የ19ኛው ሳምንት የማሳረጊያ ቀን ቀዳሚ በሆነው ጨዋታ ዙሪያ እነዚህን ነጥቦች አንስተናል።
በሰንጠረዡ የታች እና የላይኛው ፉክክር ውስጥ ይገኙ እንጂ የቡድኖቹ የነገው ጨዋታ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ፋሲል ከነማ የአምስት ተከታታይ የድል ጉዞው በባህር ዳር ቢቋረጥም ከተከታዩ ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት እምብዛም የሚያሰጋው አይደለም። ያም ቢሆን ግን በቶሎ ወደ አሸናፊነት በመመለስ ልዩነቱን ዳግም ለማስፋት ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅበታል። ሲዳማ ቡና በበኩሉ ከረጅም ጊዜ በኋላ ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን ማሸነፍ መቻሉ በመውረድ ስጋቱ ላይ ተስፋው እንዲለመልም ሆኗል። ነገ ሙሉ ነጥብ ማሳካት ከቻለም ድሬዳዋ ከተማ የነጠቀውን የ10ኝነት ደረጃ መልሶ የማግኘት ተስፋ አለው።
ተደጋጋሚ ሽንፈት የሚያገኛቸው ቡድኖች ያለባቸው በራስ ያለመተማመን ችግር በሲዳማ እያተቃለለ ይመስላል። በወልቂጤው ጨዋታ አልፎ አልፎ ይታይበት የነበረው መረበሽ እና ከራስ ሜዳ በእርጋታ ቅብብሎችን እያደርጉ የመውጣት ችግር ግን አሁንም ሙሉ ለሙሉ የሚፈለገው ደረጃ ላይ እንዳልደረሰ ይናገራል። በሌላ በኩል ከሉጉ መሪ እና ከአንድ ጊዜ በላይ ሽንፈት ያልገጠመው ቡድን ጋር መገናኘቱ ውጤት ከቀናው የስነ ልቦና ትርፉን ከፍ ያደርግለታል። በተጋጣሚ ወቅታዊ ብቃት እና ደረጃ አቋማቸው የማይለዋወጡት ፋሲሎች ግን ነገም በተለመደው ደጋግሞ የማጥቃት ሀሳብ ውስጥ ሆነው ጨዋታው ን እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
በጨዋታው ከሚጠበቁ ፍልሚያዎች አንፃር በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ምንም ግብ ያላስተናገደው የሲዳማ የኋላ ክፍል ነገ በስል የአጥቂ ክፍል የሚፈተን ይሆናል። በተመሳሳይ እንደ አዲስ ይዋቀር እንጂ በቶሎ አስፈሪ መሆን የቻለው የቡድኑ የፊት ክፍልም ከጠንካራው የፋሲል የኋላ ክፍል ጋር ይጋፈጣል። እንቅስቃሴን ከኋላ በመጀመርም ሆነ ጥቃቶችን በማቋረጥ ከፍተኛ እርጋታ የተላበሱት የአፄዎቹ ተከላካዮች ከግዙፎቹ አጥቂዎች ጋር ሲገናኙ ምን ይፈጠራል የሚለው ከወዲሁ ተጠባቂ ሆኗል። ከጨዋታ ምርጫ አንፃር ግን ፋሲል ከነማ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን በማግኘት የሜዳውን ስፋት ከግምት ባስገባ አኳኋን ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት ሲያደርግ ሲዳማ ቡና የመልሶ ማጥቃት ምርጫ እንደሚኖረው ይገመታል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– በሊጉ እስካሁን 7 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ሲዳማ ቡና አራት ፋሲል ከነማ ደግሞ ሦስት ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል። አቻ በማያውቋቸው ሰባት ጨዋታዎችም ሲዳማ 10 ሲያስቆጥር ፋሲል 8 ማስቆጠር ችሏል።
* ወቅታዊው የኮቪድ ወረርሺኝ በቡድኖቹ የስብስብ ምርጫ ላይ እያሳደረ ካለው ተለዋዋጭነት አንፃር ግምታዊ አሰላለፍ ለማውጣት አዳጋች በመሆኑ የወትሮው የአሰላለፍ ትንበያችን በዳሰሳው ያልተካተተ መሆኑን እንገልፃለን።
© ሶከር ኢትዮጵያ