የ18ኛ የጨዋታ ሳምንት መጠናቀቅን ተከትሎ ሌሎች የትኩረት ነጥቦች በዚህ ፅሁፍ ተካተዋል።
👉 በስታድየሞቻችን ችላ የተባለው መሰረታዊ ጉዳይ
በሀገራችን የሚገኙ ስታድየሞች እርግጥ ለእግርኳስ ውድድር ብቻ ተብለው የተሰሩ ባይሆኑም በእነዚሁ የኦሊምፒክ ስታድየሞች አንዱ መሠረታዊ ጉዳይ የመጫወቻ ሜዳው ጉዳይ ነው።
ይህ ጉዳይ ግን በሀገራችን እግርኳስ ችላ የተባለ ይመስላል። ትኩረቶች በሙሉ በከፍተኛ ወጪ የስታድየሙ የሲቪል መዋቅር ሥራ ለመስራት እንጂ ለሌሎች ሥራዎች በቂ ትኩረት እየተሰጠ እንደማይገኝ በተደጋጋሚ ማስተዋል ችለናል።
እውነታው ግን በርካታ ረብጣ ሚሊየኖች ወጪ በተደረገበት ስታድየም ዋነኛው ትርዒት የሚቀርበው የመጫወቻ ሜዳ ላይ መሆኑ ነው። ለትርዒቱ ምቹ ባልሆነ መደላድል ላይ ስታድየሙ በሰዎች ቢሞላም የሚፈለገው ዓይንን የሚስብ እንቅስቃሴ የመታየቱ ነገር ጥያቄ ውስጥ ይገኛል።
ከጅምሩ ጥያቄዎች የነበሩበት የድሬዳዋ ስታድየም የመጫወቻ ሜዳ ይባስ ብሎ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ቀን በጣለው ዝናብ የሜዳው አብዛኛው ክፍል ተበላሽቶ ተመልከተነዋል። ይህም ጨዋታዎችን ፈታኝ ሲያደርግ አስተውለናል። ከአንድ ዓመት በፊት በከፍተኛ ወጪ የመጫወቻ ሳሩን እና የፍሳሽ ማስተላለፍያው ተሻሽሎ እንደተገነባለት በተነገረው በዚህ ሜዳ ውሃ ቋጥሮ በጭቃ ለጨዋታ አስቸጋሪ ሲሆን መመልከት ግን በጣም የሚያስገርም ጉዳይ ነው።
የአዲስ አበባ እና ጅማ ዩኒቨርሲቲ ሜዳዎችም ዕድለኛ ሆነው የዝናቡ ፈተና አልደረሰባቸውም እንጂ ከዚህ የባሰ ውጤት ሊታይባቸው ይችል እንደነበር መገመት ይቻላል። ይህ ሁኔታ እስካሁን ውድድሩን ካስተናገዱ ከተማዎች ከባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታድየም ውጪ የአብዛኞቹ የሀገራችን ሜዳዎች መገለጫ መሆኑ ይበልጡኑ ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ የሚያሳስብ ይመስላል።
👉 በመለያ የተንበሸበሸው ድሬዳዋ ከተማ
በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተካፋይ ከሆኑ ክለቦች በድሬዳዋ ከተማ ደረጃ በዘንድሮው የውድድር ዘመን መለያዎችን የቀያየረ ቡድን ፈልጎ ማግኘት ይከብዳል።
ከዘንድሮው ውድድር ጅማሮ አንስቶ ቡድኑ በዚህኛው ሳምንት የተጠቀመውን ጨምሮ አራተኛ መለያውን ተጠቅሟል።
በወላይታ ድቻ ጋር በነበረው ጨዋታ የተጠቀሙት መለያ ከሌሎች የሚለየው በሀገር በቀሉ ጎፈሬ የትጥቅ አምራች ኩባንያ የተሰራ ሲሆን በተጨማሪም በደጋፊዎች ዘንድ እጅግ የሚወደደውን የብርቱካናማ በነጭ ዳማው መለያ ሀሳብ ያረፈበት መሆኑ ለየት ያደርገዋል።
👉 የቀድሞዎቹ አሰልጣኞች በስታድየም መገኘት
የሀገራችን የፕሪምየር ሊግ ውድድር በሱፐር ስፖርት ሽፋን ማግኘቱን ተከትሎ በቀጥታ ስርጭቱ ላይ ትንተና ከሚሰጡ የተቋሙ ባለሙያዎች በተጨማሪ ሌሎች በእግርኳስ ሙያ ውስጥ ያለፉ እና አሁንም በሥራ ላይ የሚገኙ ግለሰቦች በተጋባዥነት ሲቀርቡ ተመልክተናል። እስካሁንም የቀድሞው ተጫዋቾች የነበሩት ሳምሶን ሙሉጌታ፣ ጌታቸው ካሣ እና አዳነ ግርማ እንዲሁም የአሁኑ የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ተጠቃሾች ናቸው። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ የኢትዮ ኤሌክትሪክ የሴቶች ቡድን ዋና አሰልጣኝ የሆኑት ኢንስትራክተር መሠረት ማኒን በእንግድነት ተመልተናቸዋል።
ኢንስትራክተሯ የጨዋታ ሳምንቱ መክፈቻ በነበረው የወላይታ ድቻ እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ላይ በተንታኝነት መቅረባቸው ደግሞ አጋጣሚውን ልዩ ያደርገዋል። በዚህም በ 2008 የውድድር ዓመት ዳግም ወደ ሊጉ የመለሱትን እና ከግማሽ በላይ ውድድሩን በአሰልጣኝናት አብረው የዘለቁት የቀድሞው ክለባቸውን ጨዋታ ሲተነትኑ ተመልክተናል። ከዚህ በተጨማሪ ከተሰረዘው የውድድር ዓመት አንስቶ ዘንድሮ እስከ 11ኛው ሳምንት ቡድኑን የመሩት አሰልጣኝ ፍሰሀ ጥዑመልሳንም በስታድየሙ ተገኝተው ይየቀድሞ ክለባቸውን እና ሌሎች ጨዋታዎችን ሲከታታሉ ነበር። አሰልጣኝ ፍሰሀ ከጨዋታ በፊት እና በኋላ በሚሰጧቸው አስተያየቶችም ለስፖርቱ ተከታታይ የየሳምንቱ የትኩረት ነጥብ ሆነው መቆየታቸው ይታወሳል።
👉 ከቆይታ በኋላ ወደ ሜዳ የተመለሱት አርቢትር አነጋጋሪ ገጠመኝ
በሳምንቱ ትኩረት ከሳቡ ጉዳዮች መካከል የወልቂጤ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ ላይ የተመለከትነው ክስተት አንዱ ነው። የወልቂጤው ቶማስ ስምረቱ ከሲዳማው ጊት ጋትኮች ጋር በነበራቸው ጉሽሚያ መነሻነት ሁለቱም ላይ ቢጫ ካርድ የመዘዘቱ የዕለቱ አርቢትር ብርሀኑ መኩሪያ ለቶማስ ያሳዩት ሁለተኛ ቢጫ መሆንኑ ዘንግተው ጨዋታውን ቀጥለዋል። ነገር ግን ከደቂቃዎች በኋላ በአራተኛ ዳኛው ጠቋሚነት ስህተቱን አርመው ቶማስን በቀይ ካርድ ከሜዳ እንዲወጣ አድርገዋል።
ከቢጫ ካርዶቹ መወዛገብ ባለፈ ቶማስ ስምረቱ በቃላት ልውውጥ ካልሆነ በቀር ከጊት ጋር የነበረው ጉሽሚያ ለሁለተኛ ቢጫ ካርድ የበቃዋል ወይ ? የሚለውም ጉዳይ እንዲሁ አወዛጋቢ ሆኖ ለአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ተቃውሞ መነሻም ሆኖ አምሽቷል። አርቢትሩ በተመሳሳይ አነጋጋሪ ከነበረው እና ሦስት የፍፁም ቅጣት ምት ከሰጡበት የሦስተኛ ሳምንቱ የኢትዮጵያ ቡና እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ በኋላ ወደ ሜዳ ሲመለሱ ራሳቸውን በመሰል ውዝግብ ውስጥ ማግኘታቸው ግን ይበልጥ ትኩረት የሚስብ ጉዳይ ሆኖ አልፏል።
© ሶከር ኢትዮጵያ