የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫ እና የሽልማት ጉዳዮች …

አስራ ስምንት የጨዋታ ሳምንታትን የተጓዘው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በተመለከተ ዛሬ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ማብራርያ ተሰጥቷል። በዚህ ፅሁፍም የ2013 የውድድር ዘመን ሽልማትን በተመለከተ የተነሱ ነጥቦችን ተመልክተናል።

የሊግ ኩባንያው ሰብሳቢ መቶአለቃ ፈቃደ ማሞ በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተብራራው የ2013 የውድድር ዓመት ግንቦት 18 ፍፃሜውን የሚያገኝ ሲሆን ግንቦት 21 ላይ የአክሲዮን ማኅበሩ ጠቅላላ ጉባዔ ይካሄዳል። በዚሁ ዕለትም የመዝጊያ መርሐ ግብር በተመረጠ ሆቴል ተከናውኖ ለኮከቦች ሽልማት ይበረከታል።

ከዚህ ቀደም በሊጉ አንደኛ ዙር ግምገማ ወቅት በሽልማት ዙርያ መቶ አለቃ ፈቃደ ባደረጉት ንግግር የሚበረከተውን ሽልማት የሊግ ሥያሜ ስፖንሰር አድራጊው ተቋም እንደሚሸፍን በውል ላይ የነበረ ቢሆንም “ለኮከቦች ሽልማት ይበረከታል ከማለት ውጪ የተብራራ ነገር አለመኖሩን በመግለፅ የሽልማቱን ወጪ አንሸፍንም ብለውናል” በማለት መግለፃቸው ይታወሳል። በዛሬው መግለጫ ላይ ከመልቲቾይዝ እና ቤትኪንግ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን የገለፁት ሰብሳቢው የገንዘብ መጠኑ ባይታወቅም የሽልማት ወጪዎችን እንዲሁም ለፕሮግራሙ ማስኬጃ የሚወጡ ወጪዎች በቤትኪንግ እንደሚሸፈን ተናግረዋል።

በውድድር ዓመቱ በሚበረከተው ዋንጫ ዙርያ ማብራርያቸውን የሰጡት መቶ አለቃ ፈቃደ ዋንጫው የሚበረከትበትን ወቅት በመግለፅ ነበር። ከዚህ ቀደም በነበረው ተለምዷዊ አሰራር ለአሸናፊው ቡድን ዋንጫ የሚበረከተው በመዝጊያ ጨዋታ ላይ የነበረ ሲሆን ዘንድሮ ግን ቡድኑ ቻምፒዮን መሆኑን በሚያረጋግጥበት ጨዋታ ዕለት እንደሆነ ተናግረዋል።

የውድድሩ ዋንጫ በደቡብ አፍሪካ በሚገኝ ታዋቂ የዘርፉ ተቋም እየተሰራ እንደሚገኝ የተናገሩት ሰብሳቢው 80 ሴንቲሜትር ቁመት፣ ከ15-20 ኪግ ክብደት እና ወርቃማ ቀለም ይኖረዋል። ይህን ዋንጫ የሚያነሳ ቡድን በዛው የማያስቀረው ሲሆን ከተሸለመበት ዕለት እስከ አዲሱ ዓመት ውድድር ምዝገባ (ሐምሌ 2013) ድረስ ይሆናል። በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ተጠናቆ ሀገር ቤት እንደሚደርስ የሚጠበቀው የውድድሩ ዋንጫ የመድን (ኢንሹራንስ) ዋስትና እንደሚገባለት ሰብሳቢው ገልፀዋል። “ለኛ ትልቅ ንብረት ስለሆነ ኢንሹራንስ ይገባለታል። ለአሸናፊው ቡድን ተሰጥቶ ለተወሰነ ጊዜ ከቆየ በኋላም እኛ ጋር በክብር ይቀመጣል” ሲሉም በዋንጫው ዙርያ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

ከሽልማት ጋር በተያያዘ ሌላው የተጠቀሰው ጉዳይ በተለምዶ የሚሰጠው እንደየደረጃቸው የሜዳሊያ ሽልማት ነው። ይህ ከዚህ በኋላ እንደማይኖር የተናገሩት መቶ አለቃ ፈቃደ እያንዳንዱ ቡድን በየደረጃው የገንዘብ ሽልማት የሚኖረው ሲሆን ለዚህ የውውውር ዓመት ብቻ ከሌሎች ሽልማቶች በተጓዳኝ ለቻምፒዮኑ 1,000,000 ብር፣ ሁለተኛ ለሚጨርሰው 700,000 እንዲሁም ለሦስተኛው 500,000 ይበረከታል ብለዋል።

ከግለሰብ ሽልማቶች ጋር በተያያዘ በተሰጠው ማብራርያ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች የሚለየው 60% በባለሙያ እንዲሁም 40% በአጭር የፅሁፍ መልዕክት በሚሰበሰብ የሕዝብ ምርጫ ተሰባጥሮ ይሆናል። ከላይ እንደተገለፀውም መርሐ ግብሩ ግንቦት 21 ይከናወናል ተብሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ