የነገ ምሽቱን ጨዋታ በዳሰሳችን እንዲህ ተመልክተናዋል።
በሳምንቱ ከሙደረጉ ጠንካራ መርሐ ግብሮች ውስጥ የሚጠቀሰው ይህ ጨዋታ ባለፉት ሁለት ሳምንታት የሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ አሰልጣኞችን የሚያገናኝ ይሆናል። ድሬዳዋ ከተማን በመርታት ከፋሲሉ ሽንፈት ያገገሙት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ከመውረድ ሀሳብ ርቀው ሲገኙ ከዚህም በላይ ደረጃቸውን ለማሻሻል ይፋለማሉ። በተጋጣሚው በሦስት ነጥቦች የሚበለጠው የአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ሀዋሳ ከተማም ከሰባት ጨዋታዎች በኋላ አሳክቶት የነበረው ድል በጅማ መልሶ ቢቋረጥም ዳግም መልሶ ካሸነፈ ከወራጅ ቀጠናው ያለውን ልዩነት እንደ ድቻ ሁሉ ወደ ስምንት ከፍ ማድረግ ይችላል።
በወቅታዊ አቋም እና የቡድን ጥንካሬ ወላይታ ድቻ በሊጉ ምርጥ ከሚባሉ ቡድኖች ውስጥ አንዱ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። የስብስብ ጥራቱ መጨመር እና የወጣት ተጫዋቾቹ በመጀመሪያው ዙር ከፍ ያለ የጨዋታ ጊዜ ማግኘት ቡድኑን የተሻለ ዝግጁነት ላይ አድርሶታል። ኮቪድ እንደፈጠረበት ጫና ሳይሆን ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ላይ ጥሩ ተጋጣሚ ሆኖ መቅረብ የቻለውም በእነዚህ ምክንያቶች ይመስላል። በጥሩ የአዕምሮ ጥንካሬ ላይ የሚገኘው ድቻ ነገም በተመሳሳይ አኳኋን የጨዋታ ጉልበት ያለው አቀራረብ ይዞ እንደሚቀርብ ይጠበቃል።
ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በአስደናቂ የመከላከል ብቃት ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ደግሞ ተደጋጋሚ ዕድሎችን መፍጠር ችሎ በነበረበት የማጥቃት አቀራረብ የተመለከትነው ሀዋሳ ከተማም እስካሁን ያለው የድሬ ቆይታው ጥሩ የሚባል ነው። በተመሳሳይ ኮቪድ ወሳኝ ተጫዋቾቹን የነጠቀው ሀዋሳ ባለው ቀሪ ስብስብ ጥሩ ሁለት ዘጠና ደቂቃዎችን ማሳለፍ መቻሉ እንደ ድቻ ሁሉ ተጠባባቂ ወንበር ላይ የነበሩ ተጫዋቾቹ የጨዋታ ዝግጅት የሚታማ እንዳልሆነ አሳይቶናል።
ተጋጣሚዎቹ በርከት ያሉ ወጣት ተጫዋቾችን የሚጠቀሙ መሆኑ እና አብዛኞቹ በርካታ ደቂቃዎችን ሲያገኙ መቆየታቸው ጨዋታው ጥሩ ግለት ሊኖረው እንደሚችል ተስፋ እንዲጣልበት ያደርጋል። በመሆኑም ቡድኖቹ በሽግግሮች ላይ ሲሆኑ በየአቅጣጫው የሚፈጠሩ የአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ውጤቱን የመወሰን አቅማቸው ከፍ እንደሚል ይጠበቃል። ከሰሞኑ ጨዋታዎች አንፃር ስንመለከተው ደግሞ በማጥቃቱ ረገድ ያሳዩት ጠንካራ ጎን ጎሎችን እንድንጠብቅ ያደርገናል። ወላይታ ድቻ በሦስተኛው የሜዳ ክፍል መዳረሻ ላይ በአጥቂዎቸ እና በአማካዮቹ መካከል ወደ ግብ ሙከራነት የተቀየሩ ፈጣን ቅብብሎችን ሲከውን መታየቱ ሀዋሳ ደግሞ ከቆሙ እና ከተሻጋሪ ኳሶች ለተጋጣሚ ፈታኝ ሆኖ መታየቱ ሀሳባችንን ያጠናክርልናል። ነገር ግን በድቻ በኩል የመናበብ ችግር በሀዋሳ ደግሞ የትኩረት ማጣት መንስዔ የሆኑባቸው ግቦችን ማስተናገዳቸው አንዳቸው ለሌላኛቸው በራቸው እንዲከፍቱ ሊያደርጋቸው ይችላል።
የኮቪድ ውጤታቸውን ሳይጨምር በወላይታ ድቻ በኩል የጉዳት እና የቅጣት ዜና የሌለ ሲሆን ሀዋሳዎች ተከላካይ አማካያቸው ዳዊት ታደሰን በጉዳት ሳቢያ ያጣሉ።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– በሊጉ 13 ጊዜ ተገናኝተው ወላይታ ድቻ 6 በማሸነፍ ቀዳሚነቱን ሲይዝ ሀዋሳ 3 ጨዋታ አሸንፏል። በአራት አጋጣሚዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ ድቻ 14 ሀዋሳ ደግሞ 12 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።
* ወቅታዊው የኮቪድ ወረርሺኝ በቡድኖቹ የስብስብ ምርጫ ላይ እያሳደረ ካለው ተለዋዋጭነት አንፃር ግምታዊ አሰላለፍ ለማውጣት አዳጋች በመሆኑ የወትሮው የአሰላለፍ ትንበያችን በዳሰሳው ያልተካተተ መሆኑን እንገልፃለን።
© ሶከር ኢትዮጵያ