በ18ኛ የጨዋታ ሳምንት ትኩረት የሳቡ አሰልጣኝ ነክ ጉዳዮች እና ዓበይት አስተያየቶችን በዚህ ፅሁፍ ተዳሰዋል።
👉 የሙሉጌታ ምህረት ያልተጠበቀ የደስታ አገላለጽ
ሀዋሳ ከተማን የማሰልጠን ኃላፊነትን ባሳለፍነው ዓመት አጋማሽ የተረከበው የቀድሞው ድንቅ አማካይ ሙሉጌታ ምህረት በሜዳው ጠርዝ እንደ ተጫዋችነት ዘመኑ ሁሉ እርጋታን የተላበሰ ባህሪ እንዳለው ተመልክተናል።
በዚህ ሳምንት ሀዋሳ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ባደረገው ጨዋታ በ90 ደቂቃ ጥቅል እንቅስቃሴ የተሻለ የነበረው ቡድኑ ተመርቶ በመጨረሻ ደቂቃ ባስቆጠሯት የአቻነት ግብ አንድ አቻ በተለያየበት ጨዋታ ሙሉጌታ ምህረት ስሜቱን የገለፀበት መንገድ ከወትሮው የተለየ ነበር። አባይነህ ፊኖ የአቻነቷን ግቧን ሲያስቆጥር አሰልጣኝ ሙሉጌታ እጁ ላይ ይዟቸው የነበሩትን ሁለት የውሃ መያዣ ፕላስቲክ ጠርሙሶች ወደ መሬት በስሜት የወረወረበት መንገድ የተለየ ነበር።
👉 በቡድን መሪያቸው የተመሩት ፋሲል ከነማዎች
በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ የጨዋታ ሳምንት መርሐ ግብር በተጠባቂው ጨዋታ ፋሲል ከነማዎች ባህርዳር ከተማን ሲገጥሙ ያለ ዋና አሰልጣኛቸው ሥዩም ከበደ እና ምክትሎቻቸው ነበር።
ከቀናት በፊት የልደት በዓላቸውን በድምቀት ከቡድን አባላቶቻቸው ጋር ያከበሩት አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ከእነ ረዳቶቻቸው ኃይሉ ነጋሽ እና ሙሉቀን አቦሀይ ጋር ሜዳ ላይ ባልተገኙበት ጨዋታ የፋሲል ከነማው የቡድን መሪ ሀብታሙ ዘዋለ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ከነበሩ ባለልምድ ተጫዋቾች ጋር በተለይም ግብ ጠባቂው ይድነቃቸው ኪዳኔ ጋር በመሆን ጨዋታውን በጋራ መርተውታል።
በጨዋታው ሒደትም ሀብታሙ ዘዋለ ተደጋጋሚ የስልክ ልውውጦችን ሲያደርጉ የተስተዋለ ሲሆን ስለዚህ ጉዳይ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ “አሰልጣኝ ሥዩም ቤት ሆኖ ጨዋታውን በቴሌቪዥን እየተከታተለ ነበር። እያንዳንዱን የጨዋታ ሒደት እየተከታተለ ይደውልልኝ፤ መሻሻል የሚገባቸውን ነገሮች በደንብ እያወራን ነበር እኔም ብዙ የሱን ሀሳቦች እየፈፀምኩ ነበር።” ሲሉ ተደምጠዋል።
በተሰረዘው የውድድር ዘመን ቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ሰርዳን ዝቪድኖቭን ማሰናበቱን ተከትሎ ቡድኑ በአንድ ጨዋታ ላይ በህክምና ባለሙያ እና ነባር ተጫዋቾች በጣምራ ሲመራ ያስተዋልበት አጋጣሚ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።
👉 የኮኖና ምርመራ ውጤት እና የአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው አስተያየት
ድሬዳዋ ላይ እየተደረገ የሚገኘው የቤት ኪንግ የኢትዮጵያ የሪምየር ሊግ አነጋጋሪ ከሆኑ ነገሮች አንዱ የኮቪድ ወረርሺኝ ተፅዕኖ ነው። ከወትሮው በተለየ ሁኔታም በየቡድኖቹ ከአሰላለፍ ጠፍተው የማያውቁ ተጫዋቾች ከስብስባቸው ውጪ ሆነው እየተመለከትን እንገኛለን። በሌላ በኩል ክለቦች ጨዋታ ከማድረጋቸው 72 ሰዓታት አስቀድሞ የደረገው ምርመራ ውጤት ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ መግባት ከጀመረም ሰነባብቷል። በሁለቱ ሳምንታት ጨዋታዎች ችግሩ ያላገኛቸው እንዳሉ ሁሉ በርካታ አሉታዊ የምርመራ ውጤቶች የገጠሟቸውም አልጠፉም። ከእነዚህም መካከል አንደኛው ወላይታ ድቻ ነው።
የጦና ንቦቹ 17ኛው ሳምንት ላይ ሰባት የሚደርሱ ተጫዋቾቻቸውን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት መጠቀም ያልቻሉ ሲሆን በዚህም ሳምንት አስቀድሞ +ve የነበሩ የተወሰኑ ተጫዋቾችን ሲያገኙ በምትካቸው ደግሞ ሌሎችን ማጣታቸው አልቀረም። በመሆኑም ቡድኑ ያለተጠባባቂ ግብ ጠባቂ ውስን ተቀያሪዎችን ብቻ ይዞ ጨዋታውን አድርጓል። የቡድኑ አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራውም ከድሬዳዋ ከተማው ጨዋታ አስቀድሞ ከሱፐር ስፖርት ጋር በነበራቸው ቆይታ ሁኔታው እንዳልተዋጠላቸው የሚጠቁመውን ‘ምንም ተጫዋች ከማይያዝባቸው ሌሎች ክለቦች ልምድ እንወስዳለን’ የሚለው ምፀት አዘል አስተያየታቸው ትኩረት የሚስብ ነበር።
ዓበይት አስተያየቶች
👉 ደግአረገ ይግዛው ስለቶማስ ስምረቱ ቀይ ካርድ ውሳኔ
“የዳኝነት በደል በተከታታይ ነው እኛ ጋር የሚደርሰው። የዛሬው ደግሞ ጭራሽ ዓይን ያወጣ ዳኝነት ነው የነበረው። አንደኛ ለእነሱ አላስፈላጊ የሆኑ የኃይል አጨዋወት ይፈቅዳል። ቶማስ ጭራሽ ቢጫ ካርድ ሊያይም አይገባውም ነበር። ግን ቢጫ ካርድ ሰጥቶ ቀይ አሳየ። ትንሽ ያማል ፤ እንደቡድንም ደግሞ ትልቅ ጉዳት አለው።”
👉ገብረመድህን ሀይሌ ቡድኑ ካሰቡት በፈጠነ ጊዜ ወደ ውህደት ስለመምጣቱ
“ማት አያስችልም። አዳዲስ ተጫዋቾችም አሉ ፤ ወደምንፈልገው ደረጃ ገብተናል ማለት አይቻልም። ማለት የሚቻለው ከተወሰኑ ጨዋታዎች በኋላ አይተህ ነው። በሁለት ጨዋታ የምንኮፈስበት ወይም ደግሞ ተስፋ የምንቆርጥበት አይደለም። ከዚህ በኋላ ገና ስምንት ጨዋታ ይቀረናል። በእነዚህ ጨዋታዎች ደረጃችንን እያሻሻልን መሄድ ይጠበቅብናል። ነገር ግን ይሄ የአሸናፊነት ስሜት እንዲቀጥል እና በራስ መተማመን ስሜታችን እንዲጨምር ያደርጋል። ስለዚህ ጥሩ ነው። ከዛ መንፈስ ወጥቶ ወደ ተሻለ ደረጃ እየተሸጋገርን ነው ማለት ይቻላል።”
👉 ዘላለም ሽፈራው ለጋቶች ፓኖም ስለሰጡት ከአጥቂ ጀርባ የመጫወት ሚና
“አንደኛው ተጫዋቹ ካለው ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶችን የመስጠት አቅም አንፃር ነው። ዋናው ነጥባችን የነበረው ግን ሥንታየሁ ከፊት አለ እሱ ከኋላ አለ። ሁለት ጥሩ ተክለሰውነት ያላቸውን ተጫዋቾች እዛ ጋር ማቆም ማለት በተቃራኒው ከፍተኛ መከላከል ነው። በዚህም አራት የተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾች እዛው እንዲቀሩ አድርገናል። ስናጠቃ እየተከላከልንም ነው የሚል ሀሳብ ስለያዝን ነው።”
👉 ፀጋዬ ኪዳነማርያም ለአቡበከር ኑሪ ስላስተላለፉት መልዕክት
“ከዚህ ደቂቃ በኋላ ኳሶች በደንብ እየወጡ ከመስመር እንደሚመጡ እናውቃለን። በዚህ ላይ በግብ ጠባቂያችን አቡበከር እና በተካላካዮቻችን መሀል የነበረው ክፍተት በጣም የጠበበ ነው እና ትንሽ ነፃነት እንዲያገኙ ነው የፈለግኩት። የመሀል ተከላካዮቻችን ሸሽተው ከእርሱ ጋር ተቀራርበው ስለነበር ያ ቦታ ነፃ እንዲሆን እንዲገፋቸው ነው። ምክንያቱም በረኛ ከፊት ለፊቱ 21 ተጫዋች ይታየዋል። ስለዚህ አደጋ ከመፈጠሩ በፊት እሱ ማስያዝ መቻል አለበት። እንደሚታወቀው በጣም ወጣት ለሀገርም የሚጠቅም ግብ ጠባቂ ነው። እና ቡድኑን እንዲመራ ነበር። ያው ቀላል ሦስት ነጥብ አልነበረም ለእኛ ፤ አቻ ወጥተናል። ውጤቱን በፀጋ መቀበል ነው።”
👉ካሣዬ አራጌ የዛሬው ድል ለሀዋሳ ከተማው ሽንፈት ምላሽ ስለመሆኑ
“ማሸነፋችን ጥሩ ነው። ግን ጨዋታውን የተቆጣጠርንበት ሁኔታ ጥሩ አልነበረም። እኔ ጥሩ ነው የምለው እና ለቡድኑም ቀጣይነት መልካም የሚሆነው ጨዋታውን ተቆጣጥረን ብናሸንፍ ነው። ከዕረፍት መልስ መምራት ከጀመርን በኋላ ሰበታዎች በጥሩሁኔታ ጨዋታውን ተቆጣጥረውት ነበር። ግን ጎል ማግባት ስለፈለጉ ቸኩለው ነበር። ከውጤት አንፃር ጥሩ ነው ግን ከእንቅስቃሴው አንፃር መስተካከል ያለበት ነገር አለ።”
© ሶከር ኢትዮጵያ