በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረገው የአፍሪካ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ላይ የሚሳተፉ ሀገራት የሚለዩበት የምስራቁ ዞን የክለቦች ውድድር በየትኛው ሀገር እና መቼ እንደሚደረግ ታውቋል።
የአፍሪካ እግር ኳስ የበላይ አካል የሆነው ካፍ ሰኔ 23 2012 ላይ ስራ አስፈፃሚዎቹ ባደረጉት ስብሰባ የአፍሪካ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር እንዲጀመር ወስኖ እንደነበር ይታወቃል። በወቅቱም ስምንት ክለቦችን በሚወዳደሩበት መድረክ ላይ ለመሳተፍም የየሀገሮቹ የሊግ አሸናፊ ክለቦች በሚገኙበት ስድስት ቀጠናዎች በመመደብ የማጣሪያ ጨዋታቸውን በቅድሚያ እንደሚያደርጉ ተብራርቶ ነበር። ይህንን ተከትሎም ኢትዮጵያ በምትገኝበት ቀጠና ላይ የሚደረገው የቅድመ ማጣሪያ ውድድር በኬንያ አስተናጋጅነት እንደሚከወን ተሰምቷል።
የኬንያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ የስራ አስፈፃሚ አባል ባሪ ኦቲኖ ብሔራዊ ፌደሬሽናቸው ውድድሩን ለማዘጋጀት መመረጡን ገልፀዋል። የ11 ሀገር ክለቦች የሚሳተፉበት የምስራቅ ቀጠናው የማጣሪያ ውድድርም ከጁላይ 17- ኦገስት 1 (ከሀምሌ 10-25) ድረስ እንደሚከናወን ተነግሯል።
የ2013 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ የሆነው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ከውድድሩ አዘጋጅ ኬንያ እንዲሁም ዩጋንዳ፣ ታንዛንያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ዛንዚባር፣ ጂቡቲ፣ ኤርትራ፣ ሩዋንዳ እና ቡሩንዲ ከሚመጡ የሊግ አሸናፊዎች ጋር በሚያደርገው የማጣሪያ ፍልሚያ አሸናፊ ከሆነ ራሱን ለቻምፒየንስ ሊጉ ውድድር የሚያበቃ ይሆናል።
© ሶከር ኢትዮጵያ