ቅድመ ዳሰሳ | ጅማ አባ ጅፋር ከ ሰበታ ከተማ

በ19ኛው ሳምንት ቀዳሚ ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

ጅማ አባ ጅፋር ከሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ በ18ኛው ሳምንት አንድ ነጥብ ማሳካት ችሏል። ይሁን እንጂ ከበላዩ ካለው ድሬዳዋ ጋር ያለውን ልዩነት ወደ አምስት ከማጥበብ ያለፈ መሻሻል ማምጣት አልቻለም። በነገውም ጨዋታ በድጋሚ ክፍተቱን የመቀነስ ዓላማ ይዞ ወደ ሜዳ ይገባል። ከወራጅ ቀጠናው በሦስት ነጥብ ርቀት ላይ የሚገኘው ሰበታ ከተማም የነጥብ ስብስቡን ከዚህ በላይ ከፍ ለማድረግ አድርጎ ስጋቱን ለመቀነስ ጨዋታን አጥብቆ ይፈልገዋል። ይህንን ማድረግ ከቻለ ደረጃውንም በሁለት የማሻሻል ዕድል ይኖረዋል።

ከተጋጣሚው የጨዋታ ባህሪ አንፃር ጥንቃቄ ላይ አመዝኖ በቶሎ ወደ ግብ የመድረስ ዕቅድ እንደሚኖረው የሚጠበቀው ጅማ አባ ጅፋር በዚህ ረገድ ባለፉት ጨዋታዎች አንዳንድ ቅፅበቶች ላይ ያሳየው ጥንካሬ ተጠቃሚ ሊያደርገው ይችላል። ነገር ግን በአሌክስ አሙዙ እና ውብሸት ዓለማየሁ ጥሩ ጥምረት እያሳየ የሚገኘው የኋላ ክፍሉ እና አጠቃላይ የቡድኑ የመከላከል አወቃቀር እርጋታን ካልተላበሰ የማጥቃት ፍሬው ብቻውን ለውጤት እንደማያበቃው መናገር ይቻላል። እስካሁን ካደረጋቸው 17 ጨዋታዎች በስድስቱ ቀድሞ ግብ አስቆጥሮ በድል መጨረስ ያልቻለው አባ ጅፋር ምንም ያህል ውጤቱን የሚያስፈልገው ቢሆን ከስሜት በወጣ አኳኋን ጨዋታዎችን መቋጨት መቻል ይጠበቅበታል።

ይህ አጋጣሚ በመጀመሪያው ዙር ከሰበታ ጋር ባደረገው ጨዋታም ተከስቶ የነበረ መሆኑም ቡድኑ ይበልጥ ትኩረት ሰጥቶት እንዲገባ እንደሚያደርገው ይታመናል። ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች ቢበዛ በጨዋታ ከአንድ በላይ ጎል ማስቆጠር አለመቻሉም ሲታሰብ ዳግመኛ ኳስ እና መረብን ቀድሞ የማገናኘት በለስ ከቀናው የመከላከል ሽግግሩ እና አደረጃጀቱ ላይ ትኩረት አድርጎ ቢገባ አስገራሚ አይሆንም።

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ሽንፈት ያገኘው ሰበታ ከተማ ነገ ከቡና የተለየ ተጋጣሚ ጋር ይገናኛል። ያለተፈጥሯዊ የተከላካይ አማካይ ወደ ሜዳ መግባቱ አማካይ ክፍል ላይ የተጋጣሚ አማካዮች ነፃነት እንዲያገኙ ማድረጉ ጎድቶት የነበረው ሰበታ በጅማው ጨዋታ ደግሞ አመዛኙን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ያለ ጫና ኳስ የመቆጣጠር ዕድል እንደሚኖረው ይገመታል። ነገር ግን አቡበከር ናስርን ለማቆም የተቸገረው የኋላ ክፍሉ አሁንም እንደ ተመስገን ደረሰ ባሉ መልካም አቋም ላይ በሚገኙ ተጫዋቾች እንዳይፈተን ፈጣን ጥቃት ሲሰነዘር በምን መንገድ ማቆም እንዳለበት ማሰብ የግድ ይለዋል።

ከዚህ ባለፈ የቡድኑ የማጥቃት ሂደት እምብዛም ባልተከፈቱ ቦታዎች ላይ ዕድሎችን የመፍጠር ብቃቱ የሚፈተንበት ጨዋታም ሊሆን ይችላል። ፊት መስመር ላይ አስፈሪ ሊባል የሚችል የሦስትዮሽ ጥምረት መፍጠር የቻለው ሰበታ ከዚህ ጥንካሬ ውጤት ለማግኘት ከቁጥጥር ድርሻው ባለፈ በቂ ኳሶችን ለግብ እንዲሆኑ አድርጎ ማመቻቸት መቻል ይኖርበታል። ይህንን ለማድረግም የመስመር ተከላካዮቹን የማጥቃት ድፍረት መጨመር እና የአጥቂዎቹን የኋላዮሽ እንቅስቃሴ ከቡድኑ የኳስ ፍሰት ጋር ማጣጣም ይጠበቅባቸዋል።

በነገው ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋር መላኩ ወልዴ ፣ አማኑኤል ተሾመ ፣ ሮባ ወርቁ እና ብዙአየሁ እንዳሻውን በጉዳት ምክንያት እንደማያሰልፍ ሰምተናል። በሰበታ ከተማ በኩል ደግሞ ልምምድ የጀመረው ታደለ መንገሻ እንዲሁም ጌቱ ኃይለማርያም እና ዱሬሳ ሹቢሳ ለጨዋታው አይደርሱም።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– የቡድኖቹ የሊግ የመጀመሪያ ግንኙነት በነበረው የዘንድሮው ጨዋታ በፍፁም ገብረማርያም እና ሮባ ወርቁ ጎሎች 1-1 ተለያይተዋል።

* ወቅታዊው የኮቪድ ወረርሺኝ በቡድኖቹ የስብስብ ምርጫ ላይ እያሳደረ ካለው ተለዋዋጭነት አንፃር ግምታዊ አሰላለፍ ለማውጣት አዳጋች በመሆኑ የወትሮው የአሰላለፍ ትንበያችን በዳሰሳው ያልተካተተ መሆኑን እንገልፃለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ