የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አስራ ስምንተኛ ሳምንት ጨዋታዎችን በመመርኮዝ ይህንን የምርጦች ቡድን ሰርተናል።
አሰላለፍ 4-3-3
ግብ ጠባቂ
መሐመድ ሙንታሪ – ሀዲያ ሆሳዕና
ጋናዊው ግብ ጠባቂ በውድድር ዓመቱ ለሦስተኛ ጊዜ በምርጥ ቡድናችን ውስጥ ተካቷል። የሆሳዕናው የግብ ዘብ ቡድኑ ከአዳማ ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ ከኋላ ሆኖ ጥሩ አመራር ከመስጠት እና ከማነሳሳቱም በላይ እጅግ ለግብ የቀረቡት የማማዱ ኩሊባሊ፣ አብዲሳ ጀማል እና ኤልያስ ማሞ አደገኛ ሙከራዎች ማዳን ችሏል።
ተከላካዮች
ያሬድ ዳዊት – ወላይታ ድቻ
ቡድኑን በአምበልነት እየመራ የገባው ታታሪው የቀኝ መስመር ተከላካይ በውድድር ዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የምርጫችን አካል ሆኗል። ድቻ ጫና ውስጥ በነበረበት ሰዓት ላይ ለተገኘችው የፍፁም ቅጣት ምት መነሻ የነበረው ያሬድ ከመከላከሉ ባለፈ ወደ ፊት በመሄድ የቡድኑ ማጥቃት ለማገዝ ሲጥር ውሏል።
ሰለሞን ወዴሳ – ባህር ዳር ከተማ
15ኛው ሳምንት ላይ በምርጫችን ተካቶ የነበረው ሰለሞን ከአንድ ሳምንት በኋላ ተመልሷል። የረጅም ጊዜ አጣማሪው መናፍ ዐወል በሌለበት ከአህመድ ረሺድ ጋር በመሆን የቡድኑን የመሐል ተከላካይ ክፍል በመምራት እጅግ ከባድ በነበረው የፋሲሉ ጨዋታ ግብ ሳይቆጠርበት እንዲወጣ ለማድረግ ችሏል።
ፈቱዲን ጀማል – ሲዳማ ቡና
በቅጣት እና በአቋም መቀዛቀዝ ከአሰላለፍ እየራቀ የከረመው ፈቱዲን ሰንደይ ሙቱኩ በሁለት ቢጫ ካርድ ሳቢያ ባልነበረበት የአዳማው ጨዋታ ወደ አሰላለፍ መጥቶ ጥሩ እንቅስቃሴ አድርጓል። ሲዳማ ውጤት ማስጠበቅ ላይ ባተኮረባቸው ረጅም ደቂቃዎች ኳሶችን በተረጋጋ ሁኔታ በማራቅ ቡድኑ ይበልጥ እንዳይቸገር የበኩሉን ማድረግ ችሏል።
አሥራት ቱንጆ – ኢትዮጵያ ቡና
ድንቅ የውድድር ዓመት እያሳለፈ የሚገኘው አሥራት በሳምንቱ ምርጣችን ውስጥ ሲካተት ይህ ለስድስተኛ ጊዜው ነው። የሰበታ ከተማው ኦሰይ ማውሊን የመቆጣጠር ትልቅ ኃላፊነት የነበረበት ተጫዋቹ የማጥቃት ድፍረቱም አብሮት የነበረ ሲሆን ለአቡበከር ናስር የመጀመሪያ ጎል የመጨረሻ ኳስ ማመቻቸትም ችሏል።
አማካዮች
አለልኝ አዘነ – ሀዋሳ ከተማ
በአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ቡድን ውስጥ ከወንድምአገኝ ኃይሉ ጋር በመጣመር የማጥቃት ድርሻ የነበረው አለለኝ በተከላካይ አማካይነትም የመጫወት ልምዱን አስበን ይህንም ቦታ ሰጥተነዋል። ተጫዋቹ በጅማ አባ ጅፋሩ ጨዋታ ሦስት ከባድ ሙከራዎችን ሲያደር ሁለቱ ግብ ሳይሆኑ የቀሩት በአቡበከር ኑሪ ልዩ ጥረት ነበር።
ኤልያስ ማሞ – አዳማ ከተማ
በተክለ ሰውነታቸው ብቁ ከሆኑት የሀዲያ አማካዮች ጋር በተጋፈጠበት ጨዋታ የአዳማ መሐል ክፍል ከፍ ያለ ብልጫ እንዳይወሰድበት የኤልያስ መኖር ጉልህ ድርሻ ነበረው። እጅግ ንቁ የነበረው ኤልያስ በድንቅ ሁኔታ ለአብዲሳ ጀማል ጎል አመቻችቶ ሲያቀብል በሁለት አጋጣሚዎች ሌላኛውን አጥቂ ማማዱ ከሊባሊንም ከግብ ጠባቂ ጋር አገናኝቶት ነበር።
ዳዊት ተፈራ – ሲዳማ ቡና
ነባር ከሆኑ እና በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌም ዘመን ዕምነት ከተጣለባቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ዳዊት የቡድኑ የመሀል ክፍል ዋና ሰው እንደሆነ ቀጥሏል። ከያሬድ ከበደ ጋር ጥሩ ጥምረት የነበረው ዳዊት የማጥቃት እንቅስቃሴውን ሲዘውር ያመሸ ሲሆን የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት በአግባቡ መጠቀሙም ሲዳማን ባለድል አድርጓል።
አጥቂዎች
ቸርነት ጉግሳ – ወላይታ ድቻ
የመስመር አጥቂው ከቡድን ጓደኞቹ ጋር በቅቅብብል በመገናኘት ከቀኝ የሜዳው ክፍል በመነሳት ወደ ውስጥ እየገባ ያደርጋቸው የነበሩ እንቅስቃሴዎች የድቻን ጥቃት አስፈሪነት ጨምረውታል። የመጀመሪያው ግብ ሲቆጠር ቸርነት በሳጥን ውስጥ ከሁለት ተከላካዮች ጋር ታግሎ ለስንታየሁ ያመቻቸበት መንገድ ልዩ የነበረ ሲሆን ራሱም አንድ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ችሎ ነበር።
አቡበከር ናስር – ኢትዮጵያ ቡና
በሀዋሳው ጨዋታ ተፅዕኖውን ማሳደር ሳይችል ቀርቶ የነበረው አቡበከር በዚህ ሳምንት ሰበታ ላይ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር የግብ ስብስቡን 22 አድርሷል። የአጨራረስ ብቃቱ እያደር እያደገ መምጣቱን ባሳየበት በዚህ ጨዋታ ሦስተኛ ግብ ከማስቆጠር ያገደውም የግቡ አግዳሚ ብቻ ነበር።
ስንታየሁ መንግሥቱ – ወላይታ ድቻ
ወላይታ ድቻ ድሬዳዋ ከተማን በረታበት ጨዋታ ላይ እንደ ስንታየሁ ደምቆ መውጣት የቻለ ተጫዋች አልነበረም። ቁመተ መለሎው አጥቂ ሁለት ግብ አስቆጥሮ አንድ ሲያቀብል ወደ ኋላ በመመለስ ከአማካይ ክፍሉ ጋር ይገናኝ የነበረበትም መንገድም የቡድኑ የማጥቃት ሂደት ወደ ተጋጣሚ ሳጥን እንዲደርስ እገዛው የጎላ ነበር። አቡበከር ከግራ እየተነሳ መጫወት የሚችል በመሆኑም በዚህ ቦታ ተጠቅመነዋል።
አሰልጣኝ – ዘላለም ሽፈራው
እስካሁን በተደረገው ውድድር ግማሽ ያህሉን በአሰልጣኝነት መንበር ላይ ያልነበሩት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ለአራተኛ ጊዜ የሳምንቱ ምርጥ ሆነዋል። ቡድናቸው በኮቪድ ምክንያት በተመናመነበት እና ጥቂት ተጠባባቂ ተጫዋቾችን ብቻ ይዞ በገባበት ጨዋታ ከሽንፈት መልስ ወደ ድል እንዲመጣ ማድረጋቸው ለመመረጥ አብቅቷቸዋል።
ተጠባባቂዎች
አቡበከር ኑሪ – ጅማ አባ ጅፋር
ዳንኤል ደርቤ – ሀዋሳ ከተማ
ያሬድ ባየህ – ፋሲል ከነማ
በረከት ወልዴ – ወላይታ ድቻ
ሚኪያስ መኮንን – ኢትዮጵያ ቡና
ተመስገን ደረሰ – ጅማ አባ ጅፋር
አብዲሳ ጀማል – አዳማ ከተማ
© ሶከር ኢትዮጵያ