና በዚህ ሳምንት በሚጠናቀቅ የክፍያ ስምምነት ተስማምተው ጨዋታ ከሚያደርጉበት አራት ሰዓት አስቀድመው ድሬዳዋ ሊገቡ እንደሚችሉ ለማወቅ ችለናል።

የሀገሪቱ ቁጥር አንድ ውድድር ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የሆነ የቀጥታ ስርጭት ሽፋን እያገኘ እና ወደ ጥሩ ጎዳና እየተጓዘ በሚገኝበት በዚህ ወቅት እንደዚህ ያለ አሳፋሪ ውዝግብ ማየት የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅእኖ ቀላል የማይባል ስለሆነ ክለቦች፣ ተጫዋቾች፣ ፌዴሬሽኑ፣ የሊግ ካምፓኒው እና በአጠቃላይ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ቆም ብለው ማሰብ እንዳለባቸው ማስገንዘብ እንወዳለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ