ሉሲዎቹ ሁለተኛውን የአቋም መለኪያ ጨዋታም አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ከደቡብ ሱዳን አቻው ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ አከናውኖ 3ለ0 አሸንፏል፡፡

10፡00 ሰዓት ሲል በጀመረው የዛሬው ሁለተኛ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ካለፈው መርሀግብር አንፃር ቀዝቀዝ ያለ እንደነበር መመልከት ችለናል፡፡ የመጀመሪያዎቹን አስራ አምስት ደቂቃዎች ከሙከራ የራቀ ቢሆንም በሂደት ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተሻለ የአጨዋወት መንገድ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ሲደርስ ታይቷል። በተለይም ደግሞ ቡድኑ ሴናፍ ዋቁማ በተሰለፈችበት የግራ መስመር በኩል የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ ተስተውሏል። ደቡብ ሱዳኖች በበኩላቸው የሉሲዎቹን የኳስ ቅብብል ለማቋረጥ እና የሚያገኟቸውን ኳሶች ከርቀት በመሞከር ግብ ለማግኘት ሲታትሩ አምሽተዋል። በዚህ አጨዋወትም ቡድኑ በ10ኛው ደቂቃ ጆሴፒ ማኩዊይ የሉሲዎቹን የመከላከል ድክመት ተጠቅማ ከቀኝ መስመር ጥቃት ፈፅማ የነበረ ቢሆንም ንግስቲ መዐዛ ዕድሉን አምክናዋለች።

በአንድ ሁለት ቅብብሎሽ በቀላሉ ወደ ደቡብ ሱዳን የግብ ክልል መድረስ የጀመሩት የአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ተጫዋቾች ሎዛ አበራ ከርቀት ሞክራ ካልዳ ሀሰን በመለሰችባት ሙከራ የተጋጣሚያቸውን የግብ ክልል ጎብኝተው ተመልሰዋል። በ26ኛው ደቂቃ ግን ቡድኑ ወደ ደቡብ ሱዳን አምርቶ ሲመለስ ያለምንም አለነበረም። በዚህም ቡድኑ መሪ የሆነበትን ኳስ ከመረብ አገናኝቷል።
በደቂቃውም እፀገነግ እና ሎዛ በፈጠሩት ድንቅ ጥምረት የመጨረሻ ኳስ ከሎዛ ያገኘችው ሴናፍ ኳስ እና መረብን አገናኝታለች። መመራት የጀመሩት ደቡብ ሱዳኖች አብዛኞቹን የዚህኛውን አጋማሽ ደቂቃዎች ወደ መከላከሉ አመዝነው ሲጫወቱ ታይቷል። በተቃራኒው ሉሲዎቹ ደግሞ እጅግ በርከት ያሉ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢችሉም ተጨማሪ ጎሎችን ለማስቆጠር ሲቸገሩ ነበር። በተለይ ደግሞ ሎዛ አበራ፣ ሴናፍ ዋቁማ እና ዮርዳኖስ ምዑዝ በተመሳሳይ ግልፅ የግብ ማግባት ዕድሎችን ቢያገኙም ሳይጠቀሙ የቀሩበት አጋጣሚ አስቆጪዎች ነበሩ፡፡

ከእረፍት መልስ ሉሲዎቹ የበላይነት ሲኖራቸው ደቡብ ሱዳኖች ደግሞ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ በመከላከሉ ላይ ትኩረት አድርገው ነገር ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ስህተት በመጠቀም ከርቀት የተገኙትን ጥቂት ዕድሎች ወደ ግብነት ለመቀየር ጥረዋል። ዮርዳኖስ ምዑዝ ገና ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ አንድ ደቂቃ ውስጥ ያለቀለትን ነፃ ኳስ አግኝታ አስቆጠረች ተብሎ ቢጠበቅሞ ሳትጠቀምበት ቀርታለች፡፡ የስህተት ኳስ ላይ ትኩረትን ያደረጉት ደቡብ ሱዳኖች 49ኛው ደቂቃ ላይ ጀስሊን ፈኪ የግል አቅሟን ተጠቅማ ለያሙሲ ጁካ ሰጥታት አማካዩዋም ከሳጥን ውጪ አክርራ መታ እንደምንም ንግስቲ መዐዛ አድናባታለች፡፡ ብልጫ ማሰየት ቢችሉም ካለፈው ጨዋታ አንፃር በተወሰነ መልኩ ለመፈተን የተገደዱት ሉሲዎቹ 51ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ጎግ አግኝተዋል፡፡ በዚህም ሴናፍ ዋቁማ ከሳጥን ውጪ ሁለት ተጫዋቾችን አልፋ በቀጥታ አክርራ መታ ለራሷ እና ለሀገሯ ሁለተኛ ጎሏን አስመዝግባለች፡፡ 60ኛው ደቂቃ ላይም በድጋሜ ሉሲዎቹ ለግብ ቀርበው ነበር። በዚህም አረጋሽ ከመስመር በቀጥታ ወደ ጎል መታ ግብ ጠባቂዋ ስትመልሰዎ ሎዛ ከጎሉ ትይዩ ሆና ብታገኘውም ኳሱ ወደ ውጪ ወጥቶባታል።

ጥረት ከማድረግ ያልተቆጠቡት የሉሲዎቹ አባላት ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ክልል እየደረሱ ተጨማሪ ጎልን ለማከል በተደጋጋሚ ቢሞክሩም ይታይባቸው የነበረው ጉጉት ውጥናቸው እንዳይሰምር አድርጎ ጨዋታው ቀጥሏል። 87ኛው ደቂቃ ላይ ግን መሳይ ተመስገን ከቅጣት ምት አጠገቧ ለነበረችሁ አረጋሽ ሰጥታት ባለ ግራ እግሯ ተጫዋች ሶስተኛዋን ጎል በማስቆጠር ጨዋታው 3ለ0 በሆነ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡





© ሶከር ኢትዮጵያ