በሁለት ምደብ ተከፍሎ በአስራ ሦስት ቡድኖች መካከል እየተካሄደ የሚገኘው የአዲስ አበባ ከ17 ዓመት በታች የታዳጊዎች ውድድር የመጀመርያው ዙር ዛሬ ተጠናቀቀ።
የውድድር ዓመቱ አጋማሽ የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች በሁለት ሜዳዎች ተከናውነዋል። በመከላከያ ሜዳ መከላከያና ዲኤፍቲን ያገናኘው ጨዋታ በሁለት አቻ ውጤት ተጠናቋል። ሁለት መልክ በነበረው በዚህ ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ በአንፃራዊነት ወደ ጎል በመድረስ የተሻሉ የነበሩት ባለሜዳዎቹ መከላከያዎች በ13ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር ከተከላካይ ጀርባ የተጣለለትን ኳስ አንድ ተካላካይ ቆርጦ በማለፍ ከግብጠባቂው ጋር ብቻውን ተገናኝቶ ግሩም ጎል ሙሉቀን በቀለ ለመከላከያ የመጀመርያውን ጎል አስቆጥሯል።
በእንቅስቃሴ ሜዳ ውስጥ ያልነበሩት ዲኤፍቲዎች በመከላከያ የተወሰደባቸው ብልጫ መቆጣጠር አቅቷቸው በተመሳሳይ አጨዋወት ሙሉቀን ፍጥነቱን በመጠቀም በ23ኛው ደቂቃ ተጨማሪ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ የጎሉን መጠን ከፍ ማድረግ ችሏል። ጨዋታው ተቀዛቅዞ ቀጥሎ ወደ እረፍት መዳረሻ ላይ የዲኤፍቲ አጥቂ ሄኖክ
ኤርሚያስ ላይ የመከላከያው ግብጠባቂ አማን ከድር በሰራበት ጥፋት የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት በአስደናቂ ሁኔታ የመከላከያው ግብጠባቂ አማን ከድር አድኖታል። ግብጠባቂ አማን አቋቋሙ ታይሚንግ አጠባበቁ ቅልጥፍናው እና የሚያድናቸውን ኳሶች ለተመለከተ ወደፊት ተስፋ የሚጣልበት ጥሩ ግብጠባቂ እንደሚወጣው መታዘብ ችለናል።
ከእረፍት መልስ የጨዋታውን ሌላኛውን መልክ ያስመለከተን ሲሆን ሙሉ ለሙሉ ኳሱን ተቆጣጥረው በርከት ያሉ የጎል አጋጣሚዎች በመፍጠር ተሽለው የቀረቡት ዲኤፍቲዎች ነበሩ። ወደ ጨዋታ የሚመልሳቸውን ጎል በሄኖክ ኤርሚያስ የግል ጥረት ታክሎበት በ50ኛው ደቂቃ ዲኤፍቲዎች ጎል ማስቆጠር ችለዋል። ሄኖክ እጅግ አስደናቂ አቅም ያለው ታዳጊ ተጫዋች መሆኑን በየጫዋታዎቹ እያስመለከተን ሲገኝ ዛሬ ያስቆጠረውም ጎል ስምንተኛ ሆኖ ተመዝግቧል።
ተዳክመው የመጡት መከላከያዎች በቀጥተኛ አጨዋወት ሙሉቀንን ትኩረት ያደረገ ረጃጅም ኳሱ ለመጫወት ቢያስቡም ኳሱ እየባከነ ተመልሶ እራሳቸውን ጫና ውስጥ ይከቷቸው ነበር። በሁለተኛው ጎል በፍጥነት በማስቆጠራቸው የተነቃቁት ዲኤፍቲዎች ብዙም ሳይቆይ ከሳጥን ውጭ ተከላካይ እዮሳፍንት ግርማ ባስቆጠራት ጎል ሁለት አቻ መሆን ችለዋል።
ዲኤፍቲ በሁሉም ረገድ እንደወሰደው ብልጫ እና ከሁለት ለዜሮ መመራት አቻ መሆናቸውን ተከትሎ ተጨማሪ ጎሎችን በማስቆጠር ጨዋታውን የሚያሸንፉበትን የጎል ዕድል አግኝተው የነበረ ቢሆንም ከአጨራረስ ችግር ምክንያት ጨዋታው በአቻ ውጤት ለመጠናቀቅ ተገዷል።
በዚሁ ምድብ በመድን ሜዳ በተካሄደ ሁለት ጨዋታ አስቀድሞ ሀሌታ ከአፍሮ ፅዮን አገናኝቶ በሁለት አቻ ውጤት ሲጠናቀቅ ለሀሌታ አብዱልመጂድ መድድ እና አንዱዓለም ታምራት ሲያስቆጥሩ የአፍሮ ፅዮን ሁለት ጎሎች ፉአድ ቢንያም ማስቆጠር ችሏል።
በሌላ ጨዋታ የምድቡ መሪ እና በቀድሞ ድንቅ አጥቂ መስፍን አሕመድ (ጢቃሶ) እየሰለጠነ የሚገኘው ኢትዮጵያ መድን ሣራ ካኒዛሮን በሰፊ የጎል ልዩነት ስድስት ለሁለት በሆነ ውጤት አሸንፏል። የመድንን ጎሎች በየጨዋታዎቸ ጎል ማስቆጠር እና ሐት ትሪክ በመስራት ለወደፊቱ ድንቅ አጥቂ እንደሚወጣው እያስመለከተን የሚገኘው ሳላዲን አብደላ ዛሬም ሦስት ጎሎችን በማስቆጠር ሐት ትሪክ ሰርቷል። ሳላዲን የውድድሩ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትን በአስራ ሁለት ጎሎች እየመራ መሆኑም ይታወቃል። ቀሪዎችን ጎሎች ይትባረክ ሰጠኝ ዮናታን እሸቱ እና ዋቅጅራ ሽፈራው አስቆጥረዋል። የሳራ ካኒዛሮን ሁለት ጎሎች ናትናኤል ደበበ እና ሰኢድ ሽኩር ማስቆጠር ችለዋል።
የአንደኛው ዙር ማጠቃለያ
ውድድሩን የሚመራው አካል የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከመርሐግብር አወጣጥ ጀምሮ ውድድሩ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ በማድረግ እና ታዳጊዎቹ ራሳቸውን የሚያሳዩበት ምቹ ሜዳዎችን በማዘጋጀት እስካሁን ያሳየው በጠንካራ ጎኑ የሚወሰድ ነው። ሆኖም ውድድሩ የኮቪድ ፕሮቶኮልን የተጠበቀ ሆኖ ይካሄዳል ቢባልም እስካሁን ይሄን የሚያሳይ ሥራ አለመሰራቱ በድክመት የሚነሳ ሲሆን በሁለተኛው ዙር ተስተካክሎ ይቀርባል ብለን እንገምታለን። ከዚህ ውጭ በዕድሜ በእኩል የተሻለ ቡድን ይዘው የቀረቡ እንዳሉ ሁሉ የዛኑ ያህል ተገቢ ያልሆነ ዕድሜ ይዘው የቀረቡ ቡድኖች እንዳሉ ታዝበናል። በአጠቃላይ ጥሩ ቡድን ይዞ በመቅረብ ለነገ ተስፋ የሚጣልባቸው ታዳጊዎች ያሉባቸው ቡድኖች እንዳሉ ሁሉ የዛኑ ያህል ለተሳትፎ ካልሆነ በቀር በሁሉም መልኩ ብዙም ውጤታማ
ያልሆኑ ቡድኖች እንዳሉ ተመልክተናል።
© ሶከር ኢትዮጵያ