“ተጫዋቾች አንድ ቦታ ላይ ብቻ መጫወት የለባቸውም” -ተመስገን ደረሰ

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረገ ከሚገኘው ሁለገቡ ተመስገን ደረሰ ጋር ቆይታ አድርገናል።

የቀድሞው የጅማ አባ ቡና እና ወልቂጤ ከተማ ተጫዋች ተመስገን ደረሰ ዘድንሮ የሚጫወትበት ቡድኑ ጅማ አባ ጅፋር ደካማ የውድድር ዓመት እያሳለፈ የሚገኝ ቢሆንም በግሉ መልካም የሚባል የውድድር ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል። በመስመር ተከላካይነት እንዲሁም በተለያዩ የአጥቂ ሥፍራ አማራጮች በመጫወት ሁለገብነቱን ከማሳየቱ በተጨማሪ በሜዳ ውስጥ ያለው አልሸነፍ ባይነት እና ታታሪነቱ ልዩ መገለጫ እየሆነ መጥቷል። እስካሁን በሊጉ አምስት ጎል በማስቆጠር አቅሙን እያሳየ የሚገኘው ተመስገን ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በወቅታዊ አቋሙ ዙርያ ያደረገውን ቆይታ እንዲህ አቅርበነዋል።

እያሳለፈ ስለሚገኘው የውድድር ጊዜ

እጅግ በጣም ጥሩ ጊዜ በግሌ እያሳለፍኩ ነው። ቡድናችን ያለበት ደረጃ ጥሩ አይሁን እንጂ እኔ በግል ጥሩ ነኝ፤ የሚታይ ነገር አለ። ግን ቡድናችንን አሁን ካለበት ደረጃ የተሻለ ደረጃ ለማድረስ እየተጋን ነው። ከአንደኛው ዙር የተሻለ ነገር አለን። በአንደኛው ዙር እንደሚታወቀው ብዙ ችግሮችን አሳልፈናል። ያ ብዙ ተፅኖ አድርጎብናል። ያም ቢሆን አሁን የተሻለ ነገር ለማድረግ እየጣርን እንገኛለን።

ስለ ሁለገብ ተጫዋችነቱ

ሁለገብ ተጫዋች መሆኔን ብዙ ሰዎች ያነሱልኛል። ወልቂጤ እና አባቡና እያለው የቀኝ መስመር ተከላካይ ሆኜ እጫወት ነበር። አልፎ አልፎ ግራ ላይም እጫወት ነበር። አሁን ላይ የመስመር አጥቂ በመሆን እየተጫወትኩ ነው። ያው አንዳንዴ አሰልጣኝ አድርግ የሚልህን ነገር ማድረግ አለብህ። ምክንያቱም አንድ ተጫዋች ሁለት ሦስት ቦታ መጫወት አለበት። ይህ መሆኑ በአሰልጣኝ ልትፈለግ ትችላለህ፤ አማራጭም ታሰፋለህ። አንድ ተጫዋች አንድ ቦታ ላይ ብቻ መጫወት የለበትም። በተለያዩ ቦታዎች በመጫወት መተካካት ያስፈልጋል። እግርኳስ ላይ ሁለገብ መሆኑ ለተጫዋቹም ለክለቡም ጠቀሜታ አለው።

ለመጫወት ስለሚመርጠው ቦታ

እንዲህ ነው ብዬ መምረጥ አልችልም። በገባሁበት ቦታ ሁሉ መጫወት እፈልጋለው። ዋናው አላማዬ ሜዳ ውስጥ መግባት ነው። አንዳንዴ ምን ይባላል መሰላችሁ፤ መጀመርያ አስራ ስምንት ውስጥ ለመግባት ትጥራለህ፤ ከዛ ደግሞ ወደ አስራ አንድ ውስጥ ለመግባት ታስባለህ፤ ቤስት ከሆንክ ደግሞ የትኛውም ቦታ መጫወት ትፈልጋለህ። አንዳንዴ ግብጠባቂ ግባ ብባል እገባለሁ፤ አልመርጥም አሰልጣኙ ካመነብኝ። ሆኖም ግን እኔን የሚያስደስተኝ ቦታ አሁን የምጫወትበት የመስመር አጥቂነት ቦታ ነው። ምክንያቱም ጎል ታስቆጥራለህ፣ ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን ታመቻቻለህ። ብዙ ነገሮችን ለማድረግ ለኔ የሚስማማ ቦታ ይሄ ይመስለኛል። በዚሁ ቦታ በቋሚነት ብጫወት ደስ ይለኛል።

ስለ ታታሪነቱ

ታታሪነቱ በልምምድ የመጣ ነው። በቂ እረፍትም አድርጋለው። የዛኑ ያህል ልምምዴን ሳላዛንፍ በአግባቡ ነው የምወስደው። አሰልጣኝ የሚለውን ነገር በሚገባ እቀበላለሁ። በእያንዳንዱ ጨዋታ ብቁ ለመሆን በጣም ነው የምሰራው። ሜዳም ስገባ እልህ የሚባል ነገር አለ። ያ ይመስለኛል ሜዳ ውስጥ ሁሉ ነገሬን እንድሰጥ የረዳኝ። ያን ያህልም ከባድ አይደለም። ከባዱ ነገር ማድረግ እየቻልክ አለማድረግ ነው። ሜዳ ውስጥ እንዲህ ሳደርግ ነው በጣም ደስተኛ የምሆነው። ጨዋታው ተጠናቆ ስወጣ በጣም እንደሚደክመኝ አውቃለሁ። የመስመር ተጫዋች መሆን ጉልበት እና ብዙ ነገር ይጠይቃል። ያም ቢሆን ልምምዴን በአግባቡ ማድረጌ እና እረፍት መውሰዴ የጠቀመኝ ይመስለኛል። ያው ከክብደትም አንፃር ብዙ ኪሎ ስሌለብኝ ለመመላለሱ ብዙም አይከብደኝም። (ሳቅ…)


© ሶከር ኢትዮጵያ