ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የድሬዳዋ ቆይታ ሁለተኛ የጨዋታ ሳምንት በነበረው የ18ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር የታዘብናቸውን ክለብ ነክ ጉዳዮች እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል።

👉 የወላይታ ድቻ ድንቅ የጨዋታ ቀን

ገና ከጅምሩ በሊጉ ከሚገኙ ክለቦች ሁሉ ቀደመው የአሰልጣኝ ቅያሬ ያደረጉት ወላይታ ድቻዎች ውሳኔያቸው ምን ያህል ትክክለኛ እንደነበር ቡድኑ እያሳየ ከሚገኘው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ሆነ ከሚያስመዘግበው ውጤት እየተመለከትን እንገኛለን።

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት የቡድኑን ቁልፍ ተጫዋቾች በኮቪድ ምክንያት መጠቀም ያልቻሉት ወላይታ ድቻዎች በፋሲል ከነማ ሽንፈትን ቢያስተናግዱም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግን ድሬዳዋ ከተማን 3-1 በመርታት ወደ አሸናፊነት ተመልሰዋል።

በድሬዳዋው ጨዋታ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ በተጋጣሚያቸው ድሬዳዋ ከተማ እንደተወሰደባቸው ብልጫ የማሸነፉ ሚዛን ወደ ድሬዳዋ ከተማ ያደላ ቢመስልም ከሁለተኛው የውሀ ዕረፍት መልስ ፍፁም የተለየ ወላይታ ድቻን ለመመልከት በቅተናል። ዕረፍቱ የፈጥረለትን አጋጣሚ በአግባቡ በመጠቀምም በድሬዳዋ ብልጫ ምክንያት ከራሱ የግብ ክልል መውጣት አቅቶት የነበረው ድቻ ጨዋታውን ማመጣጠን ችሏል። በዚህም የድሬዳዋ ከተማን እንቅስቃሴ ከማክሰም ባለፈ ቀስ በቀስ አንድ ለአንድ እየቀጠለ በነበረው ጨዋታ በስንታየሁ መንግሥቱ እና በረከት ወልዴ ባስቆጠሯቸው ግቦች ቡድኑ አሸንፎ ለመውጣት በቅቷል።

👉 መሻሻል የተሳነው ወልቂጤ ከተማ

እንደአለመታደል ሆኖ በሀገራችን እግርኳስ ሜዳ ላይ የሚታይን መገለጫ የሆነ አንዳች የጨዋታ መንገድን ለመከተል የሚጥሩ ቡድኖችን ፈልጎ ማግኘት በጣም ከባድ ነው። አሁን አሁን በተወሰነ መልኩ ግን መሰል መገለጫ ያላቸውን ቡድኖች በሊጉ እየተመለከትን እንገኛለን። ከእነዚህም መካከል ወልቂጤ ከተማ አንዱ ነው።

ከተጫዋቾች ምርጫ አንስቶ ቡድኑ በተጋጣሚዎቹ ላይ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ወስዶ ተደጋጋሚ ዕድሎችን በክፍት ጨዋታ በተለይም በቁጥር በርከት አርገው ከሚያሰልፉቸው የአጥቂ አማካዮች መነሻነት የመፍጠር ፍላጎት ያለው ቡድን እንደሆነ በሊጉ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ የውድድር ዘመን ታዝበናል። ከዚህ በተጨማሪ ዐምና ከተሰረዘው የውድድር ዘመን አንስቶ የነበረው ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት መገለጫው የነበረ ቡድን ነበር።

ታድያ በዚህ ኳስን ቁጥጥር መሰረት ባደረገው የጨዋታ አቀራረብ ቡድኑ ከጨዋታ ጨዋታ እምርታዎችን ለማሳየት እየተቸገረ ነው። ቡድኑ የውድድር ዘመኑን ሲጀምር አንስቶ በንፅፅር ውጤታማ በነበረባቸው ጊዜያት ሁሉ ይነሱ የነበሩ ችግሮች አሁንም በችግርነት ይነሳሉ። ይባሱኑ ብሎ ከጥቂት ሳምንታት ወዲህ ደግሞ በንፅፅር በጥሩነት ይጠቀሱ የነበሩ የቡድን ጥንካሬዎች ሁሉ ቀስ በቀስ እየተዳከሙ ይገኛሉ። የመጨረሻ አምስት ጨዋታዎች ውጤቱም ይህን በደንብ የሚገልፁ ናቸው።

ወልቂጤ ገና ከጅምሩ ኳስን መስርቶ ለመውጣት የሚያደርገው ጥረት ላይ ብሎም ኳሶችን በመሀል ሜዳ ላይ ከመቆጣጠር ባለፈ ሳይቆራረጡ ወደ ላይኛው የሜዳ ክፍል ማሳደግ እንዲሁም የተገኙ ዕድሎችን ወደ ግብነት መቀየር ላይ ከፍተኛ ችግሮች ነበሩበት። አሁን ላይ ደግሞ ከእነዚህ ችግሮች በተጨማሪ ግለሰባዊ ስህተቶችን አብዝቶ የሚሰራ የተከላካይ መስመር እንዲሁም ዕድሎችን ለመፍጠር የሚቸገር ቡድን እየሆነ መጥቷል።

በውድድር ዘመኑ ሒደት ቡድኑ ከጨዋታ ጨዋታ እያሻሻለ ይሄዳል ተብሎ ቢገመትም ከመሻሻል ይልቅ ግን ቀስ በቀስ እየተዳከመ ይገኛል። በመሆኑም በአፋጣኝ ከዚህ ውጤት አልባ ጉዞ የማይወጣ ከሆነ ወደ ወራጅ ቀጠኔው አሰየተጠጋ ከመሆኑ አንፃር የአሰልጣኙ ህልውናም አደጋ ውስጥ መግባቱ የሚቀር አይመስልም።

👉 በቀናት ልዩነት ፍፁም የተለያየ መልክ የነበረው ሀዋሳ ከተማ

ሀዋሳ ከተማ ከቀናት በፊት ኢትዮጵያ ቡናን ሲረታ ጥንቃቄ በተሞላበት አቀራረብ እንደ ቡድን በአስደናቂ ትጋት መሉ ሦስት ነጥብ ይዞ መውጣት ችሎ ነበር። በቀናት ልዩነት ግን ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በመረጡት እና ውጤታማ ባደረጋቸው አቀራረብ በተቃራኒው በእጅጉ ተፈትነው ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።

በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ሀዋሳ ከተማዎች ለተጋጣሚው እጅግ ፈታኝ በነበረ እና ከተወሰኑ የጨዋታ ክፍለጊዜዎች በቀር በትጋት እንደቡድን ተደራጅተው በመከላከል በአንድ የቆመ ኳስ የጨዋታውን ውጤት ወስነው መውጣታቸው ይታወሳል። በዚህኛው ጨዋታ ደግሞ በተቃራኒው ሀይቆቹ የተሻለ የጨዋታ ቁጥጥር ይዘው ተደጋጋሚ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን በፈጠሩበት ጨዋታ በጥንቃቄ ሲከላከሉ የነበሩት ጅማ አባ ጅፋሮች በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ በተመስገን ደረሰ አማካኝነት በተቆጠረች የመልሶ ማጥቃት ግብ እስከ ጨዋታው መጠናቀቂያ ድረስ ሲመሩ ቢቆዩም ሀዋሳ ከተማዎች በ90ኛው ደቂቃ ዓባይነህ ፊኖ ባስቆጠራት ግብ አቻ ተለያይተው ለመውጣት ችለዋል።

ቡድኑ በመጀመሪያው ዙር አዲስ አበባ ላይ በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ቡናን ጥንቃቄ መርጦ በብሩክ በየነ ብቸኛ ግብ ቢረታም በተመሳሳይ በቀጣዩ ጨዋታ ደግሞ ምኞት ደበበ በራሱ ላይ እና በተቃራኒ ባስቆጠራቸው ግቦች በፍፁም መከላከል ከገጠማቸው ጅማ አባ ጅፋር ጋር አቻ መለያየታቸው ይታወሳል። የዚህ ሳምንት ጨዋታም የመጀመሪያው ዙር ኮፒ መሆኑ አስገራሚ ግጥምጥሞሽ ሆኖም አልፏል።

👉 ከአውሮፕላን እንደወረዱ ውድድር ያደረጉት ሀዲያ ሆሳዕናዎች

ቀጣይነት ያለው የገቢ ምንጭ በሌለበት የሀገራችን እግርኳስ ያልቅጥ እየጨመሩ የመጡ የተጫዋቾች ዝውውር እና ወርሃዊ ደሞዝ ወጪዎች የክለቦችን ህልውና አደጋ ውስጥ እየከተቱ መጥተዋል። በተለይ የከተማ አስተዳደር ክለቦች ለዚህ ያለልክ እየናረ ለመጣው የዝውውር እና የደሞዝ ክፍያዎች ግንባር ቀደም ሚናን በተጫወቱ ማግስት በተለይ የከተማ አስተዳደር (ዞን አመራሮች) ለውጥ በተደረገ ቁጥር የህልውናቸው ጉዳይ አጣብቂኝ ውስጥ ሲገባ በተደጋጋሚ ተመልክተናል።

በክረምቱ የዝውውር መስኮት በርካታ ቁጥር ያላቸውን ተጫዋቾች በከፍተኛ የዝውውር ሂሳብ በተለይም ከአዳማ ከተማ ያስኮበለለው ሀዲያ ሆሳዕና እነዚሁን ተጫዋቾች ሲያዘዋውር በማማለያነት የተቀመውን ጥቅማጥቅሞችን ለመክፈል ቀርቶ መሠረታዊ የሚባለውን የተጫዋቾችን እና የአሰልጣኞች ቡድን አባላትን ወርሃዊ ደመወዝን ለመክፈል ተቸግሯል። ቡድኑ ሊጉን ሲጀመር መልካም የሚባል ውጤቶችን ቢያስመዘግብም በጊዜ ሂደት ከሜዳ ውጪ ያሉ ሁነቶች በሜዳ ውስጥ ውጤታማነቱ ላይ ተግዳሮት እየሆኑ መጥተዋል።

የድሬዳዋው ውድድር ከመጀመሩ በፊት በነበሩት የዕረፍት ቀናት ቡድኑ መቀመጫውን በዝዋይ ከተማ አድርጎ ዝግጅት ሲያደርግ የቆየ ቢሆንም ተጫዋቾች በተደጋጋሚ ያነሱት ያልተከፈለ ደመወዝ እና ጥቅማጥቅም ጥያቄ በወቅቱ ምላሽ ባለማግኘቱ በ18ኛ ሳምንት ከአዳማ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ የመካሄድ ነገሩ ጥያቄ ውስጥ ገብቶ ነበር። ሆኖም የክለቡ አመራሮች ባደረጉት ርብርብ የተጫዋቾቹ ጥያቄ በተወሰነ መልኩ ምላሽ በማግኘቱ በጨዋታው ዕለት ከጨዋታው ጥቂት ሰዓታት በፊት ወደ ድሬዳዋ ያመሩት አባላቱ በጥቂት ሰዓታት ልዩነት አዳማ ከተማን ገጥመው አንድ አቻ መለያየት ችለዋል።

በተመሳሳይ ከቀናት በፊት የሀዲያ ሆሳዕና ከ20 ዓመት በታች ቡድንም አሰላ ላይ ከሀላባ ከተማ ለነበራቸው ጨዋታ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ቡድኑ ተጫዋቾችን መላክ ባለመቻሉ በተወሰኑ ቀና ሰዎች ትብብር በመጨረሻ ሰዓት ከሆሳዕና ጉዞ ጀምረው አዳራቸው በአዳማ ከተማ በማድረግ በማግስቱ ጠዋት ወደ አሰላ ጉዞ በማድረግ ጨዋታቸውን አድርገው ተመልሰዋል።

በሀገራችን እግርኳስ በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ባልተከፈለ ደመወዝ (ጥቅማጥቅም) ለቀናት ልምምድ ማቆም በዚህም የመካሄዳቸው ነገር ጥያቄ ውስጥ የገቡ መርሐ ግብሮች ጉዳይ በቀስ በቀስ እየተለመዱ ከመምጣታቸው የተነሳ ትኩረት እስከመነፈግ ደርሰዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በተሰረዘው የውድድር ዘመን ከሊጉ ለመሰናበት ቋፍ ላይ የነበረው ቡድን በውድድሩ መሰረዝ አማካኝነት ያገኘውን ሁለተኛ ዕድል በመሰል ከሜዳ ውጪ ባሉ ሁነቶች የቡድኑ መንፈስ እንዳይጎዳ ብሎም ውጤቱ እንዳያሽቆለቁል የሚመለከታቸው አካላት የተቻላቸውን ጥረት በአስቸኳይ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

👉 ባህር ዳር ከተማ በድጋሚ ፋሲል ከነማን አስጥሏል

በአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ እየተመሩ በሰንጠረዡ ኛናት በኩራት የተሰየሙት ዐፄዎቹ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ከባህርዳር ከተማ ከፍተኛ ፈተና ገጥሟቸው ነጥብ ለመጋራት ተገደዋል። በዚህም ከተከታያቸው ኢትዮጵያ ቡና ጋር ያላቸው የነጥብ ልዩነት ወደ ዘጠኝ ዝቅ ብሏል። በከፍተኛ የፉክክር ስሜት በሚታጀበው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ፤ ባህርዳር ከተማዎች በመጀመሪያውም ሆነ በሁለተኛው ዙር ከጠንካራው ፋሲል ከነማ ነጥብ ተጋርተው መውጣት ችለዋል።

ከውጤት ባለፈም ሜዳ ላይ ዓይን የሚስብ እና በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት በጉሽሚያዎች በተሞላ የጋለ እንቅስቃሴ የታየበት ጨዋታ 0-0 እንደመጠናቀቁ ሳይሆን አደገኛ ሙከራዎችንም አሳይቶናል። ሦስተኛ ደረጃ ላይ እንዳለ ቡድንም ባህር ዳር ፋሲል በተከታታይ ከገጠማቸው ቡድኖች የተሻለ ፈተና እንዲገጥመው አድርጓል። በተከታዮቹ ተደጋጋሚ ነጥብ መጣል የተነሳ ቀስ እያለ ልዩነቱን እያሳፋ ይገኝ የነበረው ፋሲል ከነማ በባህርዳሩ ጨዋታ ነጥብ መጣሉን ተከትሎ እርግጥ አሁንም ያለው የነጥብ ልዩነት ሰፊ ቢመስልም በተወሰነ መልኩ በዋንጫ ፉክክሩ ላይ ነፍስ የዘራ ውጤት ሆኗል።

👉 በመጠኑም ቢሆን የተሻሻለው አዳማ ከተማ

በመጀመሪያው ዙር የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እጅግ አስደንጋጭ አጀማመርን ያደረጉት አዳማ ከተማዎች በሁለተኛው ዙር ከሊጉ ግርጌ ተላቀው በሊጉ የሚያከርማቸውን ውጤት ለማምጣት በማሰብ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ተጫዋቾች በውድድሩ አጋማሽ በነበረው የዝውውር መስኮት ማስፈረማቸው ይታወቃል።

በቡድኑ አከርካሪዎች ላይ ያስፈረማቸው የውጪ ሀገር ዜግነት ያላቸው ግብጠባቂውን ሴኩምባ ካማራ (ግብጠባቂ)፣ ኤሊሴ ጆናታን (አማካይ) ፣ ላሚን ኩማር (ተከላካይ) ፣ ማማዱ ኩሊባሊ (አጥቂ) በሙሉ ግልጋሎታቸውን ለመጀመርያ ጊዜ ባገኙበት በዚሁ ጨዋታ በመጀመሪያው ዙር ከነበረው አዳማ ከተማ የተለየን የመጀመሪያ ተመራጭ ተጫዋቾችን ተመልክተናል። በመጀመሪያው ዙር ከቡድኑ ጋር ያልነበሩ ስድስት ተጫዋቾችን በመጀመሪያ ተመራጭነት ያስጀመረው ቡድኑ በርካታ ተጫዋቾችን በአጋማሹ እንደማዘዋወሩ ከቡድን ውህደት ጋር በተያያዘ ሊቸገር እንደሚችል ይገመታል።

በ18ኛ ሳምንት ጨዋታ ግን አዳማ ከተማዎች ተስፋ የሚሰጥን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ አሳይተዋል። በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ በጥሩ የመከላከል አወቃቀር ባለፈ በቀጥተኛ ቅብብሎሽ ላይ የተመሰረቱ ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች ጥሩ ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችንም መፍጠር ችለዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃ በፈጣን መልሶ ማጥቃት አዳማ ከተማን መሪ ያደረገችውን ግብ በአብዲሳ ጀማል አማካኝነት ብትቆጠረም ነጥብን የተራቡት አዳማ ከተማዎች ከግቧ መቆጠር ወዲህ በፍጥነት ከግቧ በፊት በነበሩት ደቂቃዎች የነበራቸው የማጥቃት ፍላጎታቸው ፍፁም በመዳከሙ የተነሳ ከተጋጣሚያቸው ከፍ ያለ ጫናን በመጋበዝ በስተመጨረሻም የአቻነቷን ግብ ለማስተናገድ ተገደዋል።

በ8 ነጥብ በሊጉ ግርጌ የሚገኙት አዳማ ከተማዎች ምንም እንኳን ተጋጣሚያቸው ሀዲያ ሆሳዕና በድህረ ጨዋታ ቀናት ያሳለፉት ፈታኝ ሂደቶች በጨዋታው ላይ ያሳደሩት ተፅዕኖ እንዳለ ሆኖ አዳማ ከተማዎች በመከላከሉ ረገድ በተለይ ስህተት የማያጣቸውን ግብ ጠባቂዎቹን የተካበት እንዲሁም በማጥቃቱ ረገድ በኤልያስ ማሞ እና አብዲሳ ጀማል መካከል እየተፈጠረ የሚገኘው ተግባቦት ለቡድኑ ተስፋ የሚሰጥ ያደርገዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ