በ2014 የትግራይ ክልል ክለቦች ካልተሳተፉ በነማን ይተካሉ …?

የትግራይ ክልል ክለቦች ባለመሳተፋቸው ምክንያት የ2013 የውድድር ዓመትን በ13 ክለቦች መካከል እያካሄደ የሚገኘው የሊግ ካምፓኒው በቀጣዩ ዓመት ይህን ሁኔታ እንዴት እንደሚያስኬድ ሰብሳቢው መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ማብራርያ ሰጥተዋል።

የሊጉ ተሳታፊ የነበሩት መቐለ 70 እንደርታ፣ ስሑል ሽረ እና ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ በትግራይ ክልል ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ሳይወዳደሩ መቅረታቸው ይታወሳል። በዚህም ምክንያት በቀጣዩ ዓመት የመሳተፍ ሁኔታ ካመቻቹ እንዲመለሱ ተወስኖ በ13 ክለቦች መካከል እየተካሄደ ይገኛል። በክልሉ አሁን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ክለቦቹ ወደ ውድድር የመመለሳቸው ጉዳይ ያልለየለት በመሆኑ ቀጣዩ የውድድር ዓመት ላይ ካልተሳተፉ የሊጉ ተሳታፊ ቁጥር ስንት ይሆናል የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል።

ከሳምንታት በፊት በጁፒተር ሆቴል በተደረገው የሊጉ አንደኛ ዙር ስብሰባ ወቅት የሊጉ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ስለ ጉዳዩ በእርግጠኝነት መናገር እንደሚቸግራቸው መግለፃቸው ይታወሳል። “የትግራይ ክለቦችን ጉዳይ አሁን ላይ ለመመርመር ዝግጁ አደለንም። ማሳሰብ የምፈልገው ነገር ቢኖር ሁሉም ክለብ ለሻምፒዮናነት እና ላለመውረድ ይጫወት። ስለዚህ የትኛውም ክለብ መውረድ ካጋጠመው ይወርዳል።” ሲሉ መቶ አለቃ ፍቃደ በወቅቱ ገልፀው ነበር።

በዛሬው መግለጫ ላይ ከትግራይ ክልል ክለቦች ጋር የሥራ ግንኙነት እያደረጉ እንደማይገኙ የገለፁት ሰብሳቢው ወልዋሎ ባለፈው ዓመት ያልተከፈላቸውን ገንዘብ በደብዳቤ ከመጠየቅ ውጪ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ግንኙነት እንዳልፈጠሩ ተናግረዋል። ” አሁን ላይ ከክለቦቹ ጋር ግንኙነት እያደረግን አይደለም። የሊጉ ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር ከሰተ የክልሉ ሰው ናቸው። ባለፉት ሁለት ስብሰባዎቻችን ላይ ተካፍለዋል። እንኳን እኛ እርሳቸው (ዶ/ር ከሰተ ስለ መቐለ 70 እንደርታ ትንሽ እውቀቱ ቢኖራቸው እንጂ ስለሌሎቹ ክለቦች ወቅታዊ ሁኔታ ብዙም እውቀቱ የላቸውም። ክለቦቹ ለቀጣይ ዓመት ቢመዘገቡ ደስ ይለናል። ከብዙ ችግርም ያድኑናል። ሆኖም ያሉበትን ችግር ፈትቶ ወደ ውድድር መመለስ የእኛ ሳይሆን የስፖርት ኮሚሽን ሥራ ነው። እኛ ማወዳደር ነው ሥራችን። ” ሲሉ መቶ አለቃ ፈቃደ ተናግረዋል።

ሐምሌ አንድ የቀጣዩ ዓመት ምዝገባ ሲከናወን ሦስቱ ክለቦች እንደሚመዘገቡ ተስፋቸውን የገለፁት ዋና ሰብሳቢው ይህ የማይሳካ ከሆነ ውድድሩ በ16 ክለቦች መካሄዱን መቀጠል ስላለበት ተክተው የሚወዳደሩ ክለቦች የሚሳተፉበት መንገድ ላይ ገለፃ አድርገዋል። “ሦስቱ የትግራይ ክልል ክለቦች የሚሳተፉ ከሆነ በቀጥታ የመጨረሻ ሦስት ደረጃ የያዙ ቡድኖች ይወርዱና በ2014 አስራ ስድስት ክለቦች ይዘን እንቀጥላለን። ያ የማይሆን ከሆነ ከሆነ ደግሞ ከውሳኔ ላይ የደረስነው በፕሪምየር ሊጉ 11ኛ፣ 12ኛ እና 13ኛ ደረጃ ይዘው የሚያጠናቅቁ ክለቦች እንዲሁም በከፍተኛ ሊጉ ሦስቱ ምድቦች ላይ ሁለተኛ ደረጃን ይዘው የሚያጠናቅቁ በአጠቃላይ ስድስት ቡድኖች የመለያ ውድድር አድርገው የማይወዳደሩትን ክለቦች እንዲተኩ ነው። ” ያሉት ሰብሳቢው በማይሳተፉት ክለቦች መጠን (አንድ፣ ሁለት ወይም ሦስት) ክለቦች እንደሚተኩ ተናግረዋል።

የትግራይ ክልሎች የማይሳተፉ ከሆነ በነሱ የሚተኩ ክለቦችን ለመለየት የሚደረገው ውድድር በምን መልኩ እንደሚካሄድ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር መወያየታቸውን የገለፁት ሰብሳቢው በውድድሩ ላይ በሚሳተፉ ተጫዋቾች ዙርያ የአቋም ልዩነት መኖሩን ተናግረዋል። ” የእኛ አቋም የክለቦች ምዝገባ ከሐምሌ 1-15 ስለሚካሄድ በዛ ሒደት የሚያልፉ ተጫዋቾች በጨዋታዎቹ ላይ ይካፈሉ የሚል ሲሆን በፌዴሬሽኑ በኩል ውድድሩ የ2013 ስለሆነ በውድድር ዓመቱ የተመዘገቡ ተጫዋቾች ብቻ መሳተፍ ይኖርባቸዋል የሚል ነው። ሁለቱም በሀሳብ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸው ስለሆኑ በዝርዝር ከፌዴሬሽኑ ጋር ተወያይተንበት የምንወስነው ይሆናል።” ብለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ