የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር በሁለት ከተሞች ይደረጋል

አስራ ስድስት ክለቦችን ተካፋይ የሚያደርገው የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር በሁለት ከተሞች መደረግ ይጀምራል፡፡

የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የ2013 የውድድር ዘመን የኮቪድ 19 ፕሮቶኮልን በጠበቀ መልኩ በአርባ አምስት ክለቦች መካከል በአምስት ምድቦች ተከፍሎ ከታኅሣሥ 25 እስከ ሚያዝያ 1 ድረስ በአስር ከተሞች ላይ ሲደረግ ቆይቶ ከሰሞኑ ወደ ማጠቃለያው ያለፉ አስራ ስድስት ክለቦችን ለይቶ የምድብ ጨዋታዎች መጠናቀቃቸው ይታወሳል፡፡ ከአንድ እስከ ሶስት የወጡ እንዲሁም ከአንድ ምድብ ምርጥ አራተኛን ጨምሮ በድምሩ አስራ ስድስት ክለቦች ወደ ከፍተኛ ሊግ ለመግባት ወደሚደረገው የማጠቃለያ ውድድር ያለፉ ሲሆን እነዚህም ክለቦች በቀጣይ ጨዋታቸውን የሚያደርጉበት የውድድር ከተማ መመረጡን በተለይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የውድድር ዳይሬክተር አቶ ከበደ ወርቁ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡

ውድድሩ በአዳማ እና በአሰላ ከተሞች እንደሚደረጉ ኃላፊው የገለፁልን ሲሆን ውድድሩም ከሚያዝያ 27 ጀምሮ መደረግ እንደሚጀምርም ገልፀውልናል፡፡ በዚህም ውድድር ላይ ከአንድ እስከ ስድስተኛ ደረጃ ይዘው የሚያጠናቅቁ ክለቦች ወደ 2014 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ላይ ተካፋይ የሚሆኑ ይሆናል፡፡

ወደ ማጠቃለያው ከየምድቡ ያለፉ ክለቦችን ለማስታወስ ፡-

ምድብ 1፡- ኤጄሬ ከተማ፣ ቡራዩ ከተማ፣ አምቦ ከተማ

ምድብ 2፡- ሐረር ከተማ፣ ሞጆ ከተማ፣ ድሬዳዋ ፖሊስ

ምድብ 3፡- አውሥኮድ፣ እንጅባራ ከተማ እና ጎጃም ደብረማርቆስ፣ ዳሞት ከተማ

ምድብ 4:- ሰንዳፋ በኬ፣ ጉለሌ ክፍለከተማ፣ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ

ምድብ 6፡- ሾኔ ከተማ፣ ጎባ ከተማ፣ ጎፋ ባራንቼ


© ሶከር ኢትዮጵያ