ሪፖርት | ሰበታ ከተማ ከመመራት ተነስቶ ጅማን አሸንፏል

የ19ኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ መርሐ-ግብር የሆነው የጅማ እና ሰበታ ጨዋታ በሰበታ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

የጅማ አባጅፋሩ አሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ቡድናቸው ከሀዋሳ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋራበት ቋሚ አሰላለፍ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ የዛሬውን ጨዋታ ጀምረዋል። በተቃራኒው በኢትዮጵያ ቡና ሽንፈት አስተናግደው ለዚህኛው ጨዋታ የቀረቡት ሰበታ ከተማዎች ከመጨረሻ ጨዋታቸው አራት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ መሳይ ጳውሎስ፣ ጌቱ ኃይለማርያም፣ ፎዓድ ፈረጃ እና ፍፁም ገብረማርያምን በቢያድግልኝ ኤልያስ፣ ዓለማየሁ ሙለታ፣ ቃልኪዳን ዘላለም እንዲሁም በአዲሱ ተጫዋቻቸው ክሪዚስቶም ንታምቢ ተክተዋል።

ቀዝቀዝ ያለ ፉክክር የታየበት የጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች እስከ 19ኛው ደቂቃ ድረስ ምንም የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ሳይስተናገድበት ቀጥሏል። በጨዋታው ላይ ግን ሰበታ ከተማዎች ኳስን በተሻለ በመቆጣጠር ሲጫወቱ ጅማዎች ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ በራሳቸው ሜዳ ተገድበው ሲንቀሳቀሱ ተስተውሏል። በጨዋታው የተሻለ ብልጫ የነበራቸው ሰበታዎችም በ19ኛው ደቂቃ አዲሱ ተጫዋቻቸው ንታምቢ ከርቀት በመታው ነገርግን የግብ ዘቡ አቡበከር ወደ ውጪ ባወጣው ኳስ መሪ ለመሆን ጥረዋል። በተጨማሪም ቡድኑ በጅማ ተከላካይ ለስህተት የቀረበ ውሳኔ የአቡበከርን መረብ ለማግኘት ጥሮ ነበር። በዚህም የግራ መስመር ተከላካዩ ያሬድ ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ አሌክስ አሙዙ አፀዳለሁ ብሎ ለጥቂት የራሱ መረብ ላይ አሳርፎት ነበር።

የተጋጣሚን አጨዋወት ያማከለ እንቅስቃሴ ማድረግ የቀጠሉት ጅማዎች በ33ኛው ደቂቃ መሪ የሆኑበትን ጎል ካልታሰበ አጋጣሚ አግኝተዋል። በዚህ ደቂቃም የቡድኑ ግብ ጠባቂ ምንተስኖት ከተፈቀደለት ክልል ውጪ ኳስ በእጁ ይዞ በመውጣቱ ምክንያት የተገኘውን የቅጣት ምት ሱራፌል አወል በጥሩ ብቃት ወደ ግብነት ቀይቶታል። ቀሪዎቹ የመጀመሪያው አጋማሽ ደቂቃም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት በጅማ አባጅፋት 1-0 መሪነት ተገባዷል።

ከእረፍት መልስ በቶሎ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ማድረጋቸውም የቀጠሉት ሰበታዎች በተደጋጋሚ የጅማን የግብ ክልል መጎብኘት ይዘዋል። ቃልኪዳን በ57ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ጎል ከጨዋታ ውጪ ከተባለ ከደቂቃ በኋላም ቡድኑ በማውሊ አማካኝነት ግብ አስቆጥሯል። ተጫዋቹም ከግራ መስመር ከቢያድግልኝ የተሻገረለትን ኳስ በነፃ አቋቋም ራሱን ነፃ በማድረግ ነው ቡድኑን አቻ ያደረገው። ከጎሉ በኋላም ወደ መሪነት ለመለወጥ ጥረታቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ሰበታዎች በግቡ ባለቤት አማካኝነት ሁለት ጠንካራ ሙከራዎችን በ60 እና 61ኛው ደቂቃ አድርገዋል። አስደንጋጮቹን ሁለት ሙከራዎች ያደረገው ማውሊ በድጋሜ በ65ኛው ደቂቃ ከቡልቻ የመጣለትን ኳስ ሞክሮት አቡበከር አድኖበታል።

በዚህኛው አጋማሽ ጫናዎች የበዛባቸው ጅማዎች በ68ኛው ደቂቃ መልካም አጋጣሚ በመልሶ ማጥቃት አግኝተው ነበር። በዚህ ደቂቃም የተገኘውን ኳስ ተመስገን ከቀኝ መስመር አክርሮ መትቶ የነበረ ቢሆንም ምንተስኖት ዕድሉን አምክኖበታል። የጅማን ተከላካዮች መረበሹን የቀጠለው ማውሊ በ73ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ናትናኤል በደረቱ ያመቻቸለትን ኳስ ወደ ግብ ልኮት ተከላካዮች ተደርበው አውጥተውበታል። በመጨረሻም ግን ማውሊ ቡድኑን መሪ ለማድረግ የለፋበትን ውጤት አግኝቷል። በዚህም በ82ኛው ደቂቃ ንታምቢ ከመሐል ሜዳ ያሻገረውን ግሩም ረጅም ኳስ ከተከላካዮች አምልጦ በተረጋጋ አጨራረስ ኳስ እና መረብን አገናኝቶ ሰበታ መሪ ሆኗል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት ሰበታን አሸናፊ አድርጓል።

ውጤቱን ተከትሎ ከመምራት ተነስተው ሽንፈት ያስተናገዱት ጅማዎች በ11 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ ጣፋጭ ሦስት ነጥብ ያገኙት ሰበታዎች ደግሞ ነጥባቸውን 22 በማድረስ ወደ ሰባተኛ ደረጃ ተሸጋግረዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ