የአሠልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 1-1 ሀዲያ ሆሳዕና

የ18ኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ ከተገባደደ በኋላ ሱፐር ስፖርት ከአሠልጣኞች የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ተቀብሏል።

አሸናፊ በቀለ – ሀዲያ ሆሳዕና

ከሜዳ ውጪ የነበረው ነገር ቡድኑ ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል?

በመጀመሪያው አጋማሽ ተቸግረናል። ተከላካዮቻችንም በአግባቡ አይደራጁም ነበር። ሌላ ጊዜ የማንሳሳተውን የቦታ አጠባበቅ ዛሬ ስንስተው ነበር። ይህንን ደግሞ በሁለተኛው አጋማሽ አስተካክለነዋል።

የቡድኑ የጨዋታው እቅድ?

መከላከል አስበን አልገባንም። ከመጀመሪያም ጀምሮ አማራጬ ማጥቃት ነበር። ግን እንዳልኩት የአቋቋምም ስህተት ነበር። እነሱ እንደውም ጥሩ ጥሩ አጋጣሚዎችን ሲፈጥሩ ነበር። የእኛ ግብ ጠባቂ ጥሩ በመሆኑ ነው ግብ ያላስተናገድነው። ግን ቀድሜም እንዳልኩት አጥቅተን ለመጫወት ነበር የፈለግነው። ቢሆንም ግን ያሰብናቸው ታክቲካል ዲሲፕሊኖች አልተሳኩልንም። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ጥሩ ነበርን።

ውጤቱ ፍትዓዊ ነው?

ለእነሱ ትልቅ ውጤት ነው። ምክንያቱም አዳማ አሁን ካለበት ደረጃ አኳያ አንፃር ነጥብ ያስፈልገዋል። እኛም ሜዳ ላይ ካደረግነው እንቅስቃሴ አኳያ አንድ ነጥቡ ለእነሱ ጥሩ ነው።

ሀዲያ ከዋንጫ ፉክክሩ ርቋል?

ከፋሲል ጋር ያለን ነጥብ ሰፊ ነው። ግን ጥሩ ተፎካካሪ መሆንም ዋንጫ እንደማግኘት ነው። ሁሉም ቡድን ዋንጫ አያገኝም። ግን በውድድር ውስጥ ጥሩ ተሳታፊ ሆኖ መቅረብም የዋንጫ ያህል ነው። በአጠቃላይ ውድድሩን ስንጀምርም ዝም ብለን አደለም። ከአንድ እስከ ሦስት ለማጠናቀቅ ራዕይ አለን። ቡድኑንም የማዘጋጀው ለዚሁ ነው።

ዘርዓይ ሙሉ – አዳማ ከተማ

ስለ ጨዋታው?

ይሄ ነጥብ ያስፈልገን ነበር። ከእረፍት በፊፌፍ ጨዋታውን መግደል ነበረብን። ከሦስት በላይ ኳሶችን አመከንን እንጂ ጨዋታው ከእረፍት በፊት ማለቅ ነበረበት። በሁለተኛው አጋማሽም ግብ ካገባን በኋላ አስጠብቀን እንድንወጣ አስቤ ነበር። ዞሮ ዞሮ ከመዓዘን ምት ግብ ተቆጥሮብን አቻ ወጥተናል። በአጠቃላይ ግን ዛሬ ቡድኔ በጣም ጥሩ እና የተሻለ ነበር። ከባለፈውም ጨዋታ የተሻለ ተንቀሳቅሰናል። አዲስ ቡድንም እንደመሆኑ መጠን ትልቅ ለውጥ አለው ብዬ ነው የማስበው። እንደምታቁት ሀዲያ ትልቅ ቡድን ነው። በተለይ ረጃጅም ኳሶችን መጫወት የሚያዘወትር ቡድን ነው። ይህንንም ቡድን ደግሞ አቁመን ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረጋችን ጥሩ ነው ብዬ ነው የማስበው።

ቡድኑ ያገኛቸውን የግብ ዕድሎች ስለማምከኑ?

እውነት ነው። ቀድሜ እንዳልኩት ዛሬ ሦስት ነጥብ ያስፈልገን ነበር። ይህንንም አስበን ነበር ወደ ሜዳ የገባነው። ከእረፍት በፊትም ብዙ ነገር ማድረግ እንችል ነበር። ከእረፍት መልስም ያገኘነውን አጋጣሚ ተጠቅመናል። ግን ይህንን ጎል አስጠብቀን ለመውጣት እያሰብን ባለበት ጊዜ ነው ጎል የተቆጠረብን። አንዳንዴ ደግሞ እንደዚህ አይነት ነገር ይከሰታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ