ሪፖርት | ሰበታ ከተማ ከመመራት ተነስቶ ጣፋጭ ድል አግኝቷል

የ21ኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ መርሐ-ግብር የሆነው የባህር ዳር እና ሰበታ ከተማ ጨዋታ ጥሩ ፉክክር፣ አነጋጋሪ ውሳኔዎች እንዲሁም በድምሩ 51 ጥፋቶች ታይተውበት ሰበታ ከተማን ባለድል አድርጓል።

ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ዋና አሰልጣኙ ፋሲል ተካልኝን በሜዳ ላይ ያገኘው ባህር ዳር ከተማ በሀዋሳ ከተማ ከተሸነፈበት ስብስብ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ አድርጎ ጨዋታውን ጀምሯል። በዚህም ግርማ ዲሳሳ እና በረከት ጥጋቡን በማሳረፍ አፈወርቅ ኃይሉ እና ሳለአምላክ ተገኘን በቋሚ አሰላለፉ ተካቷል። በአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ የሚመራው ሰበታ ከተማ በኩል በሁለት ግብ ልዩነት እየመራ ነጥብ ከጣለበት የወላይታ ድቻ ጨዋታ ከግማሽ በላይ ለውጦች አድርጓል። በዚህም ፋሲል ገብረሚካኤል በጎሉ መካከል የምንተስኖት አሎን ቦታ እንዲረከብ ሲደረግ አዲስ ተስፋዬ የአንተነህ ተስፋዬን፣ ቢያድግልኝ ኤልያስ የመሳይ ጻውሎስን፣ ክሪዚስቶም ንታምቢ የዳዊት እስቲፋኖስን፣ መስዑድ መሐመድ የፉአድ ፈረጃን እንዲሁም ፍፁም ገብረማርያም የአብዱልባሲጥ ከማልን ቦታ በመተካት ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ከጨዋታው በፊት በዘነበው ከበድ ያለ ዝናብ ምክንያት ውሃ የቋጠረው ሜዳው ተጫዋቾቹ ከበድ ያለ የጨዋታ ጊዜን እንዲያሳልፉ አድርጓል። የሁለቱም ቡድን ተጫዋቾችም በተደጋጋሚ የኳስ ቅብብላቸው በሜዳው ውሃ መቋጠር ምክንያት የታሰበለት ሰው ጋር እንዳይደርስ ሲሆን ታይቷል። ይህንን እየታገሉ በጨዋታው ቀዳሚ ለመሆን የሞከሩት ደግሞ ባህር ዳር ከተማዎች ናቸው። በ7ኛው ደቂቃም አፈወርቅ ኃይሉ ከሳምሶን ጥላሁን የተቀበለውን ኳስ ከርቀት በመምታት ቡድኑን ቀዳሚ ለማድረግ ቢጥርም የግብ ዘቡ ፋሲል ገብረሚካኤል ኳሱን ወደ ውጪ አውጥቶበታል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ለተሰነዘረባቸው ጥቃት ወዲያው ፈጣን ምላሽ የሰጡት ሰበታዎች እጅግ ለግብ ቀርበው ነበር። በዚህም ኦሴይ ማውሊ ከቀኝ መስመር ኃይለሚካኤል አደፍርስ ያሻገረውን ኳስ መስዑድ መሐመድ ሞክሮት ተከላካዮች ሲመልሱት አግኝቶ መረብ ላይ አሳረፈው ሲባል ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ፍጥነት የታከለበት የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የቀጠሉት ባህር ዳሮች በ23ኛው ደቂቃ በድጋሜ የሰበታን ግብ ጎብኝተው ተልሰዋል። በዚህም ምንይሉ ወንድሙ ፍፁም ዓለሙ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ ያቀበለውን ኳስ በመጠቀም ሙከራ ያደረገ ሲሆን ፍሲል ግን ውጥኑን አክሽፎበታል። ከአስራ ሦስት ደቂቃዎች በኋላም በፍፁም አማካኝነት ሰበታ የግብ ክልል ደርሰው ሙከራ ቢያደርጉም ተከላካዮች ተረባርበው አውጥተውባቸዋል። ወደ ውጪ የወጣውን ኳስ በመዓዘን ምት ወደ ሳጥን የላከው ቡድኑም በቁመቱ አጠር ባለው ወሰኑ ዓሊ አማካኝነት ግብ ለማስቆጠር ቢቃረብም አለማየሁ ሙለታ ኳሱን ከጎል መስመር ላይ አድኗታል።

በተቃራኒው በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ እጅግ ተሽለው የተገኙት ሰበታ ከተማዎች ወደ ጎል በመድረስ ግን ተዳክመው ታይተዋል። ወሰኑ ወደ ግብነት ለመቀየር ተቃርቦ የነበረውን ኳስ ወደ ግብ ከመላኩ ከደቂቃ በፊት ግን ቡልቻ ሹራ ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥን አሻምቶት ፍፁም ገብረማርያም ባላገኘው ኳስ የፅዮንን መረብ ለመፈተሽ ጥረዋል።

ወደ ግራ ባዘነበለ መስመር ጥቃት መሰንዘራቸውን የቀጠሉት ባህር ዳሮች የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው መሪ ሆነዋል። በዚህም ምንይሉ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ወሰኑ ለአፈወርቅ ለመስጠት ሲጥር በተጫዋቾቹ መካከል (በወሰኑ እና አፈወርቅ) የነበረው ኃይለሚካኤል አደፍርስ ኳሱን በራሱ መረብ ላይ አሳርፎታል። አጋማሹም በመገባደጃው ላይ በተቆጠረው ብቸኛ ጎል ተገባዷል።

በመጀመሪያው አጋማሽ አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ያላደረጉት ሰበታ ከተማዎች ገና አጋማሹ በተጀመረ በ5ኛው ደቂቃ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ወደ ጨዋታው ተመልሰዋል። በዚህም ኦሲ ማውሊ ከርቀት የተገኘን የቅጣት ምት በመጠቀም ወደ ግብ የመታውን ኳስ ፅዮን ሲመልሰው የተተፋውን ኳስ ለማግኘት ሲሮጥ የነበረው አለማየሁ በምንይሉ ጥፋት ተሰርቶበታል በሚል የጨዋታው የመሐል ዳኛ ተፈሪ አለባቸው የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተዋል። የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምትም ፍፁም ገብረማርያም በ53ኛው ደቂቃ ወደ ግብነት ቀይሮት ሰበታ አቻ ሆኗል። ቡድኑ ገና በአጋማሹ መባቻ ደቂቃ ላይ ግብ ካስቆጠረ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም ወደ መሪነት የሚያሸጋግረውን ጎል በመስዑድ አማካኝነት ለማግኘት ጥሮ ሳይሳካለት ቀርቷል።

በመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ እና በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ላይ ሁለት አይነት ስሜት ያስተናገዱት የባህር ዳር ከተማ ተጫዋቾች በ64፣ 65 እና 66ኛው ደቂቃ በሞከሯቸው ተከታታይ ሦስት ኳሶች መሪ ለመሆን ጥረዋል። በቅድሚያም ወሰኑ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ለመጠቀም ጥሮ ሲመክንበት በመቀጠል ደግሞ ፍፁም ከሳጥኑ ጫፍ ሆኖ ወደ ግብ በመታው ኳስ ግብ ለማስቆጠር ጥሯል። የፍፁም ሙከራ ከተደረገ ከጥቂት ሰከንዶች በኋላም ሰበታ የፍፁም ቅጣት ምት እንደዲያገኝ ጥፋት ሰርቷል የተባለው ምንይሉ ጥሩ ኳስ ወደ ፋሲል ቢልክም የተመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ወደ ውጪ ወጥቷል። እነዚህ ሙከራዎች ከተደረጉ በኋላም በ71ኛው ደቂቃ ሰበታ የግብ ክልል የደረሱት ባህር ዳሮች በፍፁም ሌላ ሙከራ ግብ ፍለጋቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።

ጥሩ ጥሩ የግብ ማግባት ሙከራዎችን ማስመልከት የቻለ የሁለቱ ቡድኖች የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በ75ኛው ደቂቃ መሪ ለማግኘት ተቃርቦ ነበር። በተጠቀሰው ደቂቃም ምንይሉ ከመሐል መሬት ለመሬት የተላከለትን ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ በመጠቀም ግብ ጠባቂው ፋሲልን ፈትኖ ነበር። ጨዋታው ቀጥሎም በ81ኛው ደቂቃ የሰበታው የመሐል ተከላካይ አዲስ ተስፋዬ ግርማ ዲሳሳ ላይ ጥፋት በመስራቱ በሁለተኛ የቢጫ ካርድ (መጀመሪያ ፍፁም ላይ ጥፋት ሰርቶ ነበር) ከሜዳው ተሰናብቷል። ቀይ ካርዱን ተከትሎ የቁጥር ብልጫ የተወሰደባቸው ሰበታዎች በ85ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ወደ ሜዳ በገባው ዱሬሳ ሹቢሳ ጎል መሪ ሆነዋል።

በተጠቀሰው ደቂቃም ዱሬሳ ከርቀት ሳጥን ላይ የተጣለውን ኳስ ማውሊ በደረቱ ሲያመቻችለት በቀጥታ ወደ ግብነት ቀይሮታል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በተከላካይ ክፍላቸው ላይ ከፍተኛ የትኩረት ማነስ ችግር የታየባቸው ባህር ዳሮች በጭማሪው ደቂቃ ፍፁም በሞከረው ጥሩ የቅጣት ምት አቻ ለመሆን ጥረው ነበር። ነገርግን ኳሱን ፋሲል በጥሩ ቅልጥፍና ወደ ውጪ አውጥቶታል። ጨዋታውም 10 ደቂቃዎች በጎዶሎ ተጫዋች በተጫወቱት ሰበታ ከተማዎች አሸናፊነት ተገባዷል።

ውጤቱን ተከትሎ ሦስት ነጥብ ያስረከቡት ባህር ዳር ከተማዎች በ31 ነጥቦች ያሉበት 4ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ ከመመራት ተነስተ ሦስት ነጥብ ያገኙት ሰበታ ከተማዎች ደግሞ ነጥባቸውን 26 አድርሰው ወደ 7ኛ ደረጃ ከፍ ብለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ