ሪፖርት | በጉሽሚያ የተሞላው የዐፄዎቹ እና የጣና ሞገዶቹ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተገባዷል

ተጠባቂው የፋሲል ከነማ እና ባህር ዳር ከተማ ጨዋታ በበርካታ ጥፋቶች ታጅቦ 0-0 በሆነ ውጤት ተቋጭቷል።

በህመም ምክንያት ዋና አሠልጣኙን (ሥዩም ከበደ) ከጨዋታው ውጪ አድርጎ ወደ ሜዳ የገባው ፋሲል ከነማ ወላይታ ድቻን ከረታበት የመጨረሻ ጨዋታው ምንም ለውጥ ሳያደርግ ለወሳኙ ፍልሚያ ራሱን አዘጋጅቷል። በተቃራኒው ወልቂጤ ከተማን ረተው ለዚህኛው ጨዋታ የቀረቡት የባህር ዳር ከተማው አሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ጉዳት ያጋጠመውን መናፍ አወልን ብቻ በሳሙኤል ተስፋዬ ለውጠዋል።

በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጥሩ ፉክክር ማሳየት የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በሦስተኛው ደቂቃ ግልፅ የግብ ማግባት ዕድል ተፈጥሮበታል። በዚህ ደቂቃም ባህር ዳር የፋሲል ከነማ ተጫዋቾችን ተጭኖ የተረከበውን ኳስ በፍጥነት ወደ ግብ ክልል አድርሶት ባዬ ገዛኸኝ ወደ ግብነት ሊቀይረው ተቃርቦ ነበር። ነገርግን አጥቂው የመታው ኳስ ለጥቂት ዒላማውን ስቶ ወደ ውጪ ወጥቷል። ለተሰነዘረባቸው ጥቃት ወዲያው ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ያላመነቱት ፋሲሎች በስድስተኛው ደቂቃ መሪ መሆን የሚያስችላቸውን ሙከራ አድርገዋል። በዚህም ፍቅረሚካኤል በዛብህ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት ሱራፌል መረብ ላይ ለማሳረፍ ጥሯል። በድጋሜም በ14ኛው ደቂቃ ሽመክት ወደ ግብ የመታውን ኳስ የባህር ዳር ተከላካዮች በሚገባ ሳያፀዱት ቀርተው አምሳሉ አግኝቶት በጥሩ ሁኔታ ወደ ግብ መትቶት ነበር።

በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች መመጣጠን የነበረው ጨዋታው ቀስ በቀስ ፋሲል ከነማን የእንቅስቃሴ የበላይ አድርጎ ቀጥሏል። ቡድኑም ከባህር ዳር በተሻለ ኳስን በመቆጣጠር የማጥቂያ አማራጩን በሁለቱ መስመሮች በማድረግ መንቀሳቀስ ይዟል። አልፎ አልፎም ግን ከሳጥን ውጪ የሚገኙ ኳሶችን ለመጠቀም ጥሯል። በዚህ የጨዋታ እንቅስቃሴም ሽመክት በ24ኛው በረከት ደግሞ በ25ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጪ ጥሩ ጥቃት ፈፅመዋል።

በተቃራኒው ወደ ራሳቸው ሜዳ በመጠጋት እየተጫወቱ የነበሩት ባህር ዳሮች የሚያገኟቸውን ኳሶች በረጅሙ ለፈጣኖቹ አጥቂዎቻቸው በመላክ አደጋ ለመፍጠር ዳድተዋል። ነገርግን ውጥናቸው ሳይሰምር አጋማሹን ያለ ምንም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አገባደዋል። ፋሲሎችም የተሻለ ብልጫ የነበራቸው ቢሆንም የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ የነበራቸውን ብልጫ በጎል ለማሳጀብ ቆርጠው የተነሱ የሚመስሉት ፋሲል ከነማዎች አጋማሹ በተጀመረ በአምስተኛው ደቂቃ ያለቀለት ሁለት ሙከራዎችን ሰንዝረው ባህር ዳርን አስደንግጠዋል። በዚህም ከመዓዘን የተሻገረው ኳስ የግብ ዘቡ ፅዮን ሲመልሰው ሳጥን ውስጥ ራሱን ነፃ አድርጎ ቆሞ የነበረው ሽመክት ጥብ ኳስ ወደ ግቡ ልኳል። ነገር ግን ሽመክት የመታውን ኳስ የግቡ አግዳሚ መልሶታል። ከ20 ሰከንዶች በኋላም ይሄው ኳስ ሳይወጣ ከቡድን አጋሩ የደረሰውን ሙጂብም በድጋሜ ወደ ጎል የመታው ኳስ የግቡ ቋሚ አክሽፎታል። ድንቅ አጀማመር ያሳየን የሁለተኛው አጋማሽ በ56ኛው ደቂቃም ሌላ የግቡ ቋሚ የመለሰውን የግብ ሙከራ አስተናግዷል። በዚህ ደቂቃም ባዬ በሀብታሙ የተሰራበትን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት በመጠቀም ከርቀት ለግብ ጠባቂ አስቸጋሪ የሆነ ኳስ ወደ ግብ የላከ ቢሆንም ቋሚው ዕድሉን አምክኖበታል።

ፍጥነት የታከለበት የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ጨዋታውን የቀጠሉት ባህር ዳሮች በ67ኛው ደቂቃ የመሐል አጥቂያቸው በሞከረው ኳስ መሪ ለመሆን ያላቸውን ፍላጎት አሳይተዋል። ፋሲሎችም ማጥቃታቸው ላይ ትንሽ ፍጥነት ጨምረውበት ባህር ዳርን ማስጨነቅ አጠናክረው ይዘዋል። በ77ኛው ደቂቃም የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሙጂብ ቃሲም እጅግ ለግብ የቀረበበትን አጋጣሚ ቢፈጥርም የፅዮንን መረብ ማግኘት ሳይችል ቀርቷል።

እጅግ በርካታ ጥፋቶች የበዙበት ጨዋታው በመጨረሻ ደቂቃዎቹ ላይ አሸናፊውን ለመለየት ተጋግሎ ቀጥሏል። ቡድኖቹም የሚያገኟቸውን ኳሶች በጥሩ ቅልጥፍና ወደ ጎልነት ለመቀየር ሲታትሩ ተስተውሏል። በዚህም ፋሲል ከነማ በ85ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ወደ ሜዳ በገባው ናትናኤል አማካኝነት የባህር ዳርን ግብ ፈትሿል። ባህር ዳርም በ89ኛው ደቂቃ ሳሙኤል በሞከረው እንዲሁም በ90ኛው ደቂቃ ዜናው በመታው ኳስ ጨዋታውን ለመግደል ተቃርቦ ነበር። ሁለቱም ቡድኖች ከጨዋታው ሦስት ነጥብ ለመውሰድ ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ጨዋታው ያለ ጎል 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ፋሲል ከነማ ነጥቡን 42 በማድረስ ከተከታዩ ኢትዮጵያ ቡና ያለውን ልዩነት ዘጠኝ አድርጓል። ባህር ዳሮችም ከዚህ በፊት የሰበሰቧቸው ነጥቦች ላይ አንድ ነጥብ አክለው በ30 ነጥቦች ሦስተኛ ደረጃን አጠናክረው ይዘዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ