የጨዋታ ዳኞች በኮሮና ታምሰዋል

በድሬዳዋ እየተካሄደ በሚገኘው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን የሚመሩ ዳኞች በከፍተኛ ሁኔታ በኮሮና መጠቃታቸው ተሰምቷል።

13 ዋና እና 13 ረዳት በጥቅሉ 26 ዳኞችን በመያዝ በብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ እየተመሩ ድሬዳዋ የከተሙት የጨዋታው ዋና አካል የሆኑት ዳኞች ከጨዋታ ጅማሬ በፊት ምደባን የሚያስቀይር የኮሮና ስጋት ሲከሰትባቸው መቆየቱ ይታወቃል። አሁን ወደ ድሬዳዋ እየተሰማ እንዳለው መረጃ ከሆነ የኮሮና ምርመራ ከተደረገላቸው 26 ዳኞች መካከል 18ቱ በኮሮና መያዛቸው ታውቋል። ይህ ያስደነገጣቸው አወዳዳሪው አካል እና ብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ውጤቱ በመጠራጠር ኮቪድ ተገኘባቸው የተባሉት 18 ዳኞችን በመያዝ በአሁኑ ወቅት ሀረማያ ዩኒቨርስቲ ለድጋሚ ምርመራ ይዘዋቸው ሄደዋል።

አሁን አስገራሚ የሆነው የዛሬን ጨዋታ ጨምሮ ሌሎችን ጨዋታዎችን ውድድሩ እንዳይቋረጥ በማሰብ የዳኞቹ የዛሬ የምርመራ ውጤት እስኪታወቅ ድረስ ዋና ዳኛ በመሆን የሚታወቁትን ረዳት በማድረግ እንዲያጫውቱ በተቃራኒው ረዳቶቹ ደግሞ ዋና ሆነው ለማጫወት የሚገደዱበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል እየተነገረ ይገኛል።

አሳሳቢው የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ በድሬዳዋ የሚካሄደው ውድድር ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳደረ ሲገኝ እየተሰማ እንዳለው ዜና ከሆነ በርከት ያሉ የክለብ ተጫዋቾች በዚህ ችግር እየተጠቁ መሆኑ ውድድሩ በአግባቡ የመካሄዱን ነገር አጣብቂኝ ውስጥ ከቶታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ