ሪፖርት | አዳማ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ነጥብ ተጋርተዋል

የ18ኛው ሳምንት የመጨረሻ መርሐ-ግብር አዳማ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕናን አገናኝቶ በ 1-1 ውጤት ተጠናቋል።

አዳማ ከተማ ከሲዳማው ሽንፈት ባደረጋቸው ለውጦች አዲስ ፈራሚ ግብ ጠባቂው ሳኩራ ካማራን በታሪክ ጌትነት ቦታ ሲለውጥ ጅሚል ያዕቆብ ፣ ማማዱ ኩሊባሊ እና በቃሉ ገነነን በታፈሰ ሰረካ ፣ አሚን ነስሩ እና ያሬድ ብርሀኑ ቦታ ተጠቅሟል። ሀዲያ ሆስዕናዎች በበኩላቸው ባህር ዳር ላይ ሲዳማን ሲረቱ ከተጠቀሙበት አሰላለፍ ፀጋሰው ደማሙ ፣ ተስፋዬ በቀለ ፣ አክሊሉ አያናው እና መድሀኔ ብርሀኔን በቴዎድሮስ በቀለ ፣ አይዛክ ኢሴንዴ ፣ ሄኖክ አርፌጮ እና ተስፋዬ አለባቸው ተክተዋል።

ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ ቀዳሚ ደቂቃዎች ሁለቱም ሙከራዎችን ማድረግ ችለው ነበር። በሆሳዕና በኩል ዑመድ ዑኩሪ ከሳጥን ውስጥ የመታውን ኳስ ተከላካዮች ተደርበው ሲያድኑበት የአዳማው ማማዱ ኩሊባሊ ከሳጥን ውጪ የመታው ኳስ ወደ ውጪ ወጥቷል። ሀዲያ ሆሳዕናዎች በአመዛኙ ወደ ቀኝ መስመር አጥቂያቸው ቢስማርክ አፒያ ያደሉ ረጃጅም ኳሶችን በመጣል በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ተጭነው ለመጫወት ሞክረዋል። በአንፃሩ አዳማዎች ከሌላው ጊዜ ጠጠር ብለው በቅብብሎች ላይ በመመስረት ወደ ግብ ለመድረስ ሲጥሩ ተስተውለዋል።

የጨዋታው የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ 17ኛው ደቂቃ ላይ ሲደረግ ከመሀል ሜዳው አለፍ ብሎ የተገኘውን ቅጣት ምት ዳዋ ሆቴሳ በአስገራሚ ሁኔታ ወደ ጎል ልኮት የአዳማው አዲስ የግብ ዘብ ሳኩራ ካማራ አድኖበታል። በአዳማዎች በኩል 26ኛው ደቂቃ ላይ የኤልያስ ማሞ ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ ኩሊባሊን ከመሀመድ ሙንታሪ ጋር አገናኝቶት ሙከራው በግብ ጠባቂው ድኗል። ቀስ በቀስ አዳማዎችም ረዘም ያሉ ኳሶችን እየተጠቀሙ በጥሩ ፉክክር በቀጠለው ጨዋታ የግብ ሙከራዎች ሳይታዩ ቢቆዩም አዳማ ከተማ ከእረፍት በፊት መሪ መሆን የሚችልበት ዕድል ፈጥሮ ነበር። በዚህም 41ኛው ደቅቂቃ ላይ ከኤልያስ ማሞ በግሩም ሁኔታ የመጣውን ኳስ አብዲሳ ከቀኝ የሳጥኑ ክፍል ሲመታው ሙንታሪ መልሶታል። ሆኖም ኳሱ ባለመራቁ በቃሉ አግኝቶ ለኤልያስ አመቻችቶለት ኤልያስ በግራ እግሩ ቢሞክርም ሙንታሪ በድጋሚ በድንቅ ሁኔታ መልሶታል።

ጨዋታው ከዕረፍት መልስ ሲቀጥል አዳማ ከተማዎች በቶሎ ግብ ቀንቷቸዋል። 48ኛው ደቂቃ ላይ ከግብ ጠባቂው የተነሳው እና ኩሊባሉ ያደረሰውን ኳስ ኤልያስ ማሞ በግሩም ሁኔታ አሻግሮለት አብዲሳ ጀማል ከቀኝ የሳጥኑ ክፍል መትቶ ወደ ጎልነት ቀይሮታል።
ቀይሮታል።

ከግቡ በኋላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ማድረጋቸውን የቀጠሉት ሀዲያዎች 61ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማግኘት ተቃርበው ነበር። በዚህም ከደቂቃ በፊት አልሀሰን ካሉሺያን ቀይሮ የገባው መድሃኔ ብርሃኔ ዑመድ ያመቻቸለትን ኳስ ወደ ግብነት ለመቀየር ጥሮ መክኖበታል። ከዚህ መከራ በተጨማሪም ዑመድ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን የቅጣት ምት አዲስ ህንፃ አሻግሮት ዳዋ ለመጠቀም ጥሮ ነበር። በተቃራኒው ግብ ካስቆጠሩ በኋላ አፈግፍገው መጫወታቸውን የቀጠሉት አዳማዎች ያገኙትን ሦስት ነጥብ ላለማጣት ሲታትሩ ታይተዋል።

ከሴኩምባ ካማራን ጀርባ የሚገኘውን መረብ ፍለጋቸውን የቀጠሉት ሀዲያዎች በ76ኛው ደቂቃ የልፋታቸውን ውጤት አግኝተው አቻ ሆነዋል። ግቡ ከመቆጠሩ በፊትም ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ ዑመድ ተገልብጦ (በመቀስ ምት) በመምታት ግብ ለማስቆጠር ቢጥርም የግብ ዘቡ ካማራ አውጥቶበታል። ግብ ጠባቂው ያወጣውን ኳስም በመጠቀም የመዓዘን ምቱን ያሻገሩት ሀዲያዎች የአዳማ ተከላካዮች በሚገባ ያላፀዱትን ኳስ አጥቂያቸው ዳዋ አግኝቶት ከመረብ ጋር አዋህዶላቸዋል። ቡድኑ የአቻነት ግብ ካስቆጠረ በኋላም በጥሩ ተነሳሽነት ማጥቃቱን ቀጥሎበታል። በተለይም ረጃጅም ተሻጋሪ ኳሶችን በመጠቀም ሦስት ነጥብ የሚያገኝበትን ጎል ማሰሱን ይዟል።

በ85ኛው ደቂቃም ከርቀር ሳጥን ላይ የተጣለውን ኳስ ግብ ጠባቂው ካማራ በሚገባ ሳይቆጣጠረው ቀርቶ ዑመድ አግኝቶታል። አጥቂውም ኳስን በጥሩ ቅልጥፍና ለማስቆጠር ቢጥርም የአዳማ ተከላካዮች ተረባርበው አውጥተውበታል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ በተጨመረው ደቂቃም ቡድኑ የመጨረሻ ሙከራውም በዑመድ አማካኝነት ሰንዝሮ ነበር። ቀሪዎቹ ደቂቃዎችም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርባቸው ጨዋታው 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ አዳማ ከተማ ነጥቦቹን 8 አድርሶ የደረጃ ሠንጠረዡ ግርጌ ላይ መቀመጡን ሲቀጥል ሀዲያዎች ደግሞ በ27 ነጥቦች ያሉበት አምስተኛ ደረጃ ላይ ፀንተው ተቀምጠዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ