ስለ 2014 የውድድር ዓመት አካሄድ ማብራርያ ተሰጥቷል

የ2013 የውድድር ዓመትን በጥሩ ሁኔታ እያስኬደ የሚገኘው የሊግ አክሲዮን ማኅበሩ በሀገራችን ባልተለመደ ሁኔታ ስለ ቀጣዩ የውድድር ዓመት ከወዲሁ የታቀዱትን ተግባራት በዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተነስቷል።

ግንቦት 18 ቀን 2013 እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቀው ሊጉ ከሐምሌ አንድ ቀን ጀምሮ ለአስራ አምስት ቀናት የክለቦችን ምዝገባ ያካሂዳል። የዝውውር መስኮቱ ከሐምሌ አንድ እስከ መስከረም ስድስት ክፍት የሚሆን ሲሆን መስከረም ሰባት የ2014 የውድድር ዓመት የሚጀመርበት ቀን ተብሎ በጊዜያዊነት ተይዟል። የአክሲዮን ማኅበሩ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ የአዲሱ የውድድር ዘመን መጀመርያ ወቅት በጊዜያዊነት የተያዘበትን ምክንያትም አብራርተዋል። ” በጊዜያዊነት ያስቀመጥንበት ምክንያት ብሔራዊ ቡድኑ የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎችን ከግንቦት መጨረሻ እስከ ጥቅምት መጀመርያ ድረስ ያከናወናል። በተለይ የመጨረሻዎቹ ሁለት የምድብ ጨዋታዎች ከመስከረም 26 እስከ ጥቅምት 2 ድረስ የሚከናወኑ በመሆኑ የሊጉን መጀመርያ ወቅት ይረብሹታል። ስለሆነም ሁለት አማራጭ ነው ያደረግነው። ነሐሴ 2013 ላይ መጀመር የሚለው አንደኛው ሀሳብ ሲሆን የ2014 ውድድርን ለምን 2013 ላይ እንጀምራለን የሚል ጥያቄ ተነስቷል። ሁለተኛው ደግሞ ብሔራዊ ቡድኑ ለኢንተርናሽናል ጨዋታ በፊፋ ህግ መሰረት ክለቦች ተጫዋቾችን የሚለቁት ከ7 እስከ 10 ቀን ነው። ስለዚህ በፊፋ ካሌንደር መሰረት ውድድር ለማካሄድ ነው ያሰብነው። ክረምት ላይ ብሔራዊ ቡድኑ ስለሚያርገው ዝግጅት እቅድ አናውቅም። ስለሆነም ውድድር የምንጀምረው መስከረም ሰባት ከሆነ ጥቂት ቀናት ውድድር ተደርጎ ለሁለቱ የምድብ ጨዋታዎች ተጫዋቾች ስለሚሄዱ መስከረም 15 ይቋረጣል። መስከረም 7 ጀምረን መስከረም 15 ማቋረጡ በክለቦች እና በብሮድካስት ተቋሙ ላይ ተፅእኖ ስለሚያሳርፍ ቀደም ብለን ነሐሴ ላይ እንጀምር የሚል ሀሳብ አለን። ብሔራዊ ቡድኑ በሐምሌ እና ነሐሴ ወር አንድ ቦታ ተቀምጬ እዘጋጃለሁ ካለ ደግሞ ይህም እቅድ ችግር ያጋጥመዋል። ስለዚህ ይህን በውይይት እና ድርድር ማጥራት አለብን። ብሔራዊ ቡድኑ ከዝግጅት ጋር በተያያዘ እኛን ምክንያት እንዲያደርግ አንፈልግም። ውድድሩን የምንጀምርበት ወቅት እንጂ ባቀድነው ጊዜ ለመጨረስ የሚሆን ጊዜ አለን።” ብለዋል።

ዘንድሮ በኮቪድ ፕሮቶኮል ምክንያት በዝግ እየተከናወነ የሚገኘው ውድድር ቀጣይ ዓመት እጣ ፈንታ በወረርሺኙ ላይ የሚመረኮዝ እንደሆነ የተናገሩት የአክሲዮን ማኅበሩ ሰብሳቢ የኮሮና ወረርሺኝ ስጋት በማይሆንበት ደረጃ ላይ መሆኑ ከተረጋገጠ ወደ ቀድሞ ተዟዙሮ የመጫወት በመመለስ እንደሚከናወን ገልፀዋል። በሁለቱም ሁኔታ ላይ ውድድሩ እንዴት ሊካሄድ እንደሚችልም በዚህ መልኩ አብራርተዋል።

ውድድሩ አሁን ባለው የኮቪድ ፕሮቶኮል የሚቀጥል ከሆነ

” ወረርሺኙ ባለበት የሚቀጥል ከሆነ በየትኛዎቹ ስታዲየሞች ይካሄዳሉ የሚለው በካፍ ክለብ ላይሰንሲንግ እና በራሳችን መመዘኛ መረጣ እናካሂዳለን። በቀጣይ የውድድር ዓመት 16 ክለቦች እንደሚኖሩ እንጠብቃለን። ስለዚህ እነዚህን ክለቦች የሚያስተናግድ የሆቴል አቅርት፣ በቂ የልምምድ ሜዳ፣ የፀጥታ፣ የቴሌቪዥን ስርጭት አመቺነት፣ የመጫወቻ ሜዳ ብቁነት መኖራቸውን ተመልክተን፤ ከዘንድሮው ልምድም ወስደን እንወስናለን። እንደ ቦርድ የወሰንነው እኛ መስፈርቶች አውጥተን ከተሞች ለማስተናገድ እንዲወዳደሩ ነው። ”

ወረርሺኙ ስጋት እንደማይሆን ተረጋግጦ ወደ ቀድሞ ሁኔታ ከተመለሰ…

” ከዚህ በኋላ ኮቪድ አስጊ ሁኔታ ላይ አይደለም የሚል ማረጋገጫ ከመንግሥት ከመጣ ተዟዙሮ መጫወት እና ተመልካች መግባት የሚፈቀድ ይሆናል። ግን ይህ ሲሆን እንደቀድሞው አጥር የሌላቸው፣ ተመልካች በአግባቡ የማይቀመጥባቸው፣ ለስርጭት አመቺ ያልሆኑ እና ፀጥታቸው አስተማማኝ ወዳልሆኑ ሜዳዎች አንሄድም። ስለዚህ ክለቦች መስፈርቱን ከሚያሟሉ ስታዲየሞች ጋር ኮንትራት ገብተው ያን ውል ሲያመጡልን እንደ ሜዳቸው እንመዘግብላቸዋለን። ”


© ሶከር ኢትዮጵያ